Saturday, 01 August 2015 14:28

ሁለት ፍቅሮች የሰሩት ሁለት ከተማ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(3 votes)

   “When there is ego I go” ትላለች አንዲት ገፀ - ባህርይ፤ ስያሜያቸውን ለማስታወስ ከሚያዳግቱኝ ብዙ የአሜሪካ ስሪት ፊልሞች በአንዱ ላይ፡፡ ከዚህች አረፍተ ነገር ውጭ ሌላው የፊልሙ ጭብጥ ትዝ እንዲለኝ ስለማልሻ ትዝ አላለኝም፡፡
“ego” የሚለውን ቃል በአማርኛ ተመጣጣኝ ፍቺ አላገኘሁለትም፡፡ ምናልባትም የቃሉ ተጨባጭ መገለጫ ለሀይማኖታዊና ሀሪሶታዊዋ ሀገራችን፣ ባይተዋር ሆኖ በመቆየቱ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ነገር ግን በየትኛውም ዘመን ሆነ በየትኛውም ስልጣኔ ወይንም ኋላቀርነት ውስጥ የሀሳቡ መለኪያ አለ፡፡ ego ባይኖር ወይንም ቢድበሰበስ ተቃራኒው ግን መኖሩ አይቀርም፡፡
የego ተቃራኒ ይኖራል፡፡ “ኢጐ” የሚለውን ቃል “እኔነኛዊነት” በሚለው ግዜያዊ ስም ብጠራው የሚቃወመኝ የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ቢኖርም የራሱን “እኔነኛዊነት” ከእኔ ጋር ለማፎካከር ሲል እንደተቃወመኝ ቆጥሬ እዘልለዋለሁ፡፡ “እኔነኛዊነት” የተፈጥሮ ፀጋ ነው እንዳልል…ሌላ ተቃራኒ የሰው መገለጫም መኖሩ ስለሚታወሰኝ አልደፍርም። እኔነኛዊነት ሰው ሁሉን ነገር በድፍረት እንዲመረምር፣ መርምሮም እንዲያውቅ፣ አውቆም ያወቀውን ነገር ለራሱ ጥቅም እንዲገለገልበት የሚያነቃው የተፈጥሮ ማንነቱ ነው፡፡
ከአራት አመት በታች የሆኑ ህፃናትን ብናስተውል፣ “እኔነኛዊነት” ከውልደት ጀምሮ በሰው ላይ ያለ ነገር መሆኑን ያስገነዝቡናል፡፡ ሁለት ህፃናት በአንድ መጫወቻ እኩል እየተዋዋሱ ሲጠቀሙ አታዩም፡፡ ጉልበት ያለው የሌለውን ወይንም የሌላትን ነጥቆ መጫወቻውን የግሉ ያደርገዋል። ነጣቂውም በመንጠቁ አይፀፀትም፤ ተነጣቂዋም በማጣቷ ተስማምታ አሜን አትልም። አምርራ ታለቅሳለች፡፡ ለቅሶዋን ነጣቂው አይሰማትም፡፡ ይህም የእኔኛዊነት መገለጫ ነው፡፡
ይህ ባህርይ ህፃናቱ ከወላጆቻቸው የቀመሱት አይደለም፡፡ በተፈጥሮ ነው “እኔነኛዊ” የሆኑት። እርግጥ በዚህ ብቻ ማጠቃለልም ይከብዳል። ሁለት መጫወቻ ያለው ህፃን፣ አንዱን ለሌላዋ ህፃን ሲሰጥም እንታዘባለን፡፡ ሁሉንም ነገር የራሱ በማድረግ ብቻም አይረካም፡፡ ደስታውን ከጠገበው በኋላ የሚጋራለትም ይሻል፡፡
እንግዲህ እነዚህ ናቸው ሁለቱ የሰው ልጅ የተፈጥሮ/የህይወት አንቀሳቃሽ ሃይሎች፡፡ ሁሉንም መንጠቅ በአንድ ጽንፍ፣ ሁሉንም አሳልፎ መስጠት በሌላ ፅንፍ፤ በመሀል ቤት ተምታተው ስለሚገኙት ቅይጦች ዛሬ ላስባቸው አልደፍርም፡፡ ግን፤ የሰው ልጅን መከራ እና ግራ መጋባት ያናሩት መሀል ቤተኞቹ ናቸው፡፡ ገላጋይ መስለው አጥቂዎቹ… አጥቂ መስለው አቃፊዎቹ፡፡
ይሄ ከላይ የፃፍኩት የሀሳቤ መነሻዎች እና ማጠንጠኛዎች ቢሆኑም በምንም ረገድ ግን የድምዳሜ ማጠናቀቂያዬ አይደሉም፡፡
ለማሰላሰል እንዲያግዘን በM.C Darcy የተፃፈውን “The Mind and the Heart of Love” የተባለውን መጽሐፍ እመረኮዛለሁኝ፡፡
በሰው ልብ እና ጭንቅላት መሀል ያለውን ርቀት “በእኔኛዊነት” “ego” እና በአብሮ “እኛዊነት” መሀል እንዳለው ልዩነት መስሎ ያቀርበዋል፡፡ እኔነኛዊነትን በተለያየ ደረጃ ቢገልፀውም ሲጠቃለል ፍቅር ነው ይለዋል፡፡ ግን የፍቅሩ አይነት አንድ ግለሰብ ያፈቀረውን ነገር የራሱ አድርጐ በቁጥጥሩ ስር በማዋል ብቻ እርካታውን የሚያገኝ ስለመሆኑ በብዙ ምሳሌ ያሳየናል፡፡
የራስ የሚደረገው ነገር እውቀት ሊሆን ይችላል፣ ሀብት ሊሆን ይችላል…ወይንም ስልጣን ወይንም የፆታ ስሜት ያረፈባት እንስት ወዘተ፡፡ ግን መሰረታዊው ነገር ያለው የተፈለገውን ነገር የራስ በማድረግ ላይ ነው፡፡
ይኼንን የእኔነኛዊነት ሃይል ምንጭ የሆነውን የፍቅር አይነት “Eros” ሲል ይጠራዋል። ኤሮስ፤ የግሪካዊያኖቹ የፍቅር አማልክት ነው።
ግሪካዊያኖቹ በፀሐያማው የንቃት ህልውና ጊዜያቸው ምክንያታዊነትን እና የሳይንስ መሰረቶችን “እውቀት” ብለው የተፈላሰፉና ግኝቶቻቸውን ለአለም በስፋት ያስደመጡ መሆናቸው ይታወሳል። ከመታወስም ባለፈ የምእራባዊያኖቹ mind set/mind style በዚሁ አንፃር የተቀረፀ መሆኑም አይዘነጋም፡፡
ሶቅራጥስ የፍቅርን መሰረታዊ ፍልስፍና ከጓዶቹ ጋር ሆኖ የመረመረበት ስራ በፕሌቶ ድርሰት የሰፈረበት መፅሐፍ “ሲምፖዚየም” ተብሎ ይጠራል። በአንድ አጋጣሚ ሀገራዊ የግጥም ሽልማት ያሸነፈ ጓደኛቸውን ደስታ ለመጋራት በተሰበሰቡበት የመጠጥ ግብዣ ላይ ሶቅራጥስ ተገኝቶ ነው የመፅሐፉ ዳራ የተወጠነው፡፡
በዚሁ ግብዣ ላይ ስለ ፍቅር ምንነት ጥያቄ እና መልስ ይደረጋል፡፡ አጋቶን (Agaton) የተባለው አባል የሚከተለውን ስለ አርዕስቱ ይላል፡-
“Love is always of something that we have not; we love the beautiful when we lack it and wish to enjoy it. Therefore love is not a god at all but a mean between fair and foul love is the son of plenty and want. Want plotted to here a child by plenty and succeeded”
እንግዲህ በዚህ አባባሉ ፍቅር፣ ፍላጎትን እና እርካታን የሚያገናኝ መልዕክተኛ ነው ይለናል፡፡ እርካታ ስኬት ነው፡፡ የሚሳካው ደግሞ “እኔነኛዊነት” የተመኘውን ነገር የራሱ አድርጐ የልቡን ሲያደርስ ነው፡፡ ስለዚህ ፍቅር በግሪካዊያኑ ከእኔኛዊነት ጋር በአንድ መስመር የተገናኘ ነው፡፡ የግለሰብን ፍላጎት (will) ከፈለገው ነገር ጋር ማጨባበጫ የተግባር ሃይል ነው፡፡
በህፃንነት ነፍስ ሳያውቅ መጫወቻውን በመንጠቅ የገለፀው የራስ ወዳድ ባህርይ ከፍ ሲል ይቀይራል ወይ ነው ጥያቄው? እንደ M.C Darcy መፅሐፍ አይቀይርም፡፡ እንዲያውም እውቀቱን እና የእድሜ ተሞክሮውን ወይንም ብስለቱን በህፃንነት ላሳየው ተፈጥሮ ባህርይ አጋዥ ግብአት ያደርገዋል። ምክንያታዊ በመሰለ፣ ሳይንሳዊ በሆነ ደርዝ የተላበሰ እርጋታ ግለሰባዊ እኔነኛዊነቱን ያካሂድበታል፡፡
“… but the force which shows itself in the animal nature as aggressive and brutal turns in a human person into a rule of reason, the mastering faculty that directs its animal to its own end and perfection”
ይህንን አይነቱን የእኔነኛዊነት ተላላኪ የሆነውን ፍቅር ፕሌቶ በሲምፖዚየም መፅሐፉ እውነተኛው የፍቅር አይነት “The philosophers love” ሲል ያቆለጳጵሰዋል፡፡ ከእኔነኛዊነት በተቃራኒ ያለውን ፅንፍ… በአጭር ቃል ግለፀው ካላችሁኝ “ego” የተባለውን ነገር ማስወገድ ነው። እኔነኛዊነትን ማስወገድ በአጭሩ የክርስቶስን ትምህርቶች ተግባራዊ ማድረግ፣ መንፈሳዊነት ማለት ነው፡፡
የክርስቶስ ትምህርት … በአንድ አረፍተ ነገር በአንድ እግርህ ቆመህ ተናገር የተባለው … የተባለው የካቶሊክ ጳጳስ እንደተጠየቀ ቆሞ፣ “thoushlat Love your neighbor as thyself” ብሎ መናገሩን በሚል ዱራንት (የፍልስፍና ታሪክ) በተባለው መፅሐፍ ላይ ተገልጿል፡፡ ቄሱ በአንድ አረፍተ ነገር የገለፀውን መርሆ ለማስረዳት ፈላስፋው ሄግል በአስር ጥራዝ ሄዶበታል፡፡
ባልንጀራህ መውደድ (empathy)… ራስን ብቻ ከመውደድ ወይንም ከእኔነኛዊነት ጎራ ባሻገር ያለው የሰው የሌላኛው ፅንፍ ባህርይ ነው። ክርስቶስም ከመምጣቱ በፊት በተፈጥሯችን ላይ እንዳለ ማረጋገጥ ከፈለግን … ምንም እውቀትም ሆነ የሀይማኖት አስተምሮ የሌላቸው በጨቅላ ደረጃ ያሉ ህፃናት ምግብ ሲጎራረሱ … አንዱ ባለቀሰው ሌላው ተከትሎ ሲያለቅስ ልብ ብለን የተፈጥሮአችን ገፅታ ስለመሆኑ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ እንደ እኔነኛዊነት … ባልንጀራዊነትም (ይሄም ለእኔ እንዲመች ያመጣሁት ቅፅል) በሰው ልጆች ማንነት ውስጥ ያለ ነው፡፡
እንግዲህ ዓለም በእዚህ ሁለት የፍቅር አይነቶች የተገነባች ከተማ ናት፡፡ (አለም የሰው ልጆች ህይወት ነው ዋና ትርጉሟ እንዳልል… ይሄም ዘርን መሰረት ያደረገ እኔነኛዊነት መሆኑ ያሰጋኛል)
ቅዱስ አጎስጢኖስ፤የባልንጀራዊነትን ወይንም የሃይማኖታዊ ፍልስፍናን መሰረት ከጣሉት አይነኬዎች መሀል አንዱ ነው፡፡  እንደሚከተለው ይናገራል፡-
“Two loves made two cities, the earthly which is built up by the love of the self to the contempt of GoD, and the heavenly which is built by the love of GoD to the contempt of the self” በዚህ አነጋገሩ ውስጥ እስካሁን ያልኩት ነገር ተጨምቆ ይገኛል፡፡
“ሁለት ፍቅሮች ሁለት ከተማዎችን ገነቡ፤ አንደኛው ከተማ ለራስ እና ለምድራዊ ፍቅር፣  ለፈጣሪ ጥላቻ የተቀለሰ ሲሆን፤ ሁለተኛው ከተማ ደግሞ ለፈጣሪ ፍቅር፣ ለምድራዊ/ለራስ ጥላቻ የቆመ ነው” ማለቱ ነው፡፡
“የራስ ጥላቻ” ሲል ለእኔ የሚገባኝ፤ የራስ ማንነታችን ዘጠና ፐርሰንት ከተሰራበት የ “እኔነኛዊነት” ለማምለጥ የሚደረግ የጥላቻ አይነት መሆኑ ነው፡፡ ለፈጣሪ ፍቅር ደግሞ ሲል ከእኔነኛውነት ማዕበል ያመለጠችዋ፣ ባልንጀራን በራስ ውስጥ የማታካትተዋ (አስር ፐርሰንት ብትሆንም) ፍቅር መሆኑን አውቃለሁ፡፡ የፈጣሪ ፍቅር፤ በምድራዊ፣ ተጨባጩ እውነታ ላይ ሊገለጽ ወይንም ሊመነዘር የሚችለው ሰው እርስበራሱ መዋደድ ወይንም መተዛዘን ከቻለ ብቻ ነው፡፡
ሰው ከገነት ተባርሮ ምድር ሲመጣ ፀጋውን ሁሉ ተገፎ ነው፡፡ ፀጋ ከመገፈፍ ጋር አውሬነቱ ጐልቷል፤ (ego) እኔነኛዊነት የዚህ ባህሪይው መገለጫ ነው። ግን በተቃራኒው አንድ ከገነት ሲገፈተር አብሮት የወደቀ የቀድሞው ማንነቱ ጭላንጭልም ወደ ወደቀበት ምድር አብሮት መጥቷል፡፡ ይህ የመጣው ነገር ነፍስ ባላወቁትም ጨቅላዎች ላይ የሚታየው የመተዛዘን መንፈስ ነው፡፡ አዳም ረታ ይሄንን ገፀ በረከት “በለስ” በተባለው አጭር ልብወለዱ ላይ ፍንትው አድርጐ ተቀኝቶታል፡፡
እንግዲህ አለም አሁን ባለንበት ጊዜ ወደ የትኛው ሚዛን አጋድላ እንደምትገኝ ግልጽ ነው። አለም ለነገሩ ሁሌም ዘንድሮ እንደሆነችው ናት። እኔነኛዊነት ነው የሚሾፍራት፡፡ የፈለገ ያህል ቢሾፍራትም ከመንፈሳዊነት ፈጽሞ ነጣጥሎ ወደተመኘው የራስ ወዳድ የፍላጐቱ ጥግ አላደረሳትም፡፡

Read 3221 times