Saturday, 18 July 2015 10:55

የውጭ ብድር እዳ ኢትዮጵያን ያሰጋታል ተባለ

Written by 
Rate this item
(15 votes)

• ስጋት ከተጋረጠባቸው 14 ሀገራት ውስጥ ተካታለች
• ሴኔጋል፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ሞዛምቢክ በዕዳ ተዘፍቀዋል

      የውጪ ብድር እዳ ኢኮኖሚያቸውን ሊፈታተን ይችላል የሚል ስጋት ከተጋረጠባቸው 14 የአለም
አገራት ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ዘ ጋርዲያን የአለም ባንክን ሪፖርት ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የብድር እዳ እንዳለባት የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርቷ 45 በመቶ የሚሆነው ከብድር የተገኘ ገንዘብ እንደሆነ ጠቁሞ፤ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ይህ አኃዝ ወደ 65 በመቶ ሊያሻቅብ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ ከለጋሽ ተቋማትና ሃገራት የሚገኝ ብድር ለአጠቃላይ አገራዊ ምርት ያለው አስተዋጽኦ ከ30 በመቶ በላይ ከሆነ ሀገራት ወደ ከፍተኛ የእዳ ቀውስ እያመሩ መሆኑን እንደሚያመለክት የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ኢትዮጵያም በዚህ የአደጋ ቀጠና በከፍተኛ ደረጃ ከገቡ 14 የአለም  ሀገሮች መካከል ተጠቅሣለች።  ከፍተኛ የውጭ እዳ ውስጥ ተዘፍቀዋል የተባሉት 14 ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ቡታን፣ ኬፕ ቨርዲ፣ ዶሚኒካ፣ ጋና፣ ላኦስ፣ ሞሪታኒያ፣ ሞንጐሊያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሣሞኣ፣ ሣኦቶሜ ፕሪንቼቤ፣ ሴኔጋል፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል 24 የአለም ሀገሮች የውጭ እዳቸው በሚያሰጋ ደረጃ እየጨመረና ወደ አደጋው ቀጠናም እየተንደረደሩ ነው በሚል ተጠቅሰዋል፡፡
አንዳንድ በአስጊ ደረጃ እዳ ውስጥ ተዘፍቀዋል የተባሉ ሀገራት፣ የተበደሩትን ገንዘብ ለተገቢው
አላማ መጠቀም አለመቻላቸው ለቀውስ እንደዳረጋቸው በሪፖርቱ የተጠቆመ ሲሆን በዚህ ረገድ ጋና ምሣሌነት ተጠቅሳለች፡፡ ሌሎችም አዋጭ የሆነ የብድር አመላለስ ስርአት ባለመከተላቸው የችግሩ ሠለባ እየሆኑ እንደመጡ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ እነዚህ ሀገራት ከዚህ እዳ የሚወጡበትን መንገድ ካላጤኑ ከፍተኛ ቀውስ ሊገጥማቸው ይችላል ብሏል፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ የግል ኩባንያዎችና መንግስታት አለም ባንክን ከመሳሰሉ አበዳሪ ተቋማት ከ2009 እ.ኤ.አ ጀምሮ በየአመቱ የሚበደሩት ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ነው ተብሏል፡፡ በ2013 እ.ኤ.አ የአለም ሀገራት አጠቃላይ የብድር መጠን 11.3 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን በ2014 13.8 እንዲሁም በዘንድሮው አመት 14.7 ትሪሊዮን ዶላር መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ 

Read 7222 times