Saturday, 01 August 2015 14:17

ኦባማ በተቃዋሚዎች ክፉኛ ተተቹ መንግሥት ትችቱን አጣጥሎታል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(25 votes)

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክቶ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ሲሆን ተቃዋሚዎች ፕሬዚዳንቱ በጉብኝታቸው የኢትዮጵያን የሰብዓዊ መብት አያያዝና የዲሞክራሲ ሁኔታ ትኩረት ነፍገውታል ብለዋል፡፡ ኦባማ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት “በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ነው” ማለታቸውን ተቃዋሚዎች ተቃውመውታል፡፡
መንግሥት በበኩሉ፤ ፕሬዚዳንት ኦባማ እውነታውን ነው የገለፁት ብሏል፡፡  
የፕሬዚዳንቱን ጉብኝት አስመልክቶ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የሚሰነዝሯቸው ትችቶች ውሃ የማይቋጥሩ ናቸው ሲልም መንግሥት ነቅፏል፡፡
በማህበራዊ ድረገፆች ላይ የግል ፖለቲካዊ ዕይታዎቹን በማቅረብ የሚታወቀው የፖለቲካል ሣይንስ ተመራቂው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው በሰጠው አስተያየት፤ ኦባማ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ያስተላለፉት መልዕክት ከጠበቀው በተቃራኒ እንደሆነበት ይናገራል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ስለ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት አያያዝ አሉታዊ ሪፖርቶችን እያወጡ ባሉበት ሁኔታ፣ ፕሬዚዳንቱ እዚህ ድረስ መጥተው “በአገሪቱ ያለው መንግሥት በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ነው” በማለት እውቅና መስጠታቸው ፈፅሞ ያልጠበቅሁት ነው” ብሏል፡፡ በፕሬስ ነፃነት ጉዳይና በሰብአዊ መብት አጠባበቅ ላይ ፕሬዚዳንቱ ይፈጥራሉ ብዬ የጠበኩትን ያህል ተፅዕኖ አለመፍጠራቸውን ተገንዝቤአለሁ ብሏል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በአፍሪካ ህብረት ያደረጉት ንግግር ይበልጥ ቴክኒካል የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር ነው ያለው ጋዜጠኛው፤ “ያ ግን በአጠቃላይ አፍሪካን እንጂ ኢትዮጵያን የሚመለከት ባለመሆኑ የሀገሪቱን የመንግስት እንቅስቃሴ ለሚከታተል ኢትዮጵያዊ ትርጉም አልባ ይሆንበታል” ብሏል፡፡
እንደ አጠቃላይ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር ከተወሰደ ፕሬዚዳንቱ በአፍሪካ ህብረት ያደረጉት ንግግር ከሊበራል መሪ የሚጠበቅ ነው የሚለው አስተያየት ሰጪው፤ ፕሬዚዳንቱ እንዲህ ያለ ንግግር ሊያደርጉ የቻሉትም አሜሪካውያን ካላቸው ግብረ-መልስን እንደትልቅ ግብአት የመጠቀም የሠለጠነ አካሄድ በመነሳት፣ በቤተመንግስት በተሰጠው መግለጫ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንደተከፋ ተገንዝበው ያደረጉት የተሠላ ንግግር ይመስለኛል ብሏል፡፡
“ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ያላቸውን ትክክለኛ አቋም ያንፀባረቁት በቤተመንግስት በሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፤ በአፍሪካ ህብረት ያደረጉት ንግግር የሽንገላ ነው” ሲልም ትዝብቱን ገልጿል፡፡
“ባለፈው እሁድ አመሻሽ ላይ ፕሬዚዳንት ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ስመለከት ከደስታዬ ብዛት አልቅሻለሁ” ያለው ሌላው አስተያየት ሰጪ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት የጋዜጠኝነት ተማሪ የሆነው ቢንያም በበኩሉ፤ ፕሬዚዳንቱ በሃገሪቱ ያለውን ለውጥ መመልከታቸውና ሰላም መሆኑን ማየታቸው ትልቅ ነገር ነው ባይ ነው፡፡
“ፕሬዚዳንቱ እንዴት ኢህአዴግ በስልጣን ላይ እያለ ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ? በሚለው ሃሳብ አልስማማም” ያለው ቢኒያም፤ “ማንም በስልጣን ላይ ቢኖር የታላቅ ሃገር መሪ መጥቶ ሲጎበኝ አገሪቱ ተሰሚነቷና ተቀባይነቷ እያደገ መምጣቱን ጠቋሚ ነው፤ ነገ ይሄ መንግስት ወርዶ በሌላ ቢተካም ሃገራዊ ጥቅምን አስቀድሞ ማየት ተገቢ ነው” ብሏል፡፡
ከጥቂት ዓመታተ በፊት ፕሬዚዳንት ኦባማ፤ ሆስኒ ሙባረክ የሚመሩትን ሃገር ለመጎብኘት ግብፅ መሄዳቸውን ያስታወሰው አስተያየት ሰጪው፤ በወቅቱ በኢትዮጵያ እንዳደረጉት ለ30 ዓመት በስልጣን ላይ ከቆዩት ሙባረክ ጋር ተወያይተው፣ ግብፅን አድንቀውና አንቆለጳጵሰው ተመልሰዋል፤ በጥቂት ወራት ውስጥ ግን የተፈጠረው ሌላ ታሪክ ነው፡፡” ይላል፡፡ በፕሬዚዳንት ኦባማ የተጎበኙት ሙባረክ፤ በህዝባዊ አመፅ ከስልጣናቸው ሲወርዱ አመፁን ከደገፉትና በአመፅ ስልጣን ላይ ለወጣው መንግሥት እውቅና ከሰጡት ቀዳሚ ሃገራት አንዷ አሜሪካ ነበረች በማለት አሁኑ ጉብኝት ዋስትና እንደማይሆን ገልጿል፡፡
“የኢትዮጵያ መንግስትም ቢሆን ሙሉ ለሙሉ በአሜሪካ የሚተማመን መንግሥት አይመስለኝም” ያለው አስተያየት ሰጪው፤ ፕሬዚዳንቱ በአፍሪካ ህብረትም ሆነ በብሄራዊ ቤተ መንግሥት ያደረጓቸው ንግግሮችና የሰጧቸው መግለጫዎች ብዙም የአቋም ለውጥ የሚያስከትሉበት አይመስለኝም” ብሏል፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ በአፍሪካ ህብረት ባደረጉት ንግግር ላይ የተገኙት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፤ “የፕሬዚዳንቱን ንግግር ልብ ብሎ ያዳመጠ ሰው ጠንከር ያለ መልዕክት መያዙን ይረዳል” ይላሉ - በተለይ በዲሞክራሲ ሂደት ላይ የአፍሪካ መሪዎች መከተል የሚገባቸውን መናገራቸውን በመግለፅ፡፡ ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሬዚዳንቱን ንግግር ሰምቶ ተግባራዊ ያደርጋል የሚል ግምት የለኝም፤ ዶ/ር ጫኔ፡፡
ኦባማ፤ “በኢትዮጵያ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግሥት ነው ያለው” ማለታቸው ከዲፕሎማሲ ቋንቋነት የዘለለ ትርጉም አይኖረውም ያሉት የኢዴፓ መሪ፤ ኦባማ ሃገሪቱን ለመጎብኘት ሲመጡ የግድ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት መቀበል ስላለባቸው እንጂ ሙሉ እውቅና ከመስጠት ጋር አይያያዝም ባይ ናቸው፡፡
“በየትኛውም መንገድ አምባገነን መሪ በስልጣን ላይ ሊቀጥል ይችላል” የሚሉት የፓርቲው መሪ፤ ኃያላኑ መንግስታት ማተኮር የሚፈልጉት የዲሞክራቲክ ተቋማት በሚጠናከሩበት ሁኔታ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡
ልማት ያለ ዲሞክራሲ ብዙ አያስኬድም ያሉት ዶ/ር ጫኔ፤ የአረብ ሃገራት በልማት የመጠቁ ሃብታሞች ቢሆኑም በዲሞክራሲ ያለመጠናከራቸው በፈጠረባቸው ጣጣ  እንደገና እየፈረሱና እየወደቁ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በኢትዮጵያም መልካም አስተዳደርና የህዝብ ይሁንታ ያለው መንግስት በስልጣን ላይ እስካልተቀመጠ ድረስ እድገቱ ቀጣይነት አይኖረውም ብለዋል፡፡ የኦባማ ንግግሮች ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም አላቸው ብዬ አላስብም ያሉት ዶ/ር ጫኔ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ካለው አደረጃጀትና አወቃቀር አንፃር እንዲህ በቶሎ ይቀየራል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልፀዋል፡፡
ባራክ ኦባማ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን በበጎ ጎኑ እንደሚመለከቱት የተናገሩት ታዋቂው  ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው፤ ፕሬዚዳንቱ በሃገሪቱ በነበራቸው ቆይታ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ለውጦች መኖራቸውን መገንዘባቸው መልካም እንደሆነ ጠቁመው በሰብአዊ መብትና ዲሞክራሲ ጉዳይ ላይ ግን የነበራቸው ግንዛቤ የተዛባ ይመስለኛል ብለዋል፡፡ በንግግራቸው ላይ የመለሳለስና ከእውነታው የመሸሽ ነገር ማስተዋላቸውን በመግለፅ፡፡
ፕሬዚዳንቱ በጉብኝታቸው በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሚያውቁትን ያህል ትችት ይሰነዝራሉ ብሎ መጠበቅ ያስቸግራል ያሉት አቶ ልደቱ፤ የጉብኝታቸው አላማ የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ በመሆኑ በአዎንታዊ ነገሮች ላይ ለማተኮር መርጠዋል፡፡ መጀመሪያም በመሬት ላይ ያለውን ሃቅ በትክክል የሚያሳይ ንግግር ያደርጋሉ ብዬ አልጠበቅሁም፤ የሆነውም እንደጠበቅሁት ነው ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ህብረት ባቀረቡት ንግግር፣ የአፍሪካ መሪዎችን ስልጣንን የሙጥኝ ማለት በተመለከተ በቀልድ አዋዝተው ያስተላለፉት መልዕክት የተሻለ ነበር ያሉት አቶ ልደቱ፤ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብት አያያዝና የዲሞክራሲ ሁኔታ ግን ያወቁ አልመሰለኝም፡፡ የሚያውቁትም ከሆነ ጠንከር ባለ ቋንቋ ለመግለፅ ድፍረት አጥተዋልሰ ብለዋል፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ያለው መንግስት “በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ነው” ማለታቸው ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው በአፍሪካ ህብረት ባደረጉት ንግግር ግን መሰረታዊ ችግሮችን በማንሳት መናገር የሚገባቸውን ያህል ተናግረዋል ብለዋል። ከኢትዮጵያ ጋር የሚያስተሳስራቸው ዋነኛ ጉዳይ ሽብርተኝነትን የመዋጋት አጀንዳ ነው ያሉት ምሁሩ፤ በዲሞክራሲና በሰብአዊ መብት ዙሪያ ብዙም ተፅዕኖ ለማድረግ አለማሰባቸውም መነሻው ይሄው ነው ብለዋል፡፡
ሌላው አንጋፋ ፖለቲከኛና የመድረክ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ደግሞ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ለኢህአዴግ መንግስት ውዳሴና ቡራኬ ከመስጠት ባሻገር ብዙም ፋይዳ አልነበረውም ባይ ናቸው። “በጉብኝቱ ኢህአዴግ ድል ተቀዳጅቷል” ያሉት ሊቀመንበሩ፤ ኦባማ የኢትዮጵያ መንግሥት “በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ነው” ማለታቸውን የጠቀሱት ፕ/ር በየነ፤ ኢህአዴግ ከዚህ በላይ የሚፈልገው ነገር ሊኖር አይችልም ሲሉ ጉብኝቱ ለመንግሥት ትልቅ ድል ማስገኘቱን ገልፀዋል፡፡ ለእኛና ለህዝቡ ግን ምንም ፋይዳ አልነበረውም ይላሉ ፕ/ር በየነ፡፡
የኢህአዴግ ጽ/ቤት የህዝብና የውጪ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው ግን ከአብዛኛው አስተያየት ሰጪዎች የተለየ አቋም ነው ያላቸው። ኦባማ የኢትዮጵያ መንግሥትን “በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ ነው” ማለታቸው ትክክለኛ አቋም መሆኑን ጠቁመው፤ ይሄ ደግሞ የእሳቸው ብቻ ሳይሆን የአሜሪካ መንግሥትም አቋም ነው ብለዋል፡፡
“ተቃዋሚዎች አሁንም ምርጫውን በተመለከተ ራሳቸውን ዞር ብለው ማየት አለባቸው፤ ህዝቡ ኢህአዴግን ለምን መረጠ? እኛ ለምን ተሸነፍን? ችግራችን ምንድን ነው? የሚለውን በዝርዝር ማየት ይገባቸው ነበር፤ ነገር ግን ይሄን ለማድረግ አሁንም ፍላጎቱ የላቸውም” ያሉት አቶ ደስታ፤ ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግም አልፈው የአሜሪካ መንግስትን በመወንጀል ላይ ናቸው ብለዋል፡፡ “ይሄ አካሄዳቸው ግን ትክክል አይደለም፤ ከእውነታው ያፈነገጠ ነው፤ የህዝቡን ውሳኔም ማክበር አለባቸው” ሲሉም አቶ ደስታ ተናግረዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት በሰላም፣ በልማትና በዲሞክራሲ ዘርፎች የተቀዳጀነው ስኬት ውጤት ነው ያሉት አቶ ደስታ፤ ኦባማ አገሪቱ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት ያላት መሆኑን መመስከራቸው የአገሪቱን ገፅታ በበጎ መልኩ እንደሚገነባ ገልፀዋል፡፡

Read 7963 times