Saturday, 11 July 2015 12:27

የኬንያ ባለስልጣናት ኦባማ ስለ ግብረ-ሰዶማውያን መብት እንዳያወሩ አስጠነቀቁ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ኦባማ አሻፈረኝ ብለው ስለዚህ ጸያፍ ነገር ካወሩ፣ ማዕቀብ እንጥልባቸዋለን!” - የኬንያ ፓርላማ አፈ ጉባኤ
   የኬንያ ከፍተኛ ባለስልጣናት በቅርቡ አገሪቱን ለመጎብኘት ቀጠሮ የያዙትን ባራክ ኦባማን፣ “አደራዎትን በጉብኝትዎ ወቅት የግብረ-ሰዶማውያንን መብት የተመለከተ ነገር እንዳይናገሩ” ሲሉ አበክረው ማስጠንቀቃቸውን ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
የኬንያ ምክትል ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶና የአገሪቱ ፓርላማ አፈጉባኤ ለኦባማ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የግብረ-ሰዶማዊነት ጉዳይ ከክርስትና እምነት ጋር የማይሄድ ጸያፍ ነገር ነውና፣ ሊጎበኙን ሲመጡ ጉዳዩን በተመለከተ ምንም ነገር ትንፍሽ እንዳይሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋቸዋል ብሏል ዘገባው፡፡
ከሳምንታት በፊት በመላው ግዛቷ የግብረ-ሰዶማውያንን ጋብቻ በህግ የፈቀደችውን አሜሪካን የሚመሩት ኦባማ ግን፣  ከዚህ ቀደምም ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ እና ሴኔጋልን ሲጎበኙ እንዲህ ያለ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው፣ አሻፈረኝ ብለው ስለ ግብረ-ሰዶማውያን መብቶች በአደባባይ እንዳወሩት ሁሉ፣ የኬንያን ባለስልጣናት ማስጠንቀቂያንም ጆሮ ዳባ ልበስ ሊሉት ይችላሉ ተብሏል፡፡
ባለፈው እሁድ ናይሮቢ ውስጥ በሚገኝ አንድ ቤተክርስቲያን በተካሄደ ስነስርዓት ላይ፣ በርካታ ምዕመናን ለግብረ-ሰዶማዊነት ያላቸውን ተቃውሞ የገለጹ ሲሆን፣ ኦባማ እና ኦባማ ወይም ሚሼል እና ሚሼል እንዲመጡ አንፈልግም ሲሉ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን ነቅፈዋል፡፡
በስፍራው የተገኙት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሩቶም፣ የምዕመናኑን ተቃውሞ በመደገፍ፣ እንዲመጡልን የምንፈልገው ኦባማ እና ሚሼልን ነው፤ ልጅ እንዲወለድልንም እንፈልጋለን ሲሉ በመናገር፣ አገራቸውን ከእንዲህ ያለው ጸያፍ ሃሳብ እንደሚከላከሉ ለምዕመናኑ ቃል ገብተዋል፡፡
የኬንያ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ጀስቲን ሙቱሪ በበኩላቸው፣ አገራቸውና ህዝባቸው ጸያፍ ነገሮችን እንደማይፈልጉ በመግለጽ፣ ኦባማ ወደ አገራችን ከገቡ በኋላ የግብረ-ሰዶማውያንን መብቶች በተመለከተ ንግግር እንዳያደርጉ እናግዳቸዋለን፣ አሻፈረኝ ብለው ከተናገሩም ማዕቀብ እንጥልባቸዋለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡   
ኦባማ ከሁለት ሳምንታት በኋላ የአባታቸው እትብት የተቀበረባትን ኬንያን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Read 2872 times