Monday, 27 July 2015 10:05

የመሬት ሊዝ ዋጋ እየናረ ነው ተባለ

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(8 votes)

* መንግሥት የመሬት አቅርቦት በመጨመር ዋጋውን አረጋጋለሁ ብሏል
              * ከሊዝና ሌሎች ገቢዎች ከ1.6 ቢ. ብር በላይ ተሰብስቧል
                          
        የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ሊዝ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ መምጣቱን የሚናገሩ አንዳንድ የመዲናዋ ነዋሪዎች፤ ሁኔታው መፍትሄ ካልተበጀለት ከጥቂት ባለፀጐች በቀር መሬት ማግኘት የማይታለም ይሆናል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ፤ የመሬት አቅርቦቱን በመጨመር የሊዝ ዋጋን አረጋጋለሁ ብሏል፡፡
የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ፤ የሊዝ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱን አምኖ፣ ችግሩን ለመፍታት በዘንድሮ በጀት ዓመት የመሬት አቅርቦቱን ከ44 ሄከታር ወደ 60 ሄክታር እንደሚያሳድግ አስታውቋል፡፡
ባለፈው ህዳር ወር በተካሄደው 11ኛው ዙር የሊዝ ጨረታ፣ መርካቶ አካባቢ ለቀረበው 449 ካ.ሜ ቦታ፣ ዝዋይ ኢንተርናሽናል ግሩፕ የተባለ ተጫራች 305 ሺ ብር በማቅረብ በአዲስ የዋጋ ክብረወሰን ጨረታውን ሲያሸንፍ፣ ሁለተኛው ተጫራች ደግሞ 268 ሺ ብር ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ጉዳዩም በፓርላማ የመወያያ አጀንዳ እስከመሆን ደርሶ ነበር፡፡
ሆኖም ባለፈው ሳምንት በተከፈተው 15ኛው ዙር የሊዝ ጨረታ፣ አሸናፊው ድርጅት መሬቱን በወቅቱ ሳይረከብ በመቅረቱ፣ ለጨረታ ማስረከቢያ ያስያዘው 118ሺ 805 ብር ለመንግስት ገቢ ተደርጐ መሬቱ በድጋሚ ለጨረታ ቀርቧል፡፡
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፤ የሊዝ ዋጋ ከመጠን በላይ እንዲያሻቅብ ያደረገው የሊዝ መሬት አቅርቦት አናሳ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ መንግሥት ለጉዳዩ እልባት ካላበጀለት የዋጋ መናሩ እየቀጠለ ሄዶ መሬት የጥቂት ባለሃብቶች እንዳይሆን እንሰጋለን ብለዋል - አስተያየት ሰጪዎቹ፡፡
የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች የስራ ሂደት መሪ አቶ ማርቆስ አለማየሁ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሊዝ ለማቅረብ የታቀደው መሬት 44 ሄክታር ቢሆንም የቀረበው ግን 58 ሄክታር ነው ብለዋል፡፡ በአዲሱ የበጀት ዓመትም የሊዝ መሬት አቅርቦት ወደ 60 ሄክታር እንደሚያድግ ሃላፊው ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል መንግስት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከሊዝ ጨረታ አሸናፊዎች ከ549.3 ሚሊዮን ብር በላይ ለማግኘት አቅዶ፣ ከ639 ሚሊዮን ብር በላይ በማስገባት የእቅዱን 116 በመቶ እንዳከናወነ አስታውቋል፡፡ ከእቅድ በላይ የተገኘው ስኬት የዋጋ ንረቱ ውጤት አይደለም ወይ? ተብለው የተጠየቁት አቶ ማርቆስ ሲመልሱ፤ መንግስት የመሬት ዋጋ እንዲንር ፍላጐት እንደሌለው ገልፀው፤ ይልቁንም በመሬቱ ላይ በሚሰራው ኢንቨስትመንትና በሚፈሰው መዋዕለ ንዋይ በሚገኘው ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን በመፈለጉ፣ የሊዝ መሬት የመነሻ ዋጋ በማስፋፊያ ከ191 እስከ 355 ብር፤ በሽግግር ዞን ከ555 እስከ 1035 ብር እንዲሁም በማእከላዊ ንግድ ቀጠና አካባቢዎች ከ894 እስከ 1686 ብር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ቢሮው በበጀት ዓመቱ ከመሬት ሊዝና ከልዩ ልዩ ገቢዎች በአጠቃላይ ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡

Read 5145 times