Saturday, 11 July 2015 12:38

ዓለም በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ወደ ምስራቅ አፍሪካ እያማተረ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

      በዓለም የጨርቃጨርቅ ምርት ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የቻይና ገበያ ዋጋ እየተወደደ ስለሆነ ዓለም አቀፍ ገዢዎች ወደ ምሥራቅ አፍሪካ አገሮች እያማተሩ ነው ተባለ፡፡
የሕንድና የአፍሪካን ንግድና ኢንቨስትመንት ለ5 ዓመት ለመደገፍ በዓለም ንግድ ማዕከል የተቋቋመው ፕሮጀክት supporting Indian trade and Investment SITA (ሲታ) ከጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ባለሀብቶችና ከሚመለከታቸው የዘርፉ አካላት ጋር በሂልተን ሆቴል ባዘጋጀው የሁለት ቀን የምክክር ወርክሾፕ አለም አቀፍ የጨርቃጨርቅ ገዢዎች  ፊታቸውን ወደ ምስራቅ አፍሪካ አገሮች ማዞር ለኢትዮጵያ ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን አመልክቷል፡፡
የወርክሾፑ ዓላማ በሕንድና በአምስት የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች (ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛንያና ሩዋንዳ) መካከል የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ማሳለጥ እንደሆነ የጠቀሱት የዓለም ንግድ ማዕከል የፕሮጀክት ልማት (ሲታ) አማካሪ ሚስ ሐና ቡሄር፣ ከአንድ ወር በፊት ከጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላት ጋር በዘርፉ ስላሉ ችግሮችና አመቺ ሁኔታዎች ዙሪያ ያደረጉት ምክክር ቀጣይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሚስ ቡሄር፤ በመጀመሪያም የምክክር ወርክሾፕ የተነሱ ችግሮችና አመቺ ሁኔታዎች ተንትኖ በማዳበር፣ ምርታማነት ተሻሽሎ፣ የሕንድና የዓለም ገበያ በሚፈልጉት መጠንና የጥራት ደረጃ የጨርቃጨርቅ ምርቶችን ማቅረብ የሕንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት የሚያደርጉበትን የተግባር መርሐ ግብር ረቂቅ ይቀረፃል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ለዓለም ገበያ ማበርከት የምትችለው ትልቅ አቅም እንዳላት በመታመኑ ነው በዚህ ዘርፍ እንድትካተት የተደረገው ያሉት ሚስ ቡሄር፣ ሠራተኞች የሙያ ሥልጠና ካገኙ፣ የአመራረትና የማኔጅመንት ሥልጠና ከተሰጠ፣ ብክነት ከተወገደ፣ ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጀ ያለው ምርት በአነስተኛ ወጪ ያለማቋረጥ ማቅረብ ከተቻለ…ኢትዮጵያ ከዘርፉ ከፍተኛ ተጠቃሚ እንደምትሆን አስረድተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ፣ ለኢትዮጵያ በሥራ ፈጠራ ከሚያስገኝው ጥቅም በተጨማሪ ሥልጠና ይሰጣል፣ የእውቀት ሽግግር እንዴት እንደሚመጣ፣ ዘመናዊ መሳሪያዎችና አዳዲስ ገበያዎች እንዴት ማግኘት እንደሚቻል፣ በአጠቃላይ የቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል እንጂ ገንዘብ እንደማይሰጥ ታውቋል፡፡
የዓለም ንግድ ማዕከል የጥጥ፣ የጨርቃጨርቅና የልብስ ዘርፍ ተፎካካሪነት የፕሮግራም ኦፊሰር ቅድስት ሞገስ ተክሉ በበኩላቸው፤ ቻይና ከምንም (ባዶ) ተነስታ በ30 ዓመት ውስጥ በዘርፉ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሷን ጠቅሰው፣ ኢትዮጵያ ጀማሪ አይደለችም፤ አነስተኛ ቢሆንም የጨርቃጨርቅ ምርቶች ኤክስፖርት እያደረገች ነው፡፡ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የሙያ ሥልጠናና አስፈላጊ ማሻሻያዎች…ካደረገች በዘርፉ ከፍተኛ ውጤት እንደምታስመዘግብ፣ ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጉልበትና የኤሌክትሪክ ኃይል ዝቅተኛ መሆን፣ መሠልጠን የሚችል በርካታ የሰው ኃይልና ዋና ዋና ምርት ተቀባይ ገበያ መኖር፣… ኢትዮጵያን በጨርቃ ጨርቅ ምርትና ኢንቨስትመንት የዓለም ሸማቾች ማዕከል ሊያደርጋት እንደሚችል ኦፊሰሯ ገልፀዋል፡፡
ባለፈው ወር ከተደረገው ውይይት እንደተረዳነው፤ ኢትዮጵያን በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ለስኬት የሚያበቃት የስትራቴጂ አማራጮች አራት ናቸው ያሉት የዓለም ንግድ ማዕከል የኤክስፖርት ስትራቴጂ ተባባሪ አማካሪ ሚስ አሌክሳንደራ ጐሎ ቮኮ፣ ምርታማነትን ማሻሻልና የሠራተኛውን ክህሎት በማዳበር የምርት ውጤቱን ማሳደግ፣ የዘርፉን ልማት ለማሳደግ አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ ለጨርቃጨርቅ ምርትና ልብስ ዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተር የሆኑትን የውጭ ካፒታል ኢንቨስትመንት ማመቻቸትና የምርትና ገበያን ዕድገት በንግድ ኢንፎርሜሽን (መረጃ) መደገፍ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሚስ ጐሎቮኮ፣ በዓለም አቀፍ የጨርቃጨርቅና ተጓዳኝ ንግድ፣ ምርትን በዝቅተኛ ዋጋ ማምረት፣ ከቀረጥ ነፃ ዕድል መጠቀም፣ ሸማቾች በሚፈልጉት ፋሽንና ተፎካካሪ በሆነ ዋጋ ምርጥ ምርት ማቅረብ የሚችል አዲስ ተፎካካሪ ትልቅ ዕድል እንዳለው አመልክተዋል፡፡

Read 2038 times