Saturday, 01 August 2015 14:31

362 ሚ. ብር የፈጀው ዮቤክ ኮሜርሻል ሴንተር ዛሬ ይመረቃል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

   የገበያ ማዕከሉ ባለ 14 እና 10 ፎቆች መንትያ ሕንፃ ነው

         ለተለያዩ የኤሌክትሪክና የንፅህና ቤት (ሳኒተሪ) ዕቃዎች ንግድና መገበያየነት ታቅዶ የተገነባው ዮቤክ ቢዝነስ ሴንተር ዛሬ ጠዋት ከ4፡00 ጀምሮ እንደሚመረቅ የዮቤክ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡
የዮቤክ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ብርሃነ ግደይ፣ በተለይ ለአዲስ አድማስ በሰጡት መግለጫ፤ በሌሎች አገሮች ተመሳሳይ ዕቃዎች የሚሸጡት በአንድ አካባቢ እንደሆነ ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያ ግን እንዲህ ዓይነት አሠራር የለም። ሁሉም ዕቃዎች፡- የኤሌክትሪክ፣ የግንባታ፣ አልባሳት፣ መለዋወጫ፣ ሸቀጣሸቀጦች፣ የሚነገዱት ተበታትነውና ተቀላቅለው ነው፡፡
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የኤሌክትሪክና የመፀዳጃ ቤት ዕቃዎች በአንድ ቦታ ያቀረበ ዮቤክ ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡ በሕንፃው 180 ኩባንያዎች ስላሉ፣ ዕቃዎቹን ለመግዛት የፈለገ ሸማች መርካቶ፣ ፒያሳ፣ ቄራ፣ ሳሪስ፣ በመንከራተት ጊዜውን አያባክንም፡፡ በተለምዶ ሰንጋ ተራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ወደ ተክለሃይማኖት በሚወስደው መንገድ ዳር ወደተከፈተው ኖቤክ ኮሜርሻል ሴንተር መጥቶ ደስ ያለውን ዕቃ መርጦ ይገዛል በማለት አስረድተዋል፡፡
የንግድ ሱቆች የያዙት እስከ 4ኛ ፎቅ ሲሆን ከዚያ በላይ ያሉት ክፍሎች ለመንግሥት መ/ቤቶች፣ ለግል ድርጅቶችና መንግሥታዊ ላልሆኑ ተቋማት ለቢሮ ይከራያሉ ብለዋል፤ አቶ ብርሃነ፡፡ የገበያ ማዕከሉ ሦስት ባንኮች (አንበሳ፣ ወጋገን እናት) ሁለት ሬስቶራንቶች፣ በአንደ ጊዜ 60 ሰዎች የሚያመላልሱ 4 ሊፍቶች፣ የተለያየ ደረጃ ያላዠው 4 ምግብ ቤቶች፣ ውሃ ቢጠፋ ለአንድ ወር የሚያገለግል 150ሺህ ሊትር መጠባበቂያ፣ ለ150 መኪናዎች ማቆሚያ ስፍራ እንዳለው ገልፀዋል፡፡
ሁለቱ ህንፃዎች በ2000 ካ.ሜ. ቦታ ላይ ነው ያረፉት፡፡ ከህንፃው ትልቅነትና ስፋት አኳያ 950 መኪኖች ማቆሚያ ለህፃው ተከራዮችና ወደ ማዕከሉ ለሚመጡት እንግዶች በቂ አይደለም፤ በጣም ያንሳል ያሉት አቶ ብርሃነ፣ በአጠገባቸው ባዶ ቦታ ስላለ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ዲዛይን ውጭ አገር አሰርተው ለመንግሥት ማቅረባቸውንና ከተፈቀደላቸው በ50 ሚሊዮን ብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡  
ህንፃውን ለመገንባት ሲያስቡ ፕሮጀክቱ ይፈጃል ተብሎ የተገመተው አሁን የወጣው 362 ሚሊዮን ብር እንዳልነበረ ጠቅሰው፣ ወጪው የበዛው በየጊዜው የግንባታ ዕቃዎች ዋጋና የሰራተኛ ክፍያ ስለሚጨምር የጣልያን ኮንትራክተሩ 3 ጊዜ የዋጋ ጭማሪ በማድረጉ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አቶ ብርሃነ ግደይ በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ አካባቢ ባለ 5 ኮከብ ሆቴል እየሰሩ ያሉ ኢንቨስተር ናቸው፡፡  

Read 2136 times