Saturday, 01 August 2015 14:53

የታሊባኑ መሪ ሙላህ ሞሃመድ ኦማር ሞቷል ተባለ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የታሊባን ቃል አቀባይ፤“መሪያችን አልሞተም፣ አሁንም እየመራን ነው“ ብሏል
 
    የአፍጋኒስታን የደህንነት ባለስልጣናት፤ የታሊባኑ መሪ ሙላህ ሞሃመድ ኦማር ከሁለት አመታት በፊት መሞቱን አረጋግጠናል ሲሉ መናገራቸውንና የቡድኑ ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ መሪያችን በህይወት አለ፤ አሁንም እየመራን ነው ሲሉ ማስተባበላቸውን ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
የአፍጋኒስታን ብሄራዊ የደህንነት ዳይሬክቶሬት ቃል አቀባይ አብዱል ሃሲብ ሳዲቅ እንዳሉት፣ ሙላህ ሞሃመድ ኦማር በጸና ታሞ በነበረበት በካራቺ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ሆስፒታል በሚያዝያ ወር 2013 ህይወቱ እንዳለፈ አረጋግጧል፡፡
ሙላህ ሞሃመድ ኦማር ለመጨረሻ ጊዜ በአደባባይ የታየው እ.ኤ.አ በ2001 እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ግለሰቡ ሞቷል ተብሎ ሲነገር ይህ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑንና አሜሪካም በዚህ ሳምንት የወጣውን መረጃ ትክክለኛ ነው ብላ መቀበሏን ገልጧል፡፡
የታሊባኑ መሪ ሙላህ ሞሃመድ ኦማር ልጅ ሙላህ ያቆብ፣ አባቱ ከአመታት በፊት እንደሞተ ማመኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ተቀማጭነቱ በፓኪስታን የሆነ አንድ አፍጋኒስታናዊ የታሊባን ከፍተኛ የጦር መሪም፣ ሙላህ ሞሃመድ ኦማር ከአመታት በፊት በተፈጥሯዊ ሞት ከዚህ አለም መለየቱን ለሮይተርስ መናገሩን ገልጧል፡፡
ታሊባንን የመምራት ሃላፊነቱን ልጅዬው ሙላህ ያቆብ እንደተረከበ እየተነገረ ሲሆን፣የታሊባን ቃል አቀባይ ቃሪ የሱፍ አህመዲ በበኩሉ፤መረጃው መሰረተ ቢስ ሃሜት ነው ሲል ማስተባበሉ ተዘግቧል።
እኔ እስከማውቀው ድረስ ሙላህ ሞሃመድ ኦማር አሁንም በህይወት አለ፣ቡድኑን የመምራት ሃላፊነቱንም በአግባቡ እየተወጣ ይገኛል ብሏል ቃል አቀባዩ፡፡

Read 3449 times