Saturday, 18 July 2015 10:16

ኢትዮጵያ በሃብት ከ184 አገራት 171ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(22 votes)

ከአፍሪካ 7ኛ ደረጃ ተሰጥቷታል (አፍሪካን ክራድል)

  ኢትዮጵያ በዓለም የሀብት ደረጃ ከ184 ሃገራት 171ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን የመንግስት ሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት “አፍሪካን ክራድል” የተሰኘ ድረገፅን ጠቅሶ ከአፍሪካ 10 ሀብታም ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ በ7ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ብሏል። የዓለም የሃብት ደረጃ አለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከ2009-2013 ሃገራት በየዓመቱ ያስመዘገቡትን አጠቃላይ የሃገር ውስጥ ምርት እድገት (GDP) መሰረት አድርጎ ያወጣው እንደሆነ ታውቋል፡፡ የዓለም ቁጥር 1 ሃብታም ሃገር የተባለችው ኳታር ስትሆን ሉክዘምበርግና ሲንጋፖር በ2ኛ እና 3ኛነት ደረጃ ይከተላሉ፡፡ ታላቋ ሃገር አሜሪካ ደግሞ በ7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ በዓለም ሃብታም ሃገራት ዝርዝር ሲሸልስ 38ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን ከአፍሪካ ሃገራት የ1ኛነት ደረጃ ይዛለች፡፡ ሲሸልሰን ተከትላ ኢኳቶሪያል ጊኒ ከዓለም በ40ኛ ደረጃ፣ ከአፍሪካ በ2ኛ
ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ከአፍሪካ ሃገራት በቀዳሚነት ከተሰለፉት መካከል ቦትስዋና፣ ጋቦን፣ ሞሪሽየስ፣ ሊቢያ፣ ደቡብ አፍሪካና ቱኒዚያ ይገኙበታል፡፡ በዓለም የሃብት ደረጃ፣ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሃገራት በ45ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ በእነ ደቡብ ሱዳን፣ ቻድ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሩዋንዳ እና ሴራሊዮንን በመሳሰሉ ሃገራት ተበልጣለች፡፡ በሌላ በኩል “አፍሪካ ክራድል” የተሰኘው ድረ ገፅ ያወጣው የአፍሪካ አገራት የሃብት ደረጃ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ካወጣው ዝርዝር ጋር እንደማይጣጣም ለማወቅ ተችሏል፡፡በ“አፍሪካ ክራድል” መረጃ መሰረት፤ ከአፍሪካ ሃገራት በሃብት 1ኛ ደረጃ የተሰጣት ደቡብ አፍሪካ ከ10 በላይ በሆኑ የአፍሪካ ሃገራት ተቀድማ በዓለም 80ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ጎረቤት አገር ኤርትራ ከዓለም 180ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን ላይቤሪያ 181ኛ፣ ቡሩንዲ 182ኛ፣ ዚምባቡዌ 183ኛ፣ ኮንጎ ኪንሻሣ 184ኛ ደረጃን በመያዝ በሃብት የመጨረሻዎቹ አገራት ሆነዋል፡፡ የ“አፍሪካን ክራድል” ጥናት የሃገራት አመታዊ ምርትን (GDP) መነሻ ያደረገ ሲሆን ደቡብ አፍሪካ በዓመት 595.7 ቢሊዮን ዶላር በማስመዝገብ 1ኛ ስትሆን፣ ግብፅ 551.4 ቢሊዮን ዶላር፣ ናይጄሪያ 478.8 ቢሊዮን ዶላር፣ አልጄሪያ 284.7 ቢሊዮን ዶላር፣ ሞሮኮ 180 ቢሊዮን ዶላር፣ ቱኒዚያ 108.4 ቢሊዮን ዶላር፣ ኢትዮጵያ 108.2 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ሱዳን 89.97 ቢሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ በማግኘት የአፍሪካ 10 ሀብታም ሃገራት ተብለዋል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ድረ - ገፁን ጠቅሶ ያስቀመጠው መረጃ ያመለክታል፡፡

Read 12591 times