Saturday, 01 August 2015 14:23

የጨው ገደል ሲናድ፣ ብልጥ ያለቅሳል ሞኝ ይልሳል

Written by 
Rate this item
(19 votes)

  ከህንድ ጦርነቶች በአንዱ እንዲህ ሆነ አሉ፡፡
የፈረሰኛው ብርጌድ የወራሪዎቹን ጐሣ ድባቅ መታና ደመሰሰ፡፡ የተረፈው የጐሣው መሪ ብቻ ነበር፡፡
የፈረሰኛው ብርጌድ አለቃ ለተረፈው መሪ እንዲህ አለው፡-
“እጅግ አድርገህ በጀግንነት ስለተዋጋህ ነብስህን አተርፍልሃለሁ - አልገድልህም!”
ያም የወራሪዎቹ ጐሣ መሪ፤ ስለተደረገለት ምህረት ምሥጋና ለማቅረብ ቃላት ሲፈልግ ሳለ፣ ከተራራው አናት መዓት የህንድ መንጋ መጥቶ የፈረሰኛውን ብርጌድ ይደመስሰዋል። የተረፈ አንድ ሰው ቢኖር የብርጌዱ አለቃ ብቻ ነው፡፡ አሁን እንግዲህ ቦታ ተለዋወጡ - የብርጌዱ አለቃና የወራሪዎቹ መሪ፡፡
የወራሪዎቹ መሪ ለተረፈው የብርጌዱ አለቃ በፈንታው እንዲህ አለው፡-
“እኔ እንዳንተ ደግ አልሆንልህም፡፡ ሞት አይቀርልህም፡፡ ግን ሦስት ምኞት እንድትናገር እድል እሰጥሃለሁ”
የብርጌዱ አለቃም፤
“የመጀመሪያ ምኞቴ፤ ፈረሴን ለማየት እንድትፈቅድልኝ ነው” አለ፡፡ ተፈቀደለትና ፈረሱ መጣለት፡፡ ከዚያም የብርጌዱ አለቃ ለፈረሱ የሆነ ነገር በጆሮው ሹክ አለው፡፡ ፈረሱ ፈረጠጠ፡፡
ይሄኔ የብርጌዱ አለቃ፤ “ትንሽ እንጠብቀው” አለ፡፡
ተፈቀደለት፡፡
ዕውነትም ፈረሱ ከአንድ ሰዓት በኋላ ተመለሰ፡፡ አንዲት በጣም ውብ የሆነች ልጃገረድ ይዞ ነው የመጣው፡፡
የብርጌዱ አለቃ ለጐሣው መሪ፤
“ይቺን ልጀገረድ ሰጥቼሃለሁ” አለው፡፡
የወራሪዎቹ መሪ ልጃገረዲቱን ወስዶ ፍቅሩን ገልጦላት ተመለሰና፡-
“ሁለተኛው ምኞትህ ምንድን ነው?” አለው፡፡
የብርጌዱ አለቃም፤
“ፈረሴ ይምጣልኝ” አለ፡፡
ተፈቀደለትና ፈረሱ መጣለት፡፡
አሁንም በጆሮው የሆነ ነገር ሹክ አለው፤ ፈረሱ ጋለበ፡፡
“ትንሽ እንጠብቀው” አለ አለቃ፡፡
ፈረሱ ከአንድ ሰዓት በኋላ ሌላ ምን የመሰለች ቆንጆ ልጅ ይዞ መጣ፡፡
አለቃም ለጐሣው መሪ፤
“ይቺንም ልጅ መርቄ ሰጥቼሃለሁ” አለው፡፡
የወራሪዎቹ ጐሣ መሪ ልጅቱን ወሰደ፡፡ ሲዝናና ቆይቶ ተመለሰና፤
“ሦስተኛው ምኞትህስ ምንድን ነው?” አለው፡፡
“ፈረሴን እንዳገኘው ይፈቀድልኝ”
ተፈቀደለትና ፈረሱ መጣ፡፡
የብርጌዱ አለቃ ፈረሱ ላይ ወጣ፡፡ እርካቡን ኮለኮለና መጭ አለ፡፡ ማን ያስቁመው? ለዐይን ተሰወረ!
*                  *                     *
ከጉልበተኝነት ብልህነት ይበልጣል፡፡ ደግ ላደረጉልን ክፉ መመለስ መበለጥ እንጂ መሻል አይደለም፡፡ ምኞቶቻችን ተጨባጭ ይሁኑ፡፡ ተጨባጭ ቢሉም ለሀገርና ለህዝብ ፋይዳ ያላቸው ማለት ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ምድራዊ ገነት ብትሆንልን ማንም የሚጠላ የለም፡፡ ሆኖም ምኞታችን አቅማችንን ያገናዘበ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በብዙ ጉዳዮች ከልኩ በላይ መወጣጠር (Over - stretched እንዲል) መሰነጣጠቅም ሆነ መሰባበርን ማስከተሉን እንገነዘባለንና፡፡
“ሲያርስ ነካክቶ፣ ሲዘራ አፈናጥሮ፣ ጥፋተኛ እኔን አድርጎ” የሚባል ተረት አለ፡፡ በቅጥ - በቅጡ ያልሰሩት ሥራ፣ በአግባቡ ያላዘጋጁት ነገር፤ በኋላ ሰበባችንን በሌሎች ላይ እንድንላክክ ያደርገናል ማለት ነው፡፡ ሁሉንም መነካካትም አንዱን ሳናበስል እንድንቀር ያደርገናል፡፡ የጎረቤቶቻችንን አያያዝ በተመለከተ አንድም በዲፕሎማሲ መስክ፣ አንድም ሉዓላዊነትን በማስከበር ረገድ፤ አሳምረን መጓዝ ያስፈልገናል፡፡ የኃያላን መንግሥታትን ድጋፍ የማይሻ አንድም የሶስተኛው ዓለም አገር ባይኖርም፤ “በራቸውን ከፍተው እየተኙ፣ ሌባ ሌባ ይላሉ” የሚለውን አባባል ማስተዋል ወቅታዊ ነው፡፡ በሌላ ወገንም ድጋፍን ከልኩ በላይ አጋኖ ማሰብ፤ “አንገቷን ደግፈው ቢያስጨፍሯት፤ ያለች መሰላት” የተባለውን መዘዝ ያመጣል፡፡
ፈረንጆቹ There is no free lunch የሚሉት (ምንም ነገር በነፃ አይገኝም እንደማለት) የዋዛ ነገር አይደለም፡፡ የሚያስከፍለን ነገር መኖሩ ገሀድ ነው፡፡ ግን ቅናሹን ዋጋ ማስተዋል አለብን፡፡ ሁሉን በሚዛን መጫወት ከአጓጉል ቡጢ ያድናል፡፡ እኛን ከሌላ አፍሪካ አገራት ምን ይለየናል? ልዩ የሚያደርገን የኢኮኖሚ ጥሪት አለን ወይ? የፖለቲካ መረጋጋታችን አስተማማኝ ነወይ? እዚያው ሞላ እዚያው ፈላ (Volatile) የሆነው የምሥራቅ አፍሪካ አባዜ ምን ያህል አይመለከተንም? “ሠርጌን አሙቅልኝ” የሚባለው ዓይነት የፖለቲካ ዘፋኝ፤ ጠንቋይ፣ ከዶክተር አይለይም በሚልባት አፍሪካ፣ የተሟሟቀ ልማት አለኝ ማለት ይቻላልን? የአፍሪካ የመከላከያ ኃይል ምን ያህል የአፍሪካ ህብረት ታዛዥ ይሆናል? የድንበረተኛ አገሮች ፍቅርስ ወረት ነው ዘላቂ? ራሳቸውን ያላረጋጉ አገሮች እንደ አሜባ የከበቧት አገራችን፤ እንዳትዋጥ እንዳትሰለቀጥ መጠንቀቋ ዋና ጉዳይ ሆኖ ለሌሎች መጠቀሚያና ማነጣጠሪያ እንዳትሆን፣ መሬት የያዘ ዕሳቤ አላትን? ብሎ መጠየቅ ያባት  ነው ! ዙሪያችን ያሉትን ሁሉ በነቃ ዐይን፣ በዐይነ - ቁራኛ መመልከት፤ ያለ፣ የነበረ ወደፊትም የሚኖር፣ መላ ነው፡፡ አለበለዚያ፤ “የጨው ገደል ሲናድ፤ ብልጥ ያለቅሳል፣ ሞኝ ይልሳል” ይሆንብናል፡፡  

Read 6977 times