Saturday, 01 August 2015 14:15

ለቅጣት በሚል የተሽከርካሪዎችን ታርጋ መፍታት ተከለከለ

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(13 votes)

በአዲስ አበባ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን ለቅጣት በሚል ታርጋ መፍታት መከልከሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
መንጃ ፍቃድ ሳይዙ ማሽከርከር፣ የክስ ወረቀት ለ48 ሰዓታት ሳይከፍሉ ማቆየት፣ በማይፈቀድ የመንጃ ፍቃድ ደረጃ ማሽከርከር እንዲሁም የሚያጠራጥር መንጃ ፍቃድ ተይዞ ሲገኝ ትራፊክ ፖሊስን ጨምሮ ሌሎች የህግ አካላት ታርጋ ይፈቱ እንደነበር የጠቆሙት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ፤ ይህ አሰራር አንዳንድ ህገ-ወጥ ግለሰቦች ሰሌዳውን ራሳቸው በመፍታት የተለያዩ ወንጀሎች እንዲፈፅሙ መንገድ በመክፈቱ የተሽከርካሪዎችን ታርጋ መፍታት ተከልክሏል ብለዋል፡፡ አሽከርካሪዎች የህግ ጥሰት ፈጽመው ሲገኙ ታርጋ ከመፍታት ይልቅ መኪናውን በቀጥታ ወደ ጣቢያ በመውሰድ ቅጣቱን እንዲያገኝ ይደረጋል ብለዋል - ምክትል ኢንስፔክተሩ፡፡ ታርጋ ሊፈታ የሚችልበትን ብቸኛ ምክንያት ሲጠቅሱም፤ የተከለከለ ቦታ መኪና ቆሞ ሲገኝና አሽከርካሪው ከሌለ ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
አሽከርካሪው መኪናውን ከማንቀሳቀሱ በፊት የክስ ወረቀት ተቀብሎ ታርጋውን ሊያስመልስ እንደሚገባ የገለፁት ምክትል ኢንስፔክተሩ፤ ያለ ታርጋ ማንቀሳቀስ በፍፁም የተከለከለ ነው ብለዋል፡፡
ያለ ሰሌዳ በመኪና መንቀሳቀስ ወንጀል በመሆኑ ህብረተሰቡ በስልክ ቁጥር 011 1 11 01 11 በመደወል ለፖሊስ ጥቆማ እንዲያደርግ ወይም በአቅራቢያው ላለ ትራፊክ ፖሊስ እንዲጠቁም ኢንስፔክተሩ አሳስበዋል፡፡ ይህንን ህግ የማይተገብሩ ትራፊክ ፖሊሶች ከተገኙም አሽከርካሪዎች በዚሁ ስልክ ቁጥር እንዲያሳውቁ ጠይቀዋል፡፡
አዲሱ ህግ እየተሰራበት ያለው በመዲናዋ ብቻ መሆኑን በመግለፅም ህጉ በክልል ከተሞችም ቢተገበር ህገ ወጦችን ለመከላከል እንደሚያስችል ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

Read 5615 times