Saturday, 01 August 2015 14:50

ከዓለማችን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ግማሽ ያህሉ የፌስቡክ ደንበኞች ናቸው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 - ከፌስቡክ ደንበኞች 65 በመቶው በየዕለቱ ይጠቀማሉ
            - ባለፉት ሶስት ወራት ገቢው 4 ቢሊዮን ደርሷል
   ኢንተርኔትን ከሚጠቀሙ 3 ቢሊዮን ያህል የተለያዩ የአለማችን አገራት ዜጎች መካከል ግማሽ ያህሉ ወይም 1.49 ቢሊዮን የሚሆኑት የታዋቂው ማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ ተጠቃሚ መሆናቸውን ኩባንያው ረቡዕ እለት ማስታወቁን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
የተጠቃሚዎቼ ቁጥር ባለፉት ሶስት ወራት በ13 በመቶ አድጓል ያለው ፌስቡክ፣ ከተጠቃሚዎቹ ውስጥ 65 በመቶ የሚሆኑትም በየዕለቱ አካውንታቸውን ከፍተው የሚጠቀሙ ትጉህ ደንበኞቹ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
የስማርት ፎን ተጠቃሚዎች በየአምስት ደቂቃው ለአንድ ደቂቃ ያህል ጊዚያቸውን ከፌስቡክ ጋር ያጠፋሉ ያለው ፌስቡክ፣ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት መስፋፋት ለማህበራዊ ድረገጹ ተጠቃሚዎች ቁጥር ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ አስታውቋል፡፡
በስማርት ፎን ተጠቃሚዎች በኩል የሚያገኘው የማስታወቂያ ሽያጭ ገቢ ጠቀም ያለ እንደሆነ የገለጸው ፌስቡክ፣ ገቢው ባለፉት ሶስት ወራት በ39 በመቶ በማደግ 4 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና ከዚህ ውስጥም 2.9 ቢሊዮን የሚሆነውን ከስማርት ፎን ማስታወቂያ እንዳገኘው ጠቁሟል፡፡

Read 1608 times