Monday, 27 July 2015 10:27

አቤቱታ ለአንድዬ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
መስከረምም ደረሰ፣ ሌላ ዓመትም ሽው ብሎ ሄደ፡፡ ይኸው ሆኗል ነገራችን-- አሮጌ ዓመት መሸኘት አዲስ ዓመት መቀበል፡፡ አምና ከዘንድሮው እየተሻለ ከተረተ አያልፍም ያልነው ነገር ሁሉ እውነት እየሆነ ይኸው እዚህ ደረስን፡፡
ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ ከብዙ ጊዜ በፊት እንዲሁ ነገሩ ሁሉ ግራ ቢገባኝ አዋይቼህ ነበር፡፡ አስታወስከኝ?
አንድዬ:- ማን ልበል አንተን?
ምስኪን ሀበሻ:- ይሄን ያህል ረስተኸኛል ማለት ነው? የሰው ልጅ መገኛ፣ የስልጣኔ መሠረት አገር ይዤ ምን ልበል ትለኛለህ? እሺ ይሁን… ምስኪኑ ሀበሻ፡
አንድዬ:- ይቅርታ… ምስኪን ሀበሻ ልጅ ነው ያልከኝ…ዘነጋሁ ልበል!
ምስኪን ሀበሻ:- እንዴት አንድዬ ይኸው ስንት ክፍለ ዘመን ሙሉ እጆቻችንን  ወዳንተ እንደዘረጋን አይደል! እንደው ተሳስተህ እንኳን “እነኛ እጆቻቸውን ያንከረፈፉት እነማን ናቸው ሳትል ቀርተህ ነው?
አንድዬ:- እህ! አስታወስኩ…እኔ የምለው እንደው ክንዳችሁ አለመዛሉ ግርም ይለኛል! የእናንተ ነገር እኮ እኔንም ግራ ገባኝ!
ምስኪን ሀበሻ:- ኧረ አንድዬ ግራ የገባን እኛ ነን። እንዴት ግራ እንደገባን ብታየን በሆነ ተአምር ግራ መጋባትን ከዓለም የሚያጠፋ የሙሴ በትር ትልክልን ነበር፡፡
አንድዬ:- ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ…መጀመሪያ የፈጠርኩት አዳምን ነበር፡፡ የእሱ ዝርያዎች ደግሞ አያሳስቱኝም፡፡ እናንተን ሳያችሁ ከዓዳም ሌላ የሆነ ሰው ፈጥሬ ይሆን እንዴ እያልኩ እራሴን እጠይቃለሁ፡፡ ብቻ ለጊዜው ብዙ ሌሎች የማያቸው ፋይሎች ስላሉ ትኩረቴ ሁሉ ወደዛ ነው፡፡ ትንሽ ተንፈስ ስል ወደ እናንተ እዞራለሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ ኧረ ተው ከእኛ የሚብስ የለም! ስንት ስምንተኛው ሺህ መሰለህ አጠገባችን እየደረሰ እያሳዘንነው ነው መሰለኝ ያልፈናል፡፡ አንድዬ ቢያንስ፣ ቢያንስ እንደው ስምንተኛው ሺህ የሚያስመስሉ ነገሮችን ሰውርልን! አንድዬ…እኛስ እንደው እንደሌላው ትንሽ ዘመን እንኳን ሳንቆራቆስ፣ “ግነን በሉኝ” ሳንባባል፣ እርስ በእርስ ሳንጠፋፋ፣ አንዳችን ለሌላችን ጉድጓድ ሳንማማስ… መኖር አያምረንም!
አንድዬ:- እንደሱ ብዬማ ብዙ ሞከረኩ፣ ባያችሁ፣ ባያችሁ እንኳን የራሳችሁን ሰባራ ልትጠግኑ ጭርሱን ወደ እኔ ዞራችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ:- ኧረ ተው አንድዬ…ምን ብለን ነው ወዳንተ የምንዞረው ማን አለንና! ጠላቶቻችን የሚነዝቱንማ አትስማ፡፡
አንድዬ:- እኔ እኮ የምለው…መቼ ነው ጠላታችን፣ ጠላታችን ማለት የሚበቃችሁ! እንደው በገዛ ፍጡርህ ላይ ጨከንክ አትበለኝና አሁን እኮ የራሳችሁ ጠላት ራሳችሁ ናችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ:- ጌታዬ፣ አታምርር እንጂ…
አንድዬ:- ደግሞ እኮ የክፋታችሁ ክፋት በገዛ ቤቴ መጥታችሁ የምትጠይቁኝ ጥያቄ የሰይጣን ጆሮ አይስማው እንጂ አንዳንዴ ምን ስል ነው የፈጠርኳቸው እላለሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ:- ምን አደረግን?
አንድዬ:- ቤቴ መጥታችሁ ጤና ስጠን፣ ፍቅር ስጠን፣ ሀብት ስጠን ብትሉ ይገባኛል። ልዩነትን አርቀህ ነፋስ የማይገባው ወንድማማችነትና እህትማማችነት ስጠን ብትሉኝ፣ ምንም እንኳን ለእኔም እንኳን የሚያስቸግር ቢመስልም፣ ይገባኛል፡፡
ምስኪን ሀበሻ:- አፋቅረንና አዋደን ከማለት ሌላ ምን አልን! እንደ ባህር አሸዋ ሀብት አብዛልን ከማለት በስተቀር ምን አልን!
አንድዬ:- ‘የእሷን ነገርማ ካላሳየኸኝ፣’ ‘እሱን ልክ ካላገባህልኝ’ እያላችሁ ጭርሱን…የዲያብሎስን ሥራ ወደ እኔ ታዞሩ፡፡
ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ ቢጨንቀን እኮ ነው…ሰዉ አላስቀምጠን ቢለን እኮ ነው! ጉልበተኛ እየበዛብን አቅም ቢያንሰን እኮ ነው!
አንድዬ:- ደግሞም ቤቴን ተሳልማችሁ ትወጡና በሩን በሚገባ ሳትሻገሩና የጸሎት መጽሐፍ ከኪሳችሁ ሳይወጣ ጠጠር ብተና ትሄዳላችሁ…ኧረ
ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ…ጨነቀና! አንተ ዝም ስትለን ሌላ በኩል እንሞክር ብለን ነዋ! ጌታዬ የቸገረው እርጉዝ ያገባል እያልን ስንተርት አልሰማህም! እዚህ፣ እዛ የምንለው ከጭንቀት ነው፡፡
አንድዬ:- ዶሮውንና ንፍሮውን በየሰዉ አጥር እየጣላችሁና እየበተናችሁ ምግብ አጠረን፣ ራበን ትሉኛላችሁ፡፡ ጽላቱን ምኑን ምናምኑን እየጫናችሁ እየወሰዳችሁ… ተወው እባክህ፣ አድሮ ጭቃ ለሚሆን ነገር ትንፋሼን የምጨርሰው እንዲሁ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ አታምርር እንጂ…
አንድዬ:- አሁን ዋናው ነገር ለምን ነበር ፈለግሁህ ያልከኝ?
ምስኪን ሀበሻ:- ኧረ አንድዬ እኛ እኮ ሁልጊዜ እንደፈለግንህ ነው፡፡
አንድዬ:- ቤቴ መጥታችሁ ጽላትና መስቀል ሸጉጣችሁ የምትወጡ ጉዶች… በአፋችሁ እኔን እያመሰገናችሁ በልባችሁ ሉሲፈርን የምትለማመኑ…አሁን እኔን የምትፈልጉኝ ክፋታችሁን፣ ሀጢአታችሁን እንድባርክላችሁ ነው!
ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ አንዳንድ ምግባረ ብልሹዎች እኮ በየቦታው አይጠፉም…ሁላችንንም አትውቀሰና!
አንድዬ:- ትሰማኛለህ የእኔን ቃል የሚያስፋፉ እኮ በባዶ እግራቸው እሾሁና ቆንጥሩ እየወጋቸው፣ ጦማቸውን እየዋሉ እያደሩ፣ በየበረሀው እየተንከራተቱ ነበር፡፡ አሁን የመኪና አይነት እያማረጥክ፡ በፎቅ ላይ ፎቅ እየከመርክ የመልካም ምግባርና የሀጢአትን ትርፍና ኪሳራ ከማስላት ይልቅ በሰበብ አስባቡ በእምነት ስም የምትሸጠውን ቁሳቁስ ትርፍና ኪሳራ እያሰላህ አንድዬ፣ አንድዬ እያልክ ልትባባልኝ አትሞክር፡፡
ምስኪን ሀበሻ:- ዛሬ የእውነትም ተበሳጭተህብናል ማለት ነው…
አንድዬ:- በቪላ ቤት እየተንደላቃቃችሁ፣ በዘመናዊ መኪና እየተንደላቀቃችሁ፣ ቀን የለበሳችሁትን ልበሰ ተክህኖ ሌሊት በብጣሽ ጨርቅ የምትለውጡ፣ በእኔ ስም የቀረቧችሁን እሀቶቻችሁን ለተራክቦ ስታግባቡ..
ምስኪን ሀበሻ:- ኧረ አንድዬ ሀጢአታችንን እንዲህ አታብዛብን! ምግባረ ብልሹዎች በየቦታው አሉ እያልኩ እኮ ነው፣ አንድዬ!  ታዲያ በጥቂት ምግባረ ብልሹዎች ሁሉም አይኮነንማ!
አንድዬ:- እኔም ሁሉንም አልኮነንኩም፡፡ አሁንም ልበ ንጹሀን፣ ምግባረ ሰናዮች ሞልተዋል፡፡
    ግን ትሰማኛለህ፣ ምስኪን ሀበሻ… ማን ምን እንደሚሠራ እያንዳንድህ ታውቀዋለህ። ደግሞ እኮ የሁልህም መጀመሪያ አንድ ዓዳም ያልነበረ ይመስል… ሦስት አራት ቦታ ጎጥ እየለያችሁ የወንዜ ልጅ፣ የአገሬ ልጅ እየተባባላችሁ ስሜን የማትፈልጉትን ማጥቂያ፣ የምትፈልጉትን መጥቀሚያ እያደረጋችሁት ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ:- ምን መሰለህ አንድዬ ትምህርቱ እየተበረዘ…
አንድዬ:- ጠባያችን እየተበረዘ በለኝ እንጂ፡፡ ቀን በእኔ ስም ዘምራችሁ ማታ እርቃናችሁን አሼሼ ገዳሜ የምትሉ..
ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ፣ አሁን ምን መሰለህ፡፡ ግራ ገባን፣ ተደነጋገረን…ብቻ ምን አለፋህ ሀበሻ ለሀበሻ እንዲሁ በነገር ተባልተን ልንተላለቅልህ ነው፡፡ መተማመን ጠፋ፣ ወዳጅነት ጠፋ፡፡
አንድዬ:- እኮ ምን አድርግ ነው የምትለኝ?
ምስኪን ሀበሻ:- ተአምሩን ላክልና አንድዬ! ተአምሩን ላክልን፡፡ የሚያስተቃቅፈንን፣ የሚያዋድደንን ተአምሩን ላክልን!
አንድዬ:- ከራሴ ጋር ልምከርና እነግርሀለሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ አንተም እንደ እኛ ቀጠሮ!
አንድዬ:- አዎ ቀጠሮ…ምን መሰለህ፣ የሀበሻ ልጅ… እንዳንተ በየጊዜው በሬን እያንኳኩ የማይጨቀጨቁኝ፣ ሥራቸውን እየሠሩ አበርታን የሚሉኝ፣ ንፍሮን ለምግብነት የሚጠቀሙ እንጂ በየሜዳው በትነው ራበን የማይሉ…  ብዙ ስላሉ ሰሞኑን እነሱን እንዴት እንደምሸልም እያሰብኩ ስለሆነ የአንተን ጉዳይ በኋላ እመለስበታለሁ፡
ምስኪን ሀበሻ:- አንድዬ!
አንድዬ:- ጨረስኩ፡፡
የእነሱን ጉዳይ ቶሎ ጨርሶ ሃሳቡን ወደ እኛ የሚያዞርበትን ጊዜ ያፍጥልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2341 times