Monday, 27 July 2015 10:04

ሆቴሎች ለኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ሚና አለባቸው ተባለ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

  አሁን ከ21ሺ በላይ አልጋ ያላቸው ከ600 በላይ ሆቴሎች አሉ
                   የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ የሆቴሎች ኮከብ ምደባ ተጠናቋል
                                  
       ኢትዮጵያ 3ኛውን ገንዘብ ለልማት ኮንፈረንስ በማስተናገዷ ለሚዲያ ከፍላ ከምታገኘው እጅግ የላቀ የገጽታ ግንባታ ማከናወኗን የባህልና ቱሪዝም ሚ/ር አስታወቀ፡፡ ሆቴሎች ለኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ሚና አላቸው ብሏል - ሚ/ር መስሪያቤቱ፡፡  
አገሪቷ በአንድ ጊዜ ከ7 ሺህ በላይ እንግዶች ተቀብላ ያለአንዳች የመስተንግዶ ችግር መሸኘቷ እጅግ የሚደነቅ ነው ያሉት በባህልና ቱሪዝም ሚ/ር የህዝብና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ፣ እንግዶቹ በተደረገላቸው መስተንግዶ ተደስተው በአገሪቷ ዕድገት ተገርመውና ተመልሰው ለመጎብኘት ቃል ገብተው የሄዱት ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ባሟሉ ሆቴሎች በመስተናገዳቸው ነው ብለዋል፡፡
ሆቴሎች በአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የሚጫወቱት ሚና እጅግ የላቀ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ገዛኸኝ ሆቴል ማለት እንግዶች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ከአንድ ቀን በላይ ለአጭርና ለረዥም ጊዜ ሲንቀሳቀሱ ምግብ፣ መጠጥና መኝታ አገልግሎት እየሠጠ የሚያቆይ ተቋም ነው ብለዋል፡፡
እንግዶቻችንን ለማስተናገድ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟሉ 8,000 አልጋዎች ያላቸው 138 ሆቴሎች መዘጋጀታቸውን፣ ድንገት አልጋ ቢያንስ በማለት ቢሾፍቱ ሄደው መጠባበቂያ መያዛቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ከፍተኛ የደህንነት ጥንቃቄ የሚደረግላቸው ቪአይፒ የአገር መሪዎችና ም/ትል ፕሬዚዳንቶች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ የተባቡት መንግሥታት (ተመድ) መሪዎች፣ የተለያዩ የኤጀንሲ ኃላፊዎች፣ የቢዝነስ ኩባንያ ባለቤቶች …. አንዳች ነገር ሳይጓደል በብቃት ማስተናገድ፣ ኢትዮጵያ እያደገች ነው የሚለውን በተጨባጭና በተግባር የመሰከረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እኛ የምናየው ሆቴሎች፣ ሬስቶንቶች … ምን ያህል ገቢ አገኙ የሚለውን ሳይሆን አጠቃላይ ገጽታውን ነው፡፡ አንድ ሰው በአገራችን ውሎ ሲያድር በቀን 234 ዶላር ወጪ ያደርጋል ተብሎ ይገመታል፡፡ ለእንግዶቹ መኝታ ተይዟል፣ ሬስቶራንቶች ምግብ አቅርበዋል፣ ሻይ፣ ቡና ማኪያቶ፣ ቢራ፣ ዊስኪ፣ … ተጠጥቷል፡፡ የምሽት ቤቶች ተጎብኝተዋል፤ አየር መንገዶች፣ ባንኮች… አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ የተጓጓዙባቸው መኪኖች ቤንዚን ቀድተዋል፣ የስጦታ ዕቃዎች ተገዝተዋል፡፡ ከተማ ተጎብኝቷል፣ በአጠቃላይ ከአምራች ገበሬው እስከ የበሰለ ምግብ አቅራቢው በእያንዳንዱ ዘርፍ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ይህ ሁሉ የገንዘብ እንቅስቃሴ ነው በኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና የሚጫወተው፡፡
ለዚህ ሁሉ የሆቴሎች መኖር እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ሆቴሎች በአንድ ጊዜ ብዙ ህዝብ የማስተናገድ ልምድ አግኝተዋል፡፡ እኛም አገሪቷ ያላትን አቅም አውቀንበታል፡፡ ምክንያቱም እነዚህን ሁሉ እንግዶች የሚያስተናግድ ሆቴል ባይኖር ስብሰባው እዚህ ባልተካሄደ፣ እንግዶችም ባልመጡ ነበር፣ … በማለት አስረድተዋል፡፡
ከ24 ዓመት በፊት በመላ አገሪቷ 51 ሆቴሎች ብቻ እንደ ነበሩ ያስታወሱት አቶ ገዛኸኝ፤ በአራቱም የአገሪቷ ማዕዘኖች ግዮን ሆቴሎች፣ በቀለ ሞላ፣ ኢትዮጵያ፣ ዋቢ ሸበሌ፣ ራስ ሆቴል፣ ሐራምቤ፣ ዲ አፍሪክ፣ ጣይቱ፣ መርካቶ አካባቢ ደግሞ አስፋው ተክሌ፣ የምስራች፣ ምዕራብ፣ አስፋ ወሰን … ብቻ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ ከ21 ሺህ በላይ መኝታ ያላቸው 621 ሆቴሎች አሉ፡፡ ይህም በአዲስ አበባና በክልሎች እየተሠሩ ያሉትን እንደማይጨምር ተናግረዋል፡፡
በዚህ ሳምንት መጨረሻ የአረብ - አፍሪካ የፓርላማና የቢዝነስ ፎረም ይደረጋል፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት እነ ኦባማ የሚሳተፉበት የመሪዎች ጉባኤ ይካሄዳል፡፡
 ቀጥሎም እስከ 10ሺህ የሚደርሱ ዲያስፖራዎች ይመጣሉ፡፡ የኮንፈረንስ ቱሪዝምን በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በክልል ከተሞችም ለማዘጋጀት ታቅዷል፡፡ ባህርዳር ተፈትናለች፡፡ ሀዋሳና ሌሎችም ከተሞች ዓለም አቀፍ ስብሰባ የማካሄድ አቅም እንዳላቸው በመረጋገጡ በእነዚህም ከተሞች ጉባኤዎች ይካሄዳሉ ሲሉ ገልፀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ በዚህ ወር ይገለጻል ቢባልም እስካሁንም ምንም የለም፡፡ ለምን ተብለው የተጠየቁት አቶ ገዛኸኝ፤ “ምደባውን በብቸኝነት የሚያካሂዱት ከዓለም ቱሪስት ድርጅት የመጡ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ እስካሁን ድረስ በ1ኛው ዙር የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ አልቋል፡፡ አሁን መዳቢዎቹ ለእረፍት ወደ አገራቸው ሄደዋል፡፡ ለ2ኛ ዙር ሲመጡ እስካሁን የሰሩትን ተረክበን ለሚዲያም ሆነ ለየሆቴሎቹ እናስታውቃለን፡፡ ያኔ “የተሰጠኝ ደረጃ አይመጥነኝም፣ አልቀበልም” የሚል ሆቴል ካለ ቅሬታ ማቅረቢያ ደንብና ሥነ - ሥርዓት ስላለ እንደገና ይታይለታል በማለት አቶ ገዛኸኝ አስረድተዋል፡፡

Read 3503 times