Saturday, 01 August 2015 14:20

ዶ/ር መቅደስ መስፍን ወልደማሪያም ማን ናት? (የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ልጅ)

Written by 
Rate this item
(16 votes)

       ከአዘጋጁ፡-
በአውስትራሊያ የሚታተም “አሻራ” የተሰኘ መጽሔት በቁጥር 2 ዕትሙ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያምን በተለያዩ ጽሑፎች ዘክሯል፡፡ እኛ ግን ለዛሬ ልጃቸው ዶ/ር መቅደስ መስፍን ወልደማሪያም ከመጽሔቱ ጋር ያደረገችውን ቃለምልልስ መርጠን ከመለስተኛ የአርትኦት ሥራ በኋላ ለአንባቢያን አቅርበነዋል፡፡

         ዶ/ር መቅደስ መስፍን ወልደማሪያም ማን ናት?
               (የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ልጅ)

   ራስሽን ለአንባቢ በማስተዋወቅ ውይይታችንን ብትጀምሪልን?
ስሜ መቅደስ መስፍን ይባላል፡፡ የፕሮፌሰር መስፍን የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡ የምኖረውም አሜሪካን አገር ማሳቹቴስ ግዛት ነው፡፡ ወደ አሜሪካ ከመጣሁ ከ20 ዓመት በላይ ሆኖኛል፡፡
በኢትዮጵያ እያለሁ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት በናዝሬት ትምህርት ቤት ሲሆን በከፍተኛ ትምህርት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ፋክሊቲ ምሩቅ ነኝ፡፡ አሜሪካን ሃገር ከመጣሁ በኋላም በቦስተን ዩኒቨርሲቲ በ Public Health የማስተርስ ዲግሪ አግኝቻለሁ፡፡ በዚሁ ሙያ ከኢሚግራንቱ ጋር በተገናኘና በኤችአይቪ መከላከል (HIV Prevention) ለረዥም ጊዜ ሥሰራ ቆይቻለሁ። አሁን ደግሞ በግል አንዳንድ ስራ ለመጀመር እየተዘጋጀሁ ነው፡፡
በቅርቡ በአንድ አጋጣሚ “Eforall 2015 Finalists” በሚል ከተዘረዘሩት 18 ሰዎች ውስጥ ስምሽን አይቻለሁ። ለመሆኑ ይህ Eforall የተሰኘው ድርጅት ምን እየሰራ ያለ ድርጅት ነው? ያንቺ ስም በFinalist ዝርዝር ውስጥ የሰፈረው ምን ሰርተሸ ነው?
(Entrepreneurship for all) ወይም በአጭሩ (Eforall) የተሰኘው ድርጅት አነስተኛ የቢዝነስ ሃሳቦችን የሚያበረታታ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ነው፡፡ ይህ ተቋም ሰዎች በራሳቸው ተነሳሽነት የቢዝነስ ሃሳብ አፍልቀው ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያደርጉትን ጥረት የሚያበረታታ ድርጅት ነው። አሰራሩም በመጀመሪያ ወደ ተግባር የሚለወጥ ቢዝነስ ሃሳብ አለን የሚሉ ሰዎችን ሃሳባቸውን ዘርዝረው በማመልከቻ መልክ ያቀርባሉ፡፡ ድርጅቱም የቀረቡለትን ማመልከቻዎች በተለያዩ መመዘኛዎች አወዳድሮ የበለጠ አሳማኝ ሆነው ያገኛቸውን ተቀብሎ ዕቅዳቸውን ወደ ተግባር የሚለውጡበትን መንገድ በተለያየ መልክ ያግዛል። እኔም እንዲሁ አንድ ያሰብኩትን ነገር ለመሞከር ጥናት እያደረኩ ባለሁበት ወቅት ነበር ድንገት ከዚህ ድርጅት የተደወለልኝ። ከዚህ በፊት ስለዚህ ድርጅት ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ደውለው “እያደረግሽ ያለውን ሙከራ እያየን ነው። እኛ እንዲህ ዓይነቱን በግል ተነሳሽነት የሚደረጉ ጥረቶችን የምናበረታታ መንግስታዊ ያልሆንን ድርጅት ነን፡፡” ብለው ራሳቸውን ካስተዋወቁኝ በኋላ፤ ለምን ሃሳብሽን በዝርዝር ገልጸሽ ማመልከቻ አታስገቢም? በርግጥ ያመለከተ ሁሉ ላንቀበል እንችላለን፡፡ ውድድሩ ጠንካራ ነው፡፡ ግን መሞከርሽ አይከፋም” ብለው ምክር ሰጡኝ። እኔም ሃሳባቸውን ተቀብዬ እንደተባልኩት አደረግኩ። በኋላም ከ80 ያህል አመልካቾች መካከል አስራ ስምንታችንን ብቻ ተቀበሉን፡፡ እንዳሉትም ውድድሩ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ማመልከቻ አስገብቶ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በየግዜው እየጠሩ ሃሳብክን በባለሙያ ፊት እንድታስረዳ ያደርጉሃል። ለሚቀርብልህ ጥያቄ ሁሉ አሳማኝ መልስ መስጠት አለብህ፡፡ ምክንያቱም እነሱን ካላሳመንክ ሌላውንም ማሳመን አትችልም ከሚል እምነት ነው፡፡ ትክክልም ይመስለኛል። አንዴ ከተቀበሉ ግን ራስህን ችለህ እስክትቆም ድረስ በሁሉም መልክ ያግዙሃል ይረዱሃል፡፡ ብዙ ልፋት ያለው ነገር ነበር። ሆኖም ግን ከ18 ተመራጮች መካከል ሆኜ ቀጣዩን ማለትም ወደ ተግባር የሚገባበትን ጎዳና ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነኝ፡፡ Eforall 2015 Finalists ስም ዝርዝር ውስጥ ስሜ የተጠቀሰው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ከመነሻዬ በደፈናው በግል አንዳንድ ስራ ለመጀመር እየተዘጋጀሁ ነው ያልኩትም ይህንኑ ነበር፡፡
ወደ ፕ/ር መስፍን እንመለስ፤ ፕሮፌሰርን እንደ አባት እንዴት ትገልጫቸዋለሽ? አሁን ላለሽ ማንነት የሳቸው አስተዋፅኦ ምን ያህል ነው? ፕሮፌሰር በትምህርት ላይ ባላቸው ጠንካራ አቋም ይታወቃሉና በዚህ ረገድ በልጅነት ዘመን በጥሩም በመጥፎም የተከሰተ ትዝታም ካለ?
እንዳልከው በትምህርት ላይ ያለው አቋም ጠንካራ ነው፡፡ ያም ሊሆን ይችላል እኛም ብዙ አላስቸገርንም። የሚፈለገውን ውጤት ስለምናመጣ ብዙም በቁጣም ሆነ ውጤት ከማጣት ጋር በተያያዘ የማስታውሰው ነገር የለም፡፡ ከሱ ይልቅ ትዝ የሚለኝ በሃይስኩል እያለን የነበረበት የስራ ውጥረት ነው፡፡ ከስራ ወጥቶ ትምህርት ቤት መጥቶ ነው ወደ ቤት የሚወስደን፤ አንዳንዴ ግን ስለሚቆይብን ብቻችንን ትምህርት ቤት ውስጥ የመቆየት ነገር ነበር (ሳቅ)፡፡
ሌላስ እንደ አባት የሚገለጽ ባህሪ የላቸውም? ቁጡ! የሚፈሩ?
ብዙ ጊዜ ጓደኞቹ አባቴ ይቆጣል! አባቴን እፈራዋለሁ … ሲሉ ይገርመኝ ነበር፡፡ እኛ ጋ እንደዚህ አይነት ነገር የለም፡፡ ከአፉ አውጥቶ ካልተናገረ በስተቀር ምንም የምናውቀው ነገር አልነበረም። የሚነግረን ነገር ካለም ረጋ ብሎ ነው የሚነግረን። ግርፊያ፤ ዱላ፤ ቁጣ … የሚባል ነገር የለም፡፡ ጥፋት እንኳ ብታጠፋ ቁጭ አድርጎ የሚነግርህ ነገር ማጥፋትክን እንድትጠላው ነው የሚያደርግህ፡፡ እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ደግሞ ብዙም አልነበረም፡፡
ሌላው ልነግርህ የምፈልገው “ቅድሚያ ለእንስት” (Ladies First) በሚለው መርህ ላይ ያለውን እምነት ነው፡፡ እኔ ልጅም ሆኜ አሁን ጓደኞቼ አብዛኞቹ ወንዶች ናቸው፤ ብዙ ግዜ “ቅድሚያ ለእንስት” (Ladies First) በሚለው መርህ ላይ እንከራከራለን፤ ለምንድነው ቅድሚያ ለሴት የሚሰጠው ዓይነት ክርክር ማለቴ ነው፤ ይህ መርህ ግን ለአባባ አፋዊ ሳይሆን የውስጥ እምነቱ ነው፡፡ ለሴት ልጅ ክብር አለው፡፡
አንድ አጋጣሚ ልንገርህ፡- ወደ አሜሪካ ልመጣ ስል፤ ኢሚግሬሽን ለፓስፖርት ይሁን አሜሪካ ኤምባሲ ለቪዛ ይሁን አሁን ዘንግቼዋለሁ፤ ከሱ ጋር አብረን ሄደን ነበር። በቀኑ በጣም ብዙ ባለ ጉዳይ ስለነበር መቀመጫም አልተገኘም፡፡ በኋላ ቀደም ብለው መጥተው ወንበር አግኝተው ከተቀመጡት ሰዎች መካከል እሱን የሚያውቁ ሰዎች እንዲቀመጥ ተነሱለት፡፡ እሱ ደግሞ “አንቺ ተቀመጪ አለኝ”። እንዴ …? የተነሱት ላንተ ነው እኔ አልቀመጥም አልኩ፡፡ እሱ ግን “አንቺ ቆመሽ እኔ አልቀመጥም” ብሎ አስቀምጦኛል፡፡ ይህ የሚያሳየው ለሴት ልጅ ያለውን ክብር ነው፡፡
እኔና እህቴን አስቀምጦ ሲመክረን ብዙ ግዜ ሴት ልጅ ከጾታዋ ጋር በተያያዘ ሊደርስባት የሚችለውን ችግር ካስረዳን በኋላ መፍትሄው ደግሞ ትምህርት እንደሆነ አያይዞ ነበር የሚነግረን፡፡ በዚህ መልኩ ነበር የትምህርት ወሳኝነት ውስጣችን የሚያሰርፀው፡፡
ፕ/ር ብዙ የሚታወቁባቸው ጠንካራ የሰብዕና መገለጫዎችና ተያይዞም ችሎታዎች አሏቸው፡፡ ወዳንቺ የመጣው የትኛው ነው?
በልጅነቴም ብዙ ሰዎች በመልክ ትመስይዋለሽ ነው የሚሉት፡፡ ሌላ ሌላው ባብዛኛው ለሌላ ሰው የሚታይ ወይም ሌላው ሊናገረው የሚችል እንጂ ራስህ ስትናገረው ይከብዳል፡፡ ከሱ የተማርኩት የሚመስለኝ አንድ ነገር ፡- አልችለውም ብሎ ተስፋ መቁረጥ የሚባል ነገር የለብኝም። ማድረግ እችላለሁ (I can do it!) ብዬ ነው የምነሳው! የጀመርኩትን ግብ ሳላደርስ ተስፋ ቆርጦ ያለመቆም ዕልህ አለብኝ። ይህም ከሱ የመጣ ይመስለናል። እሱ በዚህ እድሜው እንኳ አንድ ነገር ከጀመረ ጫፍ ሳያደርስ ምንምና ማንም አያቆመውም፡፡
ሌላው ከሱ ወሰድኩ የምለው ጥቃትን በይሁንታ ወይም በያልፋል አይነት ትዕግስት አመለቀበልን ነው። አሁን ለምሳሌ እሱ የታሰረ ጊዜ እንደኔው ቤተሰባቸው ወይም አባታቸው የታሰሩባቸው ጓደኞቼ የሆነውን ተቀበሎ የማለፍን ነገር ሲያወሩ፣ ለኔ በፍጹም አይዋጥልኝም ነበር። የኔ ጥያቄ በመጀመሪያስ ለምን ይሆናል? ለምን ይታሰራል? ነው፤ አግባብ ያልሆነ ነገር ሲፈጸምብህ ወይም መብትህ ሲነካ ታግለህ መብትን ማስከበር እንጂ ስለ ምህረትና ስለ መሳሰሉት ነገሮች ማሰብ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ይህም እምነቴ ከሱ የተገኘ ይመስለኛል፡፡
ከፕ/ር የምታደንቂላቸው ችሎታና ባህሪዎች ጥቂቱን ልትጠቅሺልኝ ትችያለሽ…?
በመጀመሪያ የተፈጥሮ ስጦታ በመሆኑ ክሬዲት የሚሰጠው ባይሆንም የሱ ጭንቅላት የተለየና በጣም የሚደንቅ ነው፡፡ በትንሽ ጊዜ ውስጥ አንድን ነገር ከተለያየ አቅጣጫ አይቶ ላንተ የማይታይህን ነገር አይቶ የሚያቀርብበት ችሎታው ሁሌም ያስገርመኛል። አንድ አወያይ ሃሳብ ከተነሳ ያ ሃሳብ ብትንትኑ ወጥቶ ካልቀረበ አይረካም፡፡ የሰው ሃሳብ በትዕግስት ያደምጣል። እሱም ያለመሰልቸት ያስረዳል፡፡ ባጠቃላይ ሃሳብን የመመርመር ችሎታና ትዕግስቱን አደንቃለሁ፡፡ ሌላው ደግሞ ያመነበትን ነገር ፊት ለፊት ከመናገር የሚያቆመው የለም።
አሁን ባለንበት ህብረተሰብ አንድን ሀሳብ ተቃውመህ አልያም ወጣ ያለና የተለየ ሃሳብ ይዘህ ስትቀርብ እንደ ጠላት ወይም እንደ ድፍረት የመውሰድ ነገር እየተለመደ ነው፡፡ የታየህን ነገር በግልጽ ስትናገር ሃሳብህን እንደተለየ ሃሳብ ተቀብሎ በዚያው ስሜት ከመመዘን ይልቅ ከጥላቻ እንደመነጨ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ እንዲህ ዓይነት ልምድ እየገዘፈ በሄደበት ህብረተሰብ ውስጥ እንደ አባባ አይነት ሃሳቡን በግልጽ የሚናገር ሰው ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች ይገጥሙታል፡፡
በሦስት መንግስታት ውስጥ ሲያልፉ በተለያየ አጋጣሚ በትረ ስልጣኑን ከያዙት አካላት ጋር በነበራቸው አለመግባባት ቤተሰባችሁ ስጋት ውስጥ የወደቀበት የምታስታውሺው ትዝታ ካለ? በተለይ መንግስቱን ውረድ ባሉበት ወቅት ምን ተሰማሽ?
በመጀመሪያ የታሰረው እኔ ገና የ11 ወይም የ12 ዓመት ልጅ ሆኜ ይመስለኛል፡፡ የረብሻው ምክንያት በጊዜው ባይገባኝም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረበሸ ተብሎ እሱም ታስሮ ቤት ውስጥ የነበረው ግርግር ትዝ ይለኛል፡፡ ያኔ ደግሞ አዋቂ ሲያወራ ልጅ ወደ ውጭ ወይም ወደ ጓዳ የሚባልበት ዘመን ነበርና ስለታሰረበትና ስለረብሻው ምክንያት ብዙም የማስታውሰው ነገር ባይኖርም እንዲሁ ብቻ መታሰሩ ቤተሰቡን እንዳሳሰበ ትዝ ይለኛል፡፡
ሌላው እንዳልከው መንግሥቱ ኃይለማሪያምን ውረድ ባለበት ወቅት የተፈጠረው ነው፡፡ ያን ሁኔታ አሁንም ድረስ ሳስበው ይገርመኛል፡፡ በጊዜው እኔ እዚሁ አሜሪካን ሀገር ነበርኩ፡፡ ይህ በሆነበት ዕለት ወይም ማግስት ይመስለኛል አንድ ለሱም ለኔም ወዳጅ የሆነ ሰው ደውሎ “መስፍንን ሰሞኑን አግኝተሸዋል? “ሲል ጠየቀኝ፡፡ አይ ሰሞኑን አላገኘሁትም ብዬ ከመለስኩ በኋላ ነገሩ ስለከነከነኝ ምነው? ምን የተፈጠረ ነገር አለ? ብዬ ጠየቅኩት፡፡
“አይ አሁንም፣ በቃ መንግሥቱን ውረድ ብሎት አሁን ያለበት አይታወቅም፤ (He is in hiding)” አለኝ። በመጀመሪያ በጣም ደነገጥኩ፤ ተደብቋል የሚለው ነገር ከአባባ ተፈጥሮና ባህሪ ጋር በፍጹም የሚስማማ አልሆነልኝም፡፡ ልቀበለው አልፈለኩም፡፡
በመሆኑም ወዲያው ደውዬ ለማረጋገጥ ፈለኩ። ላገኘው አልቻልኩም፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ ያው ወዳጃችን መልሶ ደውሎ “ተደብቋል ያልኩሽ ቀልዴን ነው፡፡ መንግሥቱን ግን ውረድ ብሎት መንግሥቱ ሳይበሰጫጭ አልቀረም” ከጉዳዩ ክብደት አንፃር ቀልዱ ባይገባኝም፣ ተደበቀ የሚለው ነገር እውነት አለመሆኑን መቀበል አልከበደኝም፡፡
በኋላም ደውዬ ሳገኘው ተረጋጋሁ፡፡ እንደተፈራው አልሆነም፤ መንግስቱም አገር ጥሎ ጠፋ፤ ሁሉም በዚሁ አበቃ፡፡ እንደሰማሁ ግን በጣም በጣም ነበር የደነገጥኩት።
የእሳቸው ልጅ በመሆንሽ ምን ይሰማሻል?
ይሄ ምን ያጠያይቃል ብለህ ነው? (ሳቅ) የሱ ልጅ በመሆኔ በጣም! በጣም ነው የምኮራው፡፡ በነገራችን ላይ እናቴም ያልተዘመረላት ጀግና እንደሚባሉት አይነት ነች። ከነዚህ ሰዎች መፈጠሬ ለኔ ክብሬም ኩራቴም ነው፡፡
እኔ ብቻ ሳልሆን ሁላችንም ኢትዮጵያዊያኖች እዚህ የደረስነው ብዙ ዋጋ ተከፍሎ ነው፡፡ ለሃገራቸው ድንቅ ስራ ሰርተው፤ ግዙፍ መስዋዕትነት ከፍለው ለዛሬው ማንነታችን ያበቁንን አባት እናቶቻችንን ውለታ ተሸክመን ነው የምንኖረው፡፡ እኔም ከሱ በመፈጠሬ ደስታዬ ወሰን የለውም፡፡

Read 9495 times