Saturday, 18 July 2015 10:38

አየር መንገድ ለስብሰባ የመጡ እንግዶችን አገር እያስጎበኘ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(16 votes)

     የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ3ኛው ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ኮንፈረንስ ላይ ለመካፈል ለመጡ ንግዶች የአገር ውስጥ ጉብኝት ልዩ ፓኬጅ አዘጋጅቶ የቱሪስት መስህብ የሆኑ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ እያደረገ ነው፡፡ አየር መንገዱ ፓኬጁን ያዘጋጀው ዩኔስኮ እውቅና ሰጥቷቸው በዓለም ቅርስነት የመዘገባቸውንና የአውሮፓ የቱሪዝምና ንግድ ም/ቤት ጠቅላላ ጉባኤ ኢትዮጵያን የ2015 የዓለም ምርጥ የባህላዊ ቱሪዝም መዳረሻ በማለት የመረጠበትን ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦች ለኮንፈረንስ የመጡ እንግዶች እንዲጎበኙት በማድረግ ቱሪስቶችን ለመሳብና እንዲሁም ለአገር ገጽታ
ግንባታና ገቢ ማግኛ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ልዩ ፓኬጆቹ የሰሜንና የደቡብ የአገሪቷ የቱሪስት መስህቦችን ያቀፉ ናቸው፡፡ የሰሜኖቹ ላሊበላ ደርሶ መልስ፣ ባህርዳርና ጎንደር፣ አክሱምና ላሊበላ ሲሆኑ የደቡቦቹ አርባ ምንጭ ጂንካ ሙርሲ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ልዩ የፓኬጅ የጉብኝት ዋጋ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በገዙት የቲኬት ዋጋ ላይ 100 ዶላር ብቻ የሚያስጨምር ነው፡፡ ለምሳሌ ለበዓል ጊዜ የተዘጋጀው ፓኬጅ ለ2 ቀን ላሊበላ ደርሶ መልስ ዋጋ 270  ዶላር ሲሆን በተጨማሪነት ለሚያዝ ዕቃ 39 ዶላር ያስጨምራል፡፡ ለፋይናንስ ጉባኤ ለመጡ እንግዶች የተዘጋጀው ልዩ ፓኬጅ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በገዙት ቲኬት ዋጋ ላይ አንድ ሰው 100 ዶላር መጨመር ብቻ ነው ያለበት፡፡ ጎብኚው ከላሊበላ ወደ አክሱም መሄድ ቢፈልግ የሚጨምረው
25 ዶላር ብቻ ነው፡፡ በበዓላት ጊዜ ፓኬጅ ለ2 ቀን ቆይታ አንድ ጎብኚ ለባህርዳር ደርሶ መልስ የሚከፍለው 412 ዶላር ሲሆን በተጨማሪነት ለሚይዘው አንድ ዕቃ 39 ዶላር ይጨምራል፡፡ ለባህርዳር -ጎንደር የ3 ቀን
ቆይታ ደርሶ መልስ አንድ ሰው 581፣ ለሚይዘው አንድ ተጨማሪ ዕቃ 99 ዶላር ይከፍላል፡፡ በሰሞኑ
ልዩ ፓኬጅ ባህርዳር - ጎንደር ደርሶ መልስ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ በገዛው ቲኬት ላይ 100 ዶላር ብቻ መጨመር ነው፡፡ በበዓላት ጊዜ ፓኬጅ ከአዲስ አበባ አክሱም፣ ከአክሱም - ላሊበላና ከላሊበላ አዲስ አበባ የ3 ቀን ቆይታ 457 ዶላር፣ በተጨማሪነት ለሚያዝ አንድ ዕቃ 55 ዲላር ይከፈል ነበር፡፡ ለጉባኤ ለመጡት
እንግዶች የተዘጋጀው ልዩ ፓኬጅ በቲኬቱ ላይ 100 ዶላር መጨመር ነው፡፡ አንድ እንግዳ አራቱንም ፓኬጆች መጠቀም ቢፈልግ፣ በ100 ዶላሩ ላይ ለየመዳረሻዎቹ 25 ዶላር በመጨመር በ200 ዶላር
አራቱንም ፓኬጅ መጎብኘት ይችላል፡፡ ከአዲስ አበባ - አርባ ምንጭ በአውሮፕላን፣ ከአርባ ምንጭ ጂንካ ሙርሲ - አርባ ምንጭ በመኪና እንዲሁም ከአርባ ምንጭ  - አዲስ አበባ ለሚደረግ የአውሮፕላን በረራ ለ3 ቀን ቆይታ ጉብኝት የሚከፈለው 1100 ዶላር፣ በተጨማሪነት ለሚያዝ አንድ ዕቃ 56 ዶላር ነበር፡፡
ለጉባኤው የመጡ እንግዶች የሚከፍሉት 100 ዶላርና ለመዳረሻው ተጨማሪ 25 ዶላር እንደሆነ ታውቋል፡፡

Read 10788 times