Monday, 27 July 2015 11:25

ሞሮኮ ወጣት ዜጎቿ ወደ ቱኒዝያ እንዳይሄዱ ከለከለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 አሸባሪ ቡድኖችን ሊቀላቀሉ ይችላሉ በሚል ሰግታለች
  የሞሮኮ መንግስት የአገሪቱ ወጣቶች ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር ሊቀላቀሉ ይችላሉ በሚል ስጋት ለመዝናናት ወደ ቱኒዝያ የሚያደርጉትን ጉዞ መከልከሉን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ወቅቱ የሞሮኮ ወጣቶች ለመዝናናት በብዛት ወደ ቱኒዝያ የሚጓዙበት እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ የአገሪቱ መንግስትም የተወሰኑ ወጣቶች አጋጣሚውን ተጠቅመው ወደ ሊቢያ በማምራት ከአሸባሪና ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር ሊቀላቀሉና የሽብርተኝነት ስልጠና ሊወስዱ ይችላሉ በሚል ስጋት፣ ሁሉንም የአገሪቱ ወጣቶች ወደ ቱኒዝያ እንዳይሄዱ መከልከሉን ገልጧል፡፡ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጽንፈኛ ቡድኖች ጋር የሚቀላቀሉ የአገሪቱ ወጣቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱ ስጋት የፈጠረበት የሞሮኮ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ወጣቶቹን ከጥፋት ተግባር ለመታደግ ውሳኔውን አስተላልፏል ብሏል ዘገባው፡፡በቅርብ ጊዜ ውስጥ ብቻ 1 ሺህ 600 ያህል ሞሮኳውያን ወደ ሶርያ በማቅናት ጽንፈኛ ቡድኖችን መቀላቀላቸውንና ስልጠና መውሰዳቸውን የገለጸው ዘገባው፣ የአገሪቱ መንግስትም የችግሩን አሳሳቢነት በማጤን የጉዞ እገዳ ውሳኔውን ማስተላለፉን አስታውቋል፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤አሸባሪውን አይሲስ የሚቀላቀሉ ሞሮኳውያን ቁጥር እያደገ መምጣቱን በመግለጽ፣ ለመዝናናት ወደ ሞሮኮ የሚሄዱ ዜጎቹን የሽብር ጥቃት ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ማስጠንቀቁንም ዘገባው አክሎ አስታውሷል፡፡በቱኒዝያ የመዝናኛ ስፍራ በተከሰተው የሽብር ጥቃት 38 የተለያዩ አገራት ዜጎች ለሞት መዳረጋቸውን ተከትሎ፣ እንግሊዝን ጨምሮ በርካታ የአለማችን አገራት ዜጎቻቸው ወደ ቱኒዝያ እንዳይሄዱ መከልከላቸውንም ዘ ኢንዲፔንደንት አስታውሷል፡፡

Read 2169 times