Saturday, 18 July 2015 11:44

የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ከፍተኛ የጦር መሪዎችን አባረሩ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ባለፈው ግንቦት በምርጫ አሸንፈው ስልጣን የያዙት አዲሱ የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ፣ አሸባሪውን ቡድን ቦኮ ሃራም ለመደምሰስ የያዙትን ቀዳሚ እቅዳቸውን በአግባቡ ለማሳካት በሚል የቀድሞ የአገሪቱ የምድር ጦር፣ የባህር ሃይል፣ የአየር ሃይልና የመከላከያ መሪዎችን ከስልጣናቸው ማባረራቸውን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን ባለፉት ስድስት አመታት በአገሪቱ ሰሜን ምስራቃዊ አካባቢዎች 13ሺህ ያህል ዜጎችን ለህልፈተ ህይወት በዳረገውና 1.5 ሚሊዮን ዜጎችን ባፈናቀለው ቦኮ ሃራም ላይ ተገቢ እርምጃ አልወሰዱም በሚል በስፋት ሲወቀሱ እንደቆዩ ያስታወሰው ዘገባው፣ አዲሱ ፕሬዚዳንት ቡሃሪ የሽብር ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውንና የጦር መሪዎችን ማባረራቸውም የዕቅዳቸው አንዱ አካል መሆኑን ገልጿል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከስልጣናቸው ያባረሯቸው የጦር መሪዎች፡- ማርሻል አሌክስ ባዴህ፣ ሜጀር ጄኔራል ኬንዝ ሚናማህ፣ ሪር አድሚራል ኡስማን ጂብሪንና ምክትል ማርሻል አዴሶላ አሞሱ ናቸው ተብሏል፡፡
በምርጫው አሸንፈው ስልጣን ከያዙ፣ የመጀመሪያ ተልዕኳቸው የሚያደርጉት ቦኮ ሃራምን መደምሰስ እንደሆነ ሲገልጹ የነበሩት ቡሃሪ፣ ግንቦት ወር ላይ ስልጣን ከተረከቡ በኋላ፣ የአገሪቱን የመከላከያ ዕዝ መቀመጫ የአሸባሪ ቡድኑ መፈጠሪያ ናት ወደምትባለው ሜዱጉሪ ማዛወራቸውንና፣ ቡኮሃራምን ለመደምሰስ ያለመውን የአገራት ጥምር ሃይል ማዘዣ ጣቢያም በቻድ መዲና ጃሜና ማቋቋማቸውንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡

Read 1187 times