Saturday, 01 August 2015 14:30

ኦባማ፤ያዘዙልንን መድሃኒት አወሳሰድ አልነገሩንም!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(12 votes)

 የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ኦባማን አብጠለጠሉ  
                        ግን ፕሬዚዳንቱ ተናገሩ ነው አቀነቀኑ የሚባለው?
        ማንም የዕድሜ ልክ ፕሬዚዳንት መሆን የለበትም - (ኦባማ ሥልጣን የሙጥኝ ላሉ የአፍሪካ መሪዎች የተናገሩት)
                                    
           እናንተ----የአገር መሪ እንደ ሆሊውድ ዝነኞች (Celebrities) አድናቂዎች ይኖሩታል ብዬ አስቤም አልሜም አላውቅም፡፡ (ባስብ ነበር የሚገርመው!) ሆኖም ዕድሜ ለኦባማ!! መሪም አድናቂዎች እንዳሉት በአይኔ አየሁ፤በጆሮዬ ሰማሁ። (በኬንያም በኢትዮጵያም!) ሰውየው በጥቂት ቀናት ጉብኝታቸው----የኬንያናና የኢትዮጵያን ወጣቶች ቀልብ ሊያሸፍቱ እኮ ምንም አልቀራቸው…ግን በድለላ ወይም በማማለል አይደለም (ሃቁን በማፍረጥ ነው!) ሁሌም አገራቱ የተጓዙበትን ጎዳና እና የደረሱበትን ዕድገት በማድነቅ ነው የሚጀምሩት፡፡ ኦባማ ሲናገሩ በልበሙሉነት ነው፡፡ ልበሙሉ ሆነው ልበሙሉ ያደርጋሉ!! ንግግራቸው ፍቅርን…ተስፈኝነትን-----መነቃቃትን የሚሞላ ነው፡፡  
በነገራችን ላይ----- የሴኩሪቲ ነገር ሆኖ ነው እንጂ ስንቶቹ ኮረዶች ጡታቸውን በገለጡ ነበር (ለማስፈረም እኮ ነው!) እዚህ ጦቢያ ----- በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ወጣቶች ለኦባማ  ድጋፋቸውን በጩኸትና በፉጨት የገለፁት፤ስልጣንን እንደ ርስታቸው ይዘው ስለተቀመጡ የአፍሪካ መሪዎች እውነቱን ባፍረጠረጡበት ወቅት ነው፡፡ (ቻይና በገነባችው የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ያልተደፈረውን የደፈሩ ጀግና!) እስቲ ይታያችሁ ----- በህብረቱ አዳራሽ ማን ወንድ ነው፣ ሥልጣንን ርስታቸው ስላደረጉ መሪዎች ትንፍሽ የሚለው? (ጎመን በጤና አለ አበሻ!)
 ኦባማ ግን አድርገውታል! (አድናቂዎች ሲያንሷቸው ነው!) የኬንያ ወጣቶች “I love u Obama” ሲሉ ነው የሰነበቱት (ፌንት አለመስራታቸውም እነሱ ሆነው ነው!) በተረፈ ወጣቱ ሁሉ በኦባማ ንግግር መንፈሱ እንደተነቃቃ ---- ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ለነገሩ የእሳቸውም ንግግር የዋዛ አልነበረም፡፡ ፕሬዚዳንቱ ማሳቅም… መሸንቆጥም… ማነቃቃትም… ይችሉበታል፡፡ በአሜሪካ መድረክ አንድ ቦታ ተገትሮ መዝፈንና እንቅልፍ የሚያመጣ ንግግር ማድረግ ቅቡልነት የለውም፡፡ (ኦባማ ግን ተናገሩ ሳይሆን አቀነቀኑ ቢባል ነው የሚሻለው!)
ኦባማ፤“ኢትዮጵያ ባሳየችው የኢኮኖሚ ዕድገት ሚሊዮኖች ከድህነት ወጥተዋል” ብለው ሲናገሩ፣ አንድ ካፒታሊስት ዘመም ወዳጄ፣ምን አለ መሰላችሁ? “መሪዎቻችን ያላሳመኑንን ኦባማ ሊያሳምነን ነው እንዴ?!” (ከምርም አምኖ ነበር!) ነገሩ እንደዛ ከሆነ ---- ለምን ኦባማ   እየመጡ የእድገትና የልማት ንግግር አድርገው አይመለሱም። (#ባቄላ ቀረ ቢሉ---#)  
እስቲ ላፍታ ወደ ኦባማ አባት አገር - ጐራ ብለን እንመለስ፡፡ ኦባማ  በኬንያ ጉብኝታቸው ለአገራቸው ልጆች (ኬንያውያን) ራሳቸውን ሲገልጹ፤ “በስልጣን ላይ ያለሁ አፍሪካን የጐበኘሁ የመጀመሪያው ኬንያ - አሜሪካን ፕሬዚዳንት ነኝ” በማለት ቀልደዋል፡፡ (ለኬንያውያን ግን ኩራት ነው!)
በአሮጌ ቮልስዋገን አቀባበል የተደረገላቸው ኦባማ፤ ከሶስት አስርት ዓመታት በኋላ ወደ ኬንያ የተመለሱት የአሜሪካንን ዋይት ሃውስ ይዘው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ 60 ሊሞዚኖችን…ከ10 የማያንሱ አውሮፕላኖች ከእሳቸው ጋር ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በነገራችን ላይ The Beast የሚል ስያሜ የተሰጣት ካዲላክ ዋን (እንደ ኤርፎርስ ዋን ማለት ነው) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኦፊሴላዊ አውቶሞቢል ናት (የትም ቢሄዱ ትከተላቸዋለች!)
ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቅንጦትና ደህንነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ (ደህንነትን ያማከለ ቅንጦት ሊባል ይችላል!) እናላችሁ---የካዲላክ ዋን መስኮት ከ5-6 ኢንች ውፍረት ያለው ሲሆን Bomb proof ነው (ቦንብ የማይበሳው እንደማለት!) ብረት የሚበሱ ጥይቶችንም የመቋቋም አቅም አለው ተብሏል፡፡ በሩ ደግሞ 8 ኢንች ውፍረት ባለው ብረት ተለብጧል (ከፕሬዚዳንት ቡሽ ሊሞዚን በሮች በ3 ኢንች ይወፍራል!) የበሮቹ ክብደት ከቦይንግ 757 የጋቢና በር እኩል ነው፡፡ (ይሄ ሁሉ ታዲያ ለሴፍቲ ነው!)
ባራክ ኦባማ፤ የኬንያው ፕሬዚዳንት ባደረጉት የእራት ግብዣ ላይ እንዲህ ብለው ቀለዱ አሉ፤ “አገር ቤት ያሉ ተቀናቃኞቼ፤ ወደ ኬንያ የመጣሁት የትውልድ ሰርተፊኬቴን ለመፈለግ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ነገሩ ግን እንደዚያ አይደለም” (ኦባማ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ተቀናቃኞቻቸው፣#የአሜሪካ ዜጋ አይደለም; በሚል ዘመቻ ከፍተውባቸው እንደነበር ይታወሳል!)  
ከዚህ በላይ የኬንያን ወሬ ከቀጠልኩ ኢቢሲን ሆኜ አርፈዋለሁ፡፡ ትዝ ይላችኋል … ኦባማ ኬንያ ሊገቡ አንድ ወይም ሁለት ቀናት ሲቀራቸው፣ ጉብኝታቸውን የተመለከተ ዘገባ በEBC ቀርቦ ነበር (ሮይተርስ በEBC መስኮት በሉት!) የዜናው ርዕስ “ኬንያና ኢትዮጵያ የኦባማን ጉብኝት በጉጉት እየተጠባበቁ ነው” የሚል ይመስለኛል (ቃል በቃል አልወጣኝም!)  ከዚያስ? ኢቢሲ ነፍሴ-- ሮይተርስ ኬንያዊ የኢኮኖሚ ባለሙያና ነዋሪዎችን አነጋግሮ ያጠናቀረውን ዘገባ እንዳለ ለቀቀብን (ኬንያ ኢትዮጵያን የጠቀለለቻት ይመስል ነበር!)
እናላችሁ … ኬንያውያን የኦባማ መምጣት የፈጠረባቸውን ሃሴት ሲናገሩ ሰማን፡፡ ምሁሩም ጉብኝቱን ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው አንፃር ተነተኑት። በዚያው የEBC ዘገባ ተቋጨ፡፡ (#አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች; እንኳን አልተጠየቁም!) ከምሬ ነው የምላችሁ----የዚያን ዕለት ምሽት ኢቢሲን ብቻ ሳይሆን ኬንያዎችንም ታዘብኳቸው፡፡ እንዴት መሃል ላይ እንኳን ስለ እኛ አያወሩም? (“አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” እንዳትሉኝ!)
አሁን ወደ ኢትዮጵያ ገብተናል፡፡ የታላቂቷ አገር አሜሪካ መሪ የሆኑት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ምን ቁም ነገር ሰርተው ሄዱ? በኬንያ ከሲቪል ማህበረሰቡና ከወጣቶች ጋር በግንባር አውርተዋል፡፡ መክረዋል፡፡ አቅጣጫ አመላክተዋል። በጦቢያስ? ተቃዋሚዎች እንደሚሉት፤ በሰብአዊ መብት አያያዝ፣በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣በምርጫ፣በፖለቲካ ምህዳር--ወዘተ  ምንም የፈየዱት ነገር የለም፡፡ ተቃዋሚዎችን ይበልጥ ያበገናቸው ደግሞ ገዢውን ፓርቲ “በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት” ማለታቸው ነው፡፡
ኦባማን በዚህ ንግግራቸው ያልተቻቸው የለም። ከአገር ውስጥ ተቃዋሚዎች እስከ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ድረስ እስኪበቃቸው አብጠልጥለዋቸዋል፡፡ አንድ ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የኦባማን አባባል፤ “አስደንጋጭ” ሲል ነው የገለጸው፡፡  
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ዋና ፀሐፊ አቶ በቀለ ነጋ ለሮይተርስ በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ “ዲሞክራሲ ማለት የሰዎችን ድምፅና የምርጫ ውጤታቸውን መዝረፍ ከሆነ አላውቅም? ሰዎችን ገድለዋል፤ በተደራጀ ማጭበርበር የድምፅ ኮሮጆውን ወስደውታል”
“ይሄንን በአሜሪካ ወይም በእንግሊዝ ያሉ ህዝቦች ይታገሱት እንደሆነ አላውቅም፡፡ በአሜሪካ ይሄ ነው የዲሞክራሲ ትርጉም? በጣም እናዝናለን፡፡ ኦባማ በምርጫችን ላይ የሰጡት አስተያት ለአምባገነኖች ድጋፍ የሚሰጥ ነው” ሲሉ ክፉኛ ተችተዋል - ዋና ጸሃፊው፡፡  
በእርግጥ ኦባማም ዝም ዝም አላሉም (ተቃዋሚዎች እንደጠበቁት አልሆነላቸው ይሆናል እንጂ!) ኢትዮጵያ በፕሬስና በፖለቲካ ነፃነት ላይ መሻሻል እንድታደርግ ለመንግስት ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ ነፃነትን በማሻሻል፣ ተቃዋሚዎችና ጋዜጠኞች በነፃነት የሚንቀሳቀሱበትን ምህዳር እንዲከፍት ጠይቀዋል፡፡
 ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያምስ ምን አሉ? “የሰብአዊ መብት አያያዝንና መልካም አስተዳደርን ለማሻሻል ቁርጠኛ ነን፤ ለዲሞክራሲ ያለን ቁርጠኝነት የይስሙላ ሳይሆን የምር ነው” ብለዋል፡፡
ኦባማ ከፍተኛ አድናቆትና ተደጋጋሚ ጭብጨባ በተንበሸበሹበት የአፍሪካ ህብረት ማንዴላ አዳራሽ ውስጥ ባደረጉት ንግግር፤ለረዥም ዘመን ሥልጣንን እንደርስት የያዙ የአፍሪካ መሪዎችን (እነ ሙሴቪኒ፣ ሙጋቤ፣ወዘተ) ያለ ሃዘኔታ በትችት ደቁሰዋቸዋል! (ያውም ራሳቸውን በምሳሌነት እየጠቀሱ!)
“እኔ ለሶስተኛ ዙር ብወዳደር አሸንፋለሁ” ያሉት ኦባማ፤ “ነገር ግን ህጉ አይፈቅድልኝም፤ ማንም ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም” ብለዋል፡፡ ማንም የዕድሜ ልክ ፕሬዚዳንት መሆን የለበትም ሲሉም አሳስበዋል -- ኦባማ፡፡ ይሄኔ እነ ሙጋቤ ምን የሚሉ ይመስላችኋል ? “አሜሪካ ሆኖበት ነው እንጂ እሱም ህገመንግስት ደልዞ ሥልጣኑን ማራዘም ጠልቶ አይደለም … ሌላ ነገር ከሚያወራ ለምን ምክር አይጠይቀንም!”
(የሥልጣን ዘመን ማስረዘምያ ምክር እኮ ነው!)
እንግዲህ ኦባማ ለኬንያም ሆነ ለኢትዮጵያ (የወደፊት ግስጋሴ) ይበጃል ያሉትን መድሃኒት አዘው ሄደዋል፡፡ (መሪዎቻችን የተሳሳተ መድሃኒት እንዳይሰጡን መፀለይ ነው!) ዋናው ችግር  ግን ምን መሰላችሁ? አወሳሰዱን ሳይነግሩን ነው የሄዱት (በኢሜይል ይጠየቁ!!)

  

Read 4873 times