Print this page
Saturday, 18 July 2015 11:20

“ጓደኛ አታሳጣኝ…”“ጓደኛ አታሳጣኝ…”“ጓደኛ አታሳጣኝ…”

Written by 
Rate this item
(8 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ኢድ ሙባረክ!
ሰውየው ጓደኛው ዘንድ ስልክ ደውሎ እንዲህ ይለዋል፡፡ “ምክር ከፈለግህ የጽሁፍ መልእክት ላክልኝ፣ ጓደኛ ከፈለግህ ደውልልኝ፣ እኔን ከፈለግኸኝ ወደ እኔ ና…ገንዘብ ከፈለግህ ግን የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም…” ብሎ ዘጋው፡፡
ስሙኝማ…ጓደኝነት፣ ወዳጅነት ምነዋ እንዲህ ቅጡን አጣ! የምትሰሙት ሁሉ አገር ታምሶ ወዳጅነቶች… ወደ ደመኛ ጠላቶች ስለተለወጡ ‘ቤስት ፍሬንዶች’… ምናምን ሺህ ብር አብሮ አደጉ ስለካደው ምስኪን…ምን አለፋችሁ… “ዓለም የትያትር መድረክ ናት…” የሚለው ላይ…አለ አይደል…ለእኛ አገር “…ያውም የትራጄዲ!” የሚለውን ልትጨምሩ ምንም አይቀራችሁ፡፡
ከምር የሆነ ነገር ነው፡፡ ሰውየው ለሁለት ወር ወርክሾፕ ወደ አንድ አፍሪካ አገር ሄዶላችኋል፡፡ ቤት ውስጥ ከሚስቱ በስተቀር ሌላ ሰው የለም፡፡ እናላችሁ…¸የልብ ጓደኛ ሆዬ የወዳጁ ሚስት ብቻዋን እንዳትሆን በማለት መለስ ቀለስ ሲል ‘አንዱ ነገር ወደ ሌላ እየመራ’ ተቀምጠው የሚያወሩ የነበሩት ጋደም ብለው ‘ወደ መወያየት’ ጀመሩላችሁ፡፡
ሰውየው ተመልሶ ሲመጣ ማን እንደነገረው ሳይታወቅ ጉዱን ይሰማል፡፡ ምንም ሳያቅማማም ፍቺ ጠይቋል አሉ፡፡ የተሻሻለ ዘመን… እንደ በፊቱ ቢሆን ለየጓደኛው እየደወለ… “ስማ አንድ ማካሮቭ ወይም ኮልት ሽጉጥ ምናምን የሚገኝበት ታውቃለህ…” ምናምን ይል ነበር፡፡ እኔ የምለው… እንትናዬዎች ሰይፍ ማማዘዝ ተዉ ማለት ነው!  ቂ…ቂ…ቂ…
ስሙኝማ…በፊት እኮ እንትናዬን ለጓደኛ በአደራ መስጠት ይህን ያህል ስጋት አልነበረውም። እንደውም አንዱ የታማኝ ጓደኛ መገለጫ የዚህን አይነት አደራ መጠበቅ ነው፡፡ የድሮ የልብ ጓደኛ እኮ ጓደኛው ርቆ ሲሄድ እንትናዬውን በአደራ ይጠብቅ ነበር፣ አሁን ግን ጓደኛ በበር ሲወጣ ‘ቤስት ፍሬንድ’ በመስኮት ሳይሆን በዛው በር የሚገባበት ዘመን ነው።
እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ፡፡ ሁለቱ ጓደኛሞች ሲጠጡ አምሽተው ዘጠነኛው ደመና ላይ ወጥተዋል፡፡ እናማ… በጨዋታ መሀል ምን ይላል…
“ስማ፣ አንድ የምነግርህ ነገር አለ፡፡ ግን ቅር አይልህም አይደል!”
“ለምንድነው ቅር የሚለኝ! “ስለ ሰው ቀድጄ ልልበሰው…” አይነት ነገር ይናገራል፡፡ ጓደኝየውም…
“ይሄን ስነግርህ አዝናለሁ፡፡ ሚስትህ ግን ለትዳሯ ታማኝ አይደለችም፣” ይላል፡፡ ሰውየው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“እሷ ሴትዮ በቃ አትሻሻልም! አንተንም ሸወደችህ ማለት ነው?” ብሎት እርፍ፡፡
ቤንጃሚን ፍራንክሊን የሚሉት ሰው… “ሦስት ታማኝ ጓደኞች አሉ፡፡ ያረጀች ሚስት፣ ያረጀ ውሻና፣ በእጅ ያለ ገንዘብ…” ብሏል አሉ ፡፡
ታዲያላችሁ…“የልብ ጓደኛዬ፣ የክፉ ቀኔ…” ምናምን ማለት እያስቸገረ ያለበት ዘመን ነው፡፡
ዘንድሮ ‘ጉድና ጅራት’ ወደኋላ መሆኑ ቀርቶ ፊት ለፊት በሆነበት ዘመን የጥንት የልብ ጓደኛ ማግኘት ደስ ይላል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ የሚወራ አይጠፋም። እናላችሁ… እንዲሁ በየኮብልስቶኑ ላይ ዘንበል፣ ዘንበል ስትሉ የጥንት ጓደኛችሁን ታገኛላችሁ፡፡ እናላችሁ ነገርዬው ይሄኔ ነው፡፡
“አንተ! የሚገርም ነው፡፡ አንድ ሀያ ምናምን ዓመት አይሆነንም!” ምናምን እያላችሁ በሰከንድ አሥራ ስምንት ጥይት ትለቃላችሁ፡፡
እሱ ሆዬ… አለ አይደል… መጀመሪያ ትኩር ብሎ ያያችኋል፡፡ ለማስታወስ ግራ የተጋባ ይመስል መልስ ሳይሰጥ ያያችኋል፡፡ እናንተም… “ረሳሁህ እንዳትል…” አይነት ነገር ትሉና “ኮከበ ጽባሀ ሁለተኛ ደረጃ…” ምናምን እያላችሁ መዝገብ መግለጥ ትጀምራላችሁ። አሁንም እንደነገሩ ያያችኋል፡፡ ብዙ ቆይቶ ትዝ ይበለውም፣ አይበለውም…“ኦ!” ይልና ከእጁ ሦስቷን ጣት ያቀረብላችኋል፡፡ እመኑኝ…ይሄ የጥንት ጓደኛችሁ ወይ ገንዘብ አግኝቷል፣ ወይ ወንበር አግኝቷል፡፡ ዘንድሮ ያስቸገሩን ሁለት ነገሮች ቢኖሩ ገንዘብና ወንበር ናቸው፡፡
እናላችሁ… “የጥንት ጓደኛዬ፣ አብረን እኮ ስንትና ስንት አድቬንቸር አሳልፈናል!” አይነት ትዝታ እየጠፋ ነው፡፡
የዘንድሮ ጓደኝነት ደግሞ የሚመሰረተው በአድቬንቸር ምናምን ሳይሆን በገበያው ሁኔታ ነው፡፡ ለጓደኝነት ለመመረጥ ‘በገበያው ላይ’ ያላችሁ ዋጋ መታወቅ አለበት፡፡ እንደ አክስዮን ገበያው ‘ዋጋችሁ’ ዝቅ ሲል “መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ…” ትባላላችሁ፡፡
እናላችሁ…የዘንድሮ ‘ቤስት ፍሬንድነት’ አንጻራዊ ነው፡፡ በቃ ወረቀት ላይ ያልሰፈረ ኮንትራት በሉት፡፡
ሰውየው ምን አለ አሉ መሰላችሁ… “ዕድሜው ከ30 ዓመት በላይ የሆነ ሰውን ምን ያህል ጓደኛ እንዳለው ጠይቀው፡፡ ከአሥር በላይ ብሎ ከመለሰልህ የቆጠረው ጓደኞቹን ሳይሆን የሥራ ባልደረቦቹን ነው፡፡” እንዴት ሸጋ አባባል ነች!
ስሙኝማ…የልብ ጓደኞች የምንባለው እኰ ድሮ የምናወራውና አሁን የምናወራው ተለውጧል፡፡ በፊት እኮ…“ስማ ያቺ የኮተቤዋን፣ ያቺ እንኳን የቀበሌ ድንኳን በሚያክለው ቀሚሷ ስር ሁለት ሱሪ ትለብስ የነበረችው… አይተኸት ታውቃለህ!” ሲባል… “የእኔ ጌታ የሆነ ባለጊዜ ጠብ አድርጋ አሁን በአጠገቧ እንኳን አታልፍም አሉ…” አይነት የጋራ አጀንዳ ነበር።
ደግሞላችሁ… ገርልዬዋን የእንትን ሰፈር ልጆች ለክፈዋት ስለተካሄደው ክትክት…አንድ ትሪ ድንች ለሦስት ተበልቶ ስለማይጠገብበት…“አንድ በራድ” ሲባል የቀዘቀዘ ሻይ ስላቀረበው አስተናጋጅ… አንድ ብር ይዞ ባሻ ወልዴ ችሎት ብቅ ብሎ “ሀምሳ ሳንቲም ጨምር…” ተብሎ ሲሮጥ ስለመጣው ጩኒ… መአት የሚወራ ነገር ነበር፡፡
ዘንድሮ ግን ድሮ ምናምን ቀርቶ ከአሥራ እምስት ዓመት በኋላ ስትገናኙ የመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር “አሁን ይቺ አገር ነች!” ምናምን አይነት ብሶት ነው። ምን አለፋችሁ…በቅጡ እንኳን የወዳጅነት ሰላምታ ሳንለዋወጥ… “ስማ በሻይ ጠቅሰን የምንበላው ዳቦ እንኳን እንዲህ ይወደድ!” እንባባላለን፡፡
እግረ መንገዴን የሆነች ያነበብኳት ነገር ትዝ አለችኝማ…
እሱና እሷ ተጋብተው የሠርጉ ስነ ስርአት ካለፈ በኋላ ሚስት አንድ መለስተኛ ሳጥን አልጋዋ አጠገብ ታስቀምጣለች፡፡ ለባሏም በምንም አይነት ሳጥኑን እንዳይከፍት ታስጠነቅቀዋለች፡፡ አርባ ዓመታት አለፉ፡፡ አንድ ቀንም አቶ ባል ነገሩ ይከነክነውና ሚስቱ ሳታውቅ ሳጥኑን ይከፍተዋል፡፡ ውስጡም ሦስት ባዶ የቢራ ጠርሙሶችና አንድ መቶ አርባ ሺህ ዶላር ያገኛል፡፡ ማታም ባል ሚስቱን “የእኔ ውድ አዝናለሁ ግን ሳጥኑን ከፍቼ ነበር፡፡ ሦስቱ ባዶ የቢራ ጠርሙሶች ምንድናቸው?” ይላታል። ሚስትም…
“ከሌላ ወንድ ጋር በተኛሁ ቁጥር አንድ ቢራ እጨልጥና ባዶውን ጠርሙስ ሳጥኑ ውስጥ አስቀምጠዋለሁ፣” ትለዋለች፡፡
ባልየውም ትንሽ ያስብና ‘በአርባ ዓመት ሦስት ጊዜ ብቻ መማገጥ ምንም አይደለም’ ብሎ ራሱን ያሳምናል፡፡ ቀጥሎም…
“እሺ፣ የጠርሙሶቹስ ይሁን፡፡ አንድ መቶ አርባ ሺህ ዶላሩን ምን ስትይ አጠራቀምሽው?” ይላታል፡፡ ሚስት ምን ብትለው ጥሩ ነው…
“ሳጥኑ ሦስት ጠርሙስ ይዞ ተጨማሪ ጠርሙስ አላስገባ ሲለኝ ባዶ ጠርሙሶችን በገንዘብ እየለወጥኩ ያስቀመጥኩት ነው…” ብላው አረፈች፡፡
ሰውየው የተዋሰውን የጓደኛውን መኪና ያጋጫል፡፡ ማታ ቤት ሲገባ ሚስቱ…
“መኪናው መገጨቱን ጓደኛህ ሲያይ ምን አለህ?” ትለዋለች፡፡
“ስድብ ስድቡን ትቼ ሌላውን ብቻ ልንገርሽ?”
“አዎ፣ ስድቡን ተወውና ሌላውን ንገረኝ፡፡”
“እንግዲያው ምንም ነገር አላለም፡፡”
ዘንድሮም ‘ስድብ፣ ስድቡን’ ስናወጣ ባዶ የሚሆኑ ንግግሮች፣ መግለጫዎች፣ ማብራሪያዎች መአት ናቸው፡፡
እናላችሁ… “ጓደኛ አታሳጣኝ…” ማለት ዘንድሮ ነው፡፡
እውነተኛ የልብ ጓደኞችን ያብዛላችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 6204 times
Administrator

Latest from Administrator