Monday, 27 July 2015 11:29

አወዛጋቢውና ደም አፋሳሹ የብሩንዲ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ምርጫው አገሪቱ በዴሞክራሲ መራመዷን ያሳያል ብለዋል
               - የዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ሌላ ምርጫ እንዲካሄድ ጠይቀዋል
   አወዛጋቢውና ደም አፋሳሹ የብሩንዲ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ባለፈው ማክሰኞ የተካሄደ ሲሆን ለመምረጥ ከተመዘገቡት 3.8 ሚሊዮን የአገሪቱ ዜጎች መካከል 74 በመቶው ድምጻቸውን እንደሰጡ የብሩንዲ የምርጫ ኮሚሽን ፕሬዚደንት ፔሪ ካልቬር ዳይካሬ ባለፈው ረቡዕ መናገራቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ህገ መንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጪ ለሶስተኛ ዙር የስልጣን ዘመን በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳባቸው የብሩንዲው ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ፣ ሃሳባቸውን እንዲቀይሩ ጫና ቢደረግባቸውም በእምቢተኝነት በተወዳደሩበት ምርጫ ድምጽ የሰጡ ሲሆን ምርጫው ብሩንዲ በዲሞክራሲ አንድ እርምጃ ወደፊት መራመዷን የሚያሳይ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የአገሪቱ ቀንደኛ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆኑት አጋቶን ርዋሳ በበኩላቸው፣ አገሪቱ እንደ አገር እንድትቀጥልና የከፋ ደም መፋሰስ እንዳይከሰት ከተፈለገ፣ የምርጫው ውጤት ይፋ በተደረገ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብሄራዊ የአንድነት መንግስት ሊያቋቁሙ ይገባል ሲሉ ለፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ ጥሪያቸውን እንዳቀረቡ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ምርጫው የአገሪቱ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ባገለሉበት ሁኔታ የተከናወነ በመሆኑ አሳታፊ አይደለም ያሉት ርዋሳ፣ የሚቋቋመው ጊዜያዊ የብሄራዊ አንድነት መንግስት በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ሌላ ምርጫ እንዲያካሂድም ጠይቀዋል፡፡
አሜሪካ የመንግስት ሃይሎች ተቃዋሚዎችንና የሲቪክ ማህበራትን በሚያዋክቡበት፣ መገናኛ ብዙኃን በተዘጉበትና መራጮች በሚገደዱበት ሁኔታ የተደረገው የብሩንዲ ምርጫ ተዓማኒነት የለውም ማለቷን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፣ ካለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ ምርጫው ባስነሳው ብጥብጥ ከ100 በላይ ዜጎች መሞታቸውንና ከ170 ሺህ በላይ የሚሆኑትም አገር ጥለው እንደተሰደዱ አስታውቋል፡፡
የተመድ ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙን በበኩላቸው፤የብሩንዲ የፖለቲካ ሃይሎች አገሪቱንና ህዝቧን ወደ ከፋ ጥፋት የሚያስገቡና በአካባቢው አለመረጋጋትን የሚያስከትሉ ተግባራትን ከመፈጸም እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመዲናዋ ቡጁምቡራና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በተቃዋሚዎችና በመንግስት ወታደሮች መካከል ግጭት በቀጠለበት ሁኔታ ማክሰኞ ዕለት የተከናወነው ምርጫ የድምጽ ቆጠራ ረቡዕ መጠናቀቁን የዘገበው አልጀዚራ፣ ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ በሰፊ ልዩነት ያሸንፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡

Read 2210 times