Saturday, 11 July 2015 12:23

ማይክሮሶፍት በስማርት ፎን ንግድ 7.6 ቢሊዮን ዶላር ከሰረ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 7ሺህ 800 ሰራተኞቹን ለመቀነስ ወስኗል

    ታዋቂው ማይክሮሶፍት ኩባንያ በኖኪያ የስማርት ሞባይል ቀፎ ንግዱ ላይ 7 ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ማጋጠሙን ተከትሎ፣ 7ሺህ 800 ሰራተኞችን ከስራ ገበታቸው እንደሚቀንስ ባለፈው ረቡዕ ማስታወቁን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
ከሁለት አመታት በፊት ኖኪያን በ7.3 ቢሊዮን ዶላር የገዛውና የሞባይል ቀፎዎችን እያመረተ ለገበያ ማቅረብ የጀመረው ማይክሮሶፍት፣ ቢዝነሱ አላዋጣው ማለቱን በማየት ባለፈው አመት ብቻ 12 ሺህ 500 ሰራተኞቹን እንደቀነሰ ያስታወሰው ዘገባው፣
ማይክሮሶፍት ከለመደው የኮምፒውተር ዘርፍ ወጣ ብሎ የተሰማራበት የሞባይል ቀፎ ንግድ ኪሳራ ላይ ጥሎታል ያሉት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ሳትያ ናዴላ፣ ቢዝነሱ ለምን አክሳሪ እንደሆነና በቀጣይ መወሰድ የሚገባቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ግምገማ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
ኩባንያው በቅርቡ የስማርት ፎን ንግዱን አዋጭ በሆነ ሁኔታ ማስቀጠል የሚችልበትን አዲስ አቅጣጫ እንደሚዘረጋና 18ሺህ ሰራተኞቹን መቀነስን ጨምሮ ሰፊ የመዋቅር ለውጥ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ማይክሮሶፍት የፊንላንዱን ኖክያ የገዛው፣ ከዚህ በፊት ያመርታቸው የነበሩትን የዊንዶውስ ሞባይሎች ከአፕል አይፎኖችና ከጎግል አንድሮይድ ሲስተሞች ጋር በገበያ ላይ ተወዳዳሪ ለማድረግ በማሰብ እንደሆነም ዘገባው ጨምሮ አስታውሷል፡፡

Read 1319 times