Saturday, 04 July 2015 11:39

የደቡብ ሱዳን መንግስት ወታደሮች፣ ሴቶችን በመድፈር በቁማቸው አቃጥለዋል ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

- 172 ሴቶች ተጠልፈዋል፣ 79 ሴቶችና ልጃገረዶች ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል
- መንግስት ወታደሮቼ ፈጸሙት የተባለውን ድርጊት ለማመን ይከብደኛል ብሏል

     የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የደቡብ ሱዳን መንግስት ወታደሮች በአገሪቱ ሴቶችና ልጃገረዶች ላይ ጠለፋ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ግርፋት፣ በቁማቸው በእሳት ማቃጠል፣ ግድያና የመሳሰሉ አሰቃቂ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን ፈጽመዋል ማለቱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ ወታደሮቻችን በገዛ ህዝባቸው ላይ ይህን አይነት አሰቃቂ ተግባር ይፈጽማሉ ብለን ለማመን ይቸግረናል፣ ይሄም ሆኖ በሪፖርቱ የቀረቡትን ውንጀላዎች ችላ አንላቸውም፣ ጉዳዩን በጥልቀት መርምረን ተገቢውን እርምጃ እንወስዳለን ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የደቡብ ሱዳን ሴቶችና ልጃገረዶች በአገሪቱ ወታደሮች የሚፈጸምባቸው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እጅግ አሰቃቂ ነው ያለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አንዳንዶቹም ተጠልፈው በግዳጅ ከመደፈራቸው ባሻገር፣ በቁማቸው በእሳት እንዲቃጠሉ መደረጋቸውን ደርሼበታለሁ ብሏል- ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው ሪፖርት፡፡
በመንግስት ጦርና በአማጽያን መካከል ላለፉት 18 ወራት የዘለቀው የደቡብ ሱዳን ግጭት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመባባስ ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት ማምራቱንና አገሪቱን የከፋ ቀውስ ውስጥ እየከተታት መሆኑን ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በመንግስት ወታደሮች ከ172 በላይ የአገሪቱ ሴቶች መጠለፋቸውንና 79 የሚሆኑ ሴቶችና ልጃገረዶችም ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው የገለጸው የተመድ ሪፖርት፣ ዘጠኝ ያህል ሴቶችና ልጃገረዶች ተገደው ከተደፈሩ በኋላ በእሳት መቃጠላቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
115 የአይን እማኞችንና የጥቃት ሰለባዎችን እማኝነት በመጥቀስ በደቡብ ሱዳን የተመድ ልኡክ ያወጣው ሪፖርት እንዳለው፣ በአገሪቱ መንግስት ወታደሮች እየተፈጸመ የሚገኘው ጥቃት እየተባባሰ ወደ አሰቃቂ ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ ሱዳን ትሪቢዩን በበኩሉ፤ የመንግስት ጦርና የአማጽያኑ ወታደሮች የአገሪቱን ዜጎች ብሄርን መሰረት አድርገው እንደሚገድሉና መንደሮችን በአሰቃቂ ሁኔታ እንደሚያቃጥሉ በሪፖርቱ መገለጹን ዘግቧል፡፡

Read 2573 times