Saturday, 11 July 2015 11:52

“ወይ ጊዜ፣ ወይ ጊዜ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(13 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እናት ልጇ እስር ቤት ነው፡፡ እናም አንዳንድ የቤት ሥራ የሚያግዛት ሰው አጥታ ተቸግራለች፡፡ ታዲያላችሁ…ለልጇ ደብዳቤ ትጽፋለች፡፡
“የተወደድከው ልጄ፣ አንተ ከታሠርክ በኋላ ኑሮ በጣም ከብዶኛል፡፡ የጓሮ አትክልት ስፍራውን የሚቆፍርልኝ ሰው አላገኘሁም፡፡ ድንችና ቲማቲሙን መትከል አልቻልኩም…” ብላ ትጽፍለታለች፡፡ ልጁም…
“እማዬ፣ እባክሽ እሱን የአትክልት ስፍራ አትነካኪው። ከቆፈርሽው ፖሊሶች ይመጡና አንቺንም ያስሩሻል፣ የእኔም የእስር ዘመን ይራዘማል…” ሲል ይጽፋል፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላ እናት መልሳ ትጽፍለታለች፡፡
“አንተ ከጻፍክልኝ ደብዳቤ ጋር ፖሊሶቹም አብረው መጡ፡፡ የጓሮ አትክልት ስፍራውን ከዳር ዳር ቆፈሩት፡፡ ግን ምንም ነገር አላገኙም፡፡ ተበሳጭተው ነው የሄዱት፡፡” ልጁ ምን ብሎ ቢጽፍ ጥሩ ነው…
“እማዬ፣ ያው የተቻለኝን አድርጌያለሁ፤ አሁን ድንችና ተማቲምሽን መትከይ ትችያለሽ፡፡” አሪፍ አይደል! እሱም የእስር ዘመኑ አይራዘምበትም፡፡
ስሙኝማ…የጊዜ መራዘም ነገር ከተነሳ አይቀር…‘ጊዜ’ እኛን ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ላቅርብ ቢል የክስ ሰነዱ በስንትና ስንት ስካኒያ ተጭኖ እንደሚሄድ አንድዬ ይወቀው፡፡ እናማ…‘ጊዜ’ እና አንድ የአገር ልጅ ቢነጋገሩ እንደሚከተለው የሚባባሉ ይመስለኛል፡፡
አያ ጊዜ፣ እንደምነህ?
እንደምን እንድሆን ትፈልጋለህ? እኔ’ኮ የሚገርመኝ ከጠባያችሁ የድፍረታችሁ!
ምን አጠፋሁ?
አየህ፣ ይሄን ነው የምልህ፣ ምን አጠፋሁ ትለኛለህ?
አያ ጊዜ፣ አልገባኝም…
ሁለት ሰዓት ቀጥረኸኝ ሦስት ሰዓት ትመጣለህ!
ውይ… ለእሱ ነው እንዴ እንዲህ የተበሳጨኸው! የሀበሻ ቀጠሮ ነዋ! ሀበሻ መሆኔን ረሳኸው እንዴ፣ ደግሞ አንድ ሰዓት ብቻ ነው የዘገየሁት፡፡ ምን አላት! እኔ እንደውም ቀጠሮ ላይ ቶሎ በመምጣት ነው የምታውቀው፡፡
የሀበሻ ቀጠሮ! የሀበሻ ቀጠሮ የምትሉት… እኔ  የሀበሻ፣ የፈረንጅ ብዬ ከልጅ ልጅ ለይቼ አውቃለሁ!
አንተ ባትለይም እኛ ሀበሾች ዩኒክ ስለሆንን…
ዩኒክ! ዩኒክ ነው ያልከው! ቃሉን ስትናገረው አታፍርም! ሰዓት አለማክበር ዩኒክነት ነው?
አያ ጊዜ ምን አዲስ ነገር አለው! ሰዓት አለማክበር በዚህ ዘመን አልተጀመረ፡፡ እኛ እኮ ሦስት ሺህ፣ አይደለም አምስት ሺህ ዘመን…
የቁጥር አባዜ የማይለቃችሁ እናንተን አየሁ፡፡ በሦስት ሺህ ዘመን ትኮራላችሁ…የበይ ተመልካች በሆናችሁበት የአፍሪካ ዋንጫ “ከሠላሳ አንድ ዓመት በኋላ…” እያላችሁ ትኮራላችሁ… እኔን ለምን መሸሸጊያ ታደርጉኛላችሁ?
አያ ጊዜ፣ እንዲህማ አፈር ድሜ አታስገባንም፡፡
የዛሬ አርባ ዓመት ኮሪያና ኢትዮጵያ ተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ነበሩ ትላላችሁ፡፡ እነሱ በደንብ ሲጠቀሙብኝ፣ እናንተ እንደ ገና ሩር ከአንድ ጫፍ አንድ ጫፍ ስትለጉኝ አይደል እንዴ የኖራችሁት! እኮ ንገረኛ… በአርባ ዓመት እነሱ እዚህ ደረጃ ሲደርሱ እናንተ የማንን ጎፈሬ ስታበጥሩ ነበር! ፋታ አጣና! ፋታ አጣን…እንደምታውቀው በእኛ የማይመቀኝ የለም…
ዓለም ሁሉ ነዋ በእናንተ ላይ የሚያሴር! እሺ ተመቀኟችሁ እንበል፤ እኔን በአግባቡ ካለመጠቀም ጋር ምን ያገናኘዋል! ለቁም ነገሩ ስትጎተቱ ለፍሬ ከርስኪው ነገር ማንም አይቀድማችሁም፡፡
አያ ጊዜ፣ ምን ማለትህ ነው?
ይሄኔ አንተ አንዷን ቆንጆ ብትቀጥር ኖሮ፣ እንኳን እንደ እኔ አንድ ሰዓት ልትገትራት፣ ለአራት ሰዓቱ ቀጠሮ ሁለት ሰዓት ሳይሞላ ሬስቱራንት፣ ወይ አውቶብስ ፌርማታ ትደርስ ነበር…
አያ ጊዜ፣ አንተ ደግሞ…ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች አሉና!
እኔን አሰቃያችሁኛ! ወይ አንደኛውን ትቻችሁ ጓዜን ጠቅልዬ አልሄድ ታሳዝኑኛላችሁ፡፡ እስቲ ንገረኝ… ሁለት ሰዓት ተኩል ይጀመራል የተባለው ስብሰባ አራት ሰዓት እንኳን የማይጀመረው ለምንድነው?
የክብር እንግዳውስ አያ ጊዜ…የክብር እንግዳውስ! የክብር እንግዳው ሳይመጣማ ስብሰባ አይጀመርም፡፡
የእናንተ አገር ስብሰባ ያለ ክብር እንግዳ አይሆንም ነው የምትለኝ!
በጭራሽ! አይሆንም ሳይሆን አይታሰብም፡፡ አያ ጊዜ ለእኛም አስብልን እንጂ! አንተ ስታስበው የክብር እንግዳ የሌለው፣ መደረኩ በባንዲራ ያልተንቆጠቆጠ፣ በየሰዉ ፊት የታሸገ ውሀ ያልተቀመጠበት ስብሰባ ምኑን ስብሰባ ነው!
የክብር እንግዳ ባይኖርስ ሰማዩ ይደፋባችኋል?
ዜና አይነገርልንማ! አየህ፣ ስብሰባን ትኩረት እንዲያገኝ የሚያደርገው አጀንዳው ሳይሆን የክብር እንግዳው ማነው የሚለው ነው፡፡ አንተ ልጄ… ምን አለብህ…
እኮ በማንኛውም ስብሰባ የክብር እንግዳ መኖር አለበት የሚል ህግ አላችሁ እንዴ!
አልገባህም አያ ጊዜ፣ የክብር እንግዳ ከሌለ ዜናው አይነገርም እያልኩህ እኮ ነው፡፡ ደግሞ ዜና ያልተሠራበት ስብሰባ ዋጋ የለውም፡፡ እየው ዜናው እንኳ ሲጀምር እንዴት መሰለህ… “በንጽህና ያልተጠበቀ የመኖሪያ አካባቢ የጤና ችግሮችን እንደሚያስከትል አቶ እከሌ አስገነዘቡ” ብሎ ነው። ከዛም ይቀጥልና… “አቶ እከሌ ይህን የተናገሩት በክብር እንግድነት በተገኙበት በጤና ጉዳዮች ላይ በሚመክረው ጉባኤ ላይ ነው…” ይልና ሦስተኛው ዓረፍተ ነገር ምን ይል መሰለህ…“ጉባኤው በሚቀጥለው ሰኞ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ይጠናቀቃል…” አየህልኝ አይደል!
እሺ የክብር እንግዳውስ ምን ይጎትተዋል…በሰዓቱ አይመጣም!
ኸረ እባክህ ቀስ በል! ደግሞ ጦስ እንዳታመጣብኝ…እንደውም ሰሞኑን ዙሪያዬን የሚያንዣብበው በዝቷል፡፡
እኮ አስረዳኛ… የክብር እንግዳው ለምን በሰዓቱ አይመጣም?
በሰዓቱ ከመጣማ ምኑን የክብር እንግዳ ሆነው! ስማ አያ ጊዜ፣ በሰዓቱ አለመምጣቱ እኮ አንዱ የክብር እንግዳ መገለጫ ነው፡፡
እሺ የክብር እንግዳው ቶሎ ሲመጣ እንኳን ስብሰባ የማይጀመረው ለምንድነው?
ቴሌቪዥንስ! የቴሊቪዥን ካሜራ በሌለበት እንዴት ስብሰባ ይጀመራል! ንገረኝ ካልክ ብዙ ስብሰባዎች የሚደረጉት እኮ ለቴሊቪዥን ዜና ነው፡፡ እየው፣ ስማኝማ…እንኳን የክብር እንግዳ፣ ሙሽሮች እንኳን በሰዓቱ መምጣት ትተዋል፡፡ እንግዶቻቸውን በሰባት ሰዓት ጠርተው እኮ እነሱ በአሥር ሰዓት ነው የሚደርሱት፡፡ እንደውም ስልክ እየተደወለ ሰዉ ገና እየገባ ስለሆነ ቆይታችሁ ኑ ይባላሉ፡፡
የእነሱ ደግሞ ጭካኔ ነው፤ ሰዉን በባዶ ሆድ…
በባዶ ሆድ! አያ ጊዜ… ሰዉ ነቄ ሆኗል፡፡ ባዶ ሆዱን ሠርግ መሄድ እኮ ትቷል፡፡ ልጄ ጥስቅ አርጎ በልቶ ነው የሚመጣው፡፡
ደግሞ እኮ እኔን መጀመሪያውኑ በሚገባ ሳትጠቀሙብኝ በሆነ ባልሆነው “ተራዝሟል…” የምትሉት ነገር አላችሁ፡፡
አያ ጊዜ፣ አልገባኝም…
“ለምዝገባ ሠላሳ ቀን ተሰጥቷል…” ካላችሁ በኋላ ቆይታችሁ “ምዝገባው ለአሥራ አምስት ቀን ተራዝሟል…” ትላላችሁ፡፡ መጀመሪያ ከሠላሳ ቀኑ ሦስቱን እንኳን በስርአት ተጠቅማችሁ ቢሆን ጥሩ፡፡ አንገላታችሁኝ፣ ተጫወታችሁብኝ…
እኛ እኮ ጥፋት የለብንም፡፡
እንዴት ጥፋት የለባችሁም…
ገና ምዝገባው አንድ  ወር ሲባል ለአሥራ እምስት ቀን እንደሚራዘም እናውቃለና፡፡
ንቃችሁኛል፣ ደፍራችሁኛል፣ ቢታመንም ባይታመንም በቁሜ ቀብራችሁኛል፡፡
አያ ጊዜ፣ ፖለቲካ መናገር ጀመርክ እንዴ! ለነገሩ አንተን ማን ይነካሃል…እኔ ልጆቼን ላሳድግበት፡፡ እንደው ልጅ ስል ምን ትዝ አለኝ መሰለህ---ዘንድሮ ልጅ እንኳን የተባለበትን ጊዜ ጠብቆ መወለድ ትቷል፡፡ ይመጣል ከተባለበት ሦስት ሳምንት ቆይቶ ይመጣል…
ይሄ በዚህ ቀን ይመጣል የሚሉት ሀኪሞች ችሎታ ማነስ ነዋ!
አይደለም…አያ ጊዜ እንደ እሱ አይደለም፡፡ ሀኪሞቹ ምንም ችግር የለባቸውም፡፡ አየህ የዘንድሮ ልጅ ተንኮል የሚጀምረው ገና ሳይወለድ ነው…
ጀመረህ ደግሞ፣ ይህን በትውልድ ላይ ጣት መቀሰር ጀመርከኝ…
እውነቴ እኮ ነው…
እኔ የምለው እዚህ አገር መቼ ነው አንዱ ትውልድ በሌላው ላይ ጣት መቀሰሩን የሚያቆመው! ምነው ሌላው አገር እንዲህ አይናቆር!
አይደለም፣ ምን መሰለህ…
ግዴለም፣ ግዴለም ይበቃናል፡፡ የእናንተን ነገር ስናወራው ብንውልና ብናድር ለከርሞም አንጨርሰው፡፡  ወይ ጉድ…የአንተው አንሶ እያስለፈለፍከኝ እኔኑ እኮ ራሴን በራሴ እንዳጠፋ እያደረግኸኝ ነው! ደህና ሰንብት!
“ወይ ጊዜ፣ ወይ ጊዜ…” ከሚል አይነት እንጉርጉሮ አውጥቶ…አለ አይደል…‘ጊዜ’ንና እኛን የሚያዋድደንን ተአምር አንድዬ ይላክልንማ፡፡
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 3387 times