Saturday, 18 July 2015 11:16

በግል የበረራ አገልግሎት ላይ የተቀመጠው የወንበር ገደብ እንዲነሳ ተጠየቀ

Written by 
Rate this item
(23 votes)

ፎከር - 50 ለመጨረሻ ጊዜ የተመረተው ከ20 ዓመት በፊት ነው

   በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፤ ከ50 ሰው በላይ እንዳያጓጉዙ የተጣለባቸው ገደብ ሊያሰራቸው እንዳልቻለ ጠቁመው ገደቡ እንዲነሳላቸው ጠየቁ፡፡  
የበረራ አገልግሎት ሰጪዎቹ፤ ከዚህ ቀደም የወንበር ገደቡን ጨምሮ የጋራዥ ቦታና ሌሎች በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ለስራቸው መሰናክል እንደሆኑባቸው ሲገልፁ ቆይተዋል፡፡
የናሽናል ኤርዌይስ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ካፒቴን አበራ ለሚ ለአዲስ አድማስ  እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት ከ79 ሰው በታች የሚጭን አውሮፕላን ገበያ ላይ የለም፡፡ በተለምዶ ፎከር - 50 በሚል የሚጠሩትና 50 ሰዎችን የሚጭኑት አውሮፕላኖች ለመጨረሻ ጊዜ የተመረቱት ከ20 ዓመታት በፊት ነው፡፡
“79 ሰው የሚጭነውን አውሮፕላን ገዝቶ 50 ሰው መጫን ኪሳራ ነው” ያሉት ካፒቴኑ፤ የወንበር ገደቡ ሊያሰራን ስላልቻለ ሊነሳ የሚችልበት መንገድ ቢኖር የግል የአቬሽን ዘርፍን ወደ አንድ ደረጃ ያሳድገዋል ብለዋል፡፡
በቅርቡ ኢትዮጵያ የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ ተብላ መመረጧን ያስታወሱት ካፒቴን አበራ፤ በወንበር ገደቡ ምክንያት ወደ ሃገሪቱ በብዛት እየጐረፉ ያሉትን ቱሪስቶች ለማስተናገድ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ ገደቡ እንዲነሳ በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰውም፣ ይነሳል እየተባለ ሶስት ዓመታት ያለ ውጤት ማለፉን ገልፀዋል፡፡
ከወንበር ገደቡ በተጨማሪም በቦታ ችግር የተነሳ፣ የሰው ሃይሉ እያለ አውሮፕላን የሚያሰሩት ደቡብ አፍሪካ ድረስ በመሄድ መሆኑን ጠቁመው፤ ይሄም ነዳጅን ጨምሮ ለተለያዩ ወጪዎች እየዳረጋቸው እንደሆነ ካፒቴኑ ገልፀዋል፡፡
በአቬሽን ዘርፍ ለረዥም ዓመታት ያገለገሉት አቶ ስንታየሁ በቀለ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በየትኛውም አገር የወንበር ገደብ እንደሌለ ገልፀው፣ የገደቡ መነሳት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እያደገች ያለች አገር በመሆኗ የኢኮኖሚ እድገቷን ተከትሎ የቱሪስት ፍሰቱም ስለሚጨምር ቱሪስት የማስተናገድ አቅሟን ልትጨምር እንደሚገባ አቶ ስንታየሁ ያስረዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ በአቬሽን ኢንዱስትሪው መልካም ስም ከተቀዳጁ አገራት መካከል አንዷ በመሆኗ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ፈትቶ፣ የግሉን ዘርፍ በመደገፍ የአቬሽን ዘርፉን ማሳደግ እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
የወንበር ገደብ መነሳቱ የተሻሉ አውሮፕላኖችን ለማስገባት እድል ስለሚፈጥር ቱሪስቶች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ያሉት አቶ ስንታየሁ፤ ቱሪስቶቹ በትናንሽ /ቻርተር/  አውሮፕላኖች የሚጠየቁት ከፍተኛ ክፍያም እንደሚቀንስላቸው አብራርተዋል፡፡

Read 4511 times