Saturday, 18 July 2015 10:12

ፍሬ ከዛፉ ርቆ አይወድቅም!

Written by 
Rate this item
(22 votes)

አንዳንድ ተረት አንዴ ተነግሮ የማይበቃውና ሰዎች ተገርተው እስኪበቃቸው የሚተረት ይሆናል፡፡ የሚከተለው ተረት የእዛ ዓይነት ነው፡፡
አንድ ቤት ውስጥ አባት፣ እናትና ህፃን ልጅ ይኖራሉ፡፡
አንድ ቀን ማታ ህፃኑ በምን እንደከፋው አይታወቅም ክፉኛ ያለቅሳል።
አባት - “አንተ ልጅ ምን ሆንኩ ብለህ ነው የምታለቅሰው?” ይሉታል።
ልጅ ለቅሶውን ይቀጥላል፡፡
እናት - “ዝም በል ማሙሽ፡፡ ዝም ካልክ የማረግልህን አታቅም” አሉት በማባባል ቃና፡፡
ልጅ አሁንም ማልቀሱን ይቀጥላል፡፡
አባት ተናደዱና፤
“እንግዲህ ዝም ካላልክ ለጅቡ ነው የምሰጥህ!”
ልጅ አሁንም ያለቅሳል፡፡
እናት ይጨመሩና፤
“ዋ! ይሄንን በር ከፍቼ እወረውርሃለሁ!”
ለካ ቤት ውስጥ ይሄ ሁሉ ሲሆን አያ ጅቦ ውጪ ቆሞ ያዳምጥ ኖሯል።
ከአሁን አሁን ህፃኑን ይጥሉልኛል ብሎ ይጠብቃል፡፡
ቀስ በቀስ ልጁ ፀጥ አለ፡፡ ባልና ሚስት ራታቸውን በሉ፡፡ ልጁን አስተኙና ተቃቅፈው ተኙ፡፡
ጅቡ ቢጠብቅ፣ ቢጠብቅ ምንም የሚጣልለት ልጅ አላገኘም፡፡
በመጨረሻም፤ ወደ በሩ ጠጋ ብሎ፤
“ኧረ የልጁን ነገር ምን ወሰናችሁ?” አለ፡፡
ባለቤቶቹ በራቸውን ቆላልፈው ለጥ ብለዋል፡፡ አያ ጅቦ ጠብቆ ጠብቆ ሊነጋበት ሲል ወደ ጫካው ሄደ፡፡
*   *   *
በማስፈራራት ልጅን ማስተኛት አይቻልም፡፡ ልጁ የተከፋበትን ምክንያት ማወቅ እንጂ ማባበልም ጥቅም አይኖረውም፡፡ በአንፃሩ እንደ አያ ጅቦ የቀቢፀ ተስፋ ምኞት መመኘትም ራስን የባሰ ረሀብ ውስጥ መክተት ነው!
በሀገራችን የተመኘናቸው የነፃነት፣ የዲሞክራሲና የፍትህ ጥያቄዎች በዱላም በካሮትም (Carrot and stick እንዲሉ) እየተሞከሩ ረዥም ዕድሜ አሳልፈዋል፡፡ ዛሬም የጠራ ጐዳና ላይ አልወጡም፡፡ የተኙ ተኝተዋል፡፡ የሚያለቅሱ ያለቅሳሉ፡፡ እንደ አያ ጅቦ ደጅ የቀሩም ይቀራሉ።
“…አሁን የት ይገኛል፣ ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ፣ የባሰ ደንቆሮ”
የሚለውን የከበደ ሚካኤልን ግጥም ልብ ማለት ለሀገራችን በጣም ጠቃሚ ነው፡፡
አሁንም የህዝብን ብሶት እናዳምጥ፡፡ ዛሬም ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ቀና ልቦና ይስጠን፡፡ ሌላው ቀርቶ የዓለም መንግሥታት የሚያደርጉልንን ድጋፍ ለመቀበልም ቀና ልቡና ያስፈልጋል፡፡ መረጃዎችን፣ አገራችንን የሚመለከቱ ጉዳዮችን እናውቅ ዘንድ ቀና ልቡና አለንና በወጉ የማወቅ መብታችን ሊጠበቅ ይገባል፡፡
የደረስንበት እንዳይርቅ፣ ከእጃችን ያለው እንዳይፈለቀቅ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ዛሬም መደማመጥ፣ መቻቻልና ዛሬም ረብ ያለው የፖለቲካ አቅጣጫና ተጨባጭ የሀገር ጉዳይን ማንሳት ይጠበቅብናል። የአሸነፈም፣ የተሸነፈም ሀገር ለምንላት የጋራ ቤት ምን ዓይነት አስተዋጽኦ እያደረግሁ ነው ብሎ መጠየቅ አለብን፡፡
ማንም ቢሆን ማን ምርቱ ይታወቃል፡፡ መንገዱም ይለያል፡፡ መሸሸግ የማይቻሉ በርካታ ነገሮች መኖራቸውን ህዝብ ያውቃል፡፡ ምክንያቱም ፍሬ ከዛፉ ርቆ አይወድም።

Read 5571 times