Saturday, 04 July 2015 10:48

የአቢሲኒያ ባንክ የተወዳዳሪነት ውጥን

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ አቅምና ጡንቻ ላላቸው የፋይናንስ ዘርፍ ኢንዱስትሪዎች በሯን እንደዘጋች ነው፡፡ ይህን በቴክኒክ፣ በካፒታል፣ በእውቀት፣ በባንክ አሰራርና በሰው ኃይል አቅማቸው ላልጠነከረውና ላልዳበረው የአገር ውስጥ ባንኮች ከለላ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ከአሁን በኋላ ግን የሚቀጥል አይመስልም፡፡
በቅርብ ዓመታት አገሪቷ የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባል እንደምትሆን እየተነገረ ነው፡፡ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው የፈረጠመ ክንድ ያላቸው ባንኮች ካፒታል፣ እውቀትና ዓለም አቀፍ ልምድ፣ … ይዘው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል፡፡ በዚያን ጊዜ አገር በቀሎቹ ባንኮች በቀድሞው ሁኔታ መቀጠል አይችሉም፡፡ በዘርፉ የላቀ እውቀትና ልምድ ያላቸው አንዳንድ ባለሙያዎች፣ በኢትዮጵያ ያሉ አንዳንድ ባንኮች ካልተዋሃዱ በስተቀር ለብቻቸው ከግዙፎቹ ባንኮች ጋር መፎካከር አይሆንላቸውም የሚል ሀሳብ እየሰነዘሩ ነው፡፡
አገር በቀሎቹ ባንኮች ይህ ሁኔታ ቢዘገይ እንጂ የማይቀር መሆኑን የተገነዘቡ ይመስላል፡፡ ወቅቱ ሲደርስ ከፋይናንስ ኢንዱስትሪው ተሽቀንጥረው እንዳይወጡ፣ ተወዳዳሪ ሆነው ገበያው ውስጥ ለመቆየትና ከአለም አቀፍ የባንክ አሰራር ጋር ለመላመድ በዘርፉ እውቅና ካላቸው ባንኮች ጋር መስራት ወይም የቀረፁትን የወደፊት ዕቅድን እንዲያስፈፅሙላቸው ወይም የአሰራር እቅድ እንዲቀርፁላቸው … እያደረጉ ነው፡፡
የአገሬው ባንኮች የውጪዎቹ የሚጠቀሙበት ዘመናዊ መሳሪያና ሶፍትዌር ሊገዙ ይችላሉ፡፡ መሳሪያዎቹ ቢገዙም በራሳቸው አይንቀሳቀሱም፡፡ መሳሪያዎቹን የሚተክል፣ ሶፍትዌሮቹን የሚገጥም፤ አሰራራቸውን የሚያውቅና የሚከታተል ክህሎቱ የዳበረ፣ በዘርፉ በሚገባ የሰለጠነ ዓለም አቀፍ የባንክ አሰራር የሚያውቅ ባለሙያ የላቸውም፡፡ እንግዲህ ይህን እጅግ አስፈላጊ የሆነ የሰው ኃይል ለማፍራት እየጣሩ ነው፡፡
በዚህ ረገድ አቢሲኒያ ባንክ አ.ማ በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ጥሩ የተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠልና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን አሰራር ለመዘርጋት፣ እንዲሁም ባንኩ በቀጣይ አምስት ዓመት የሚመራበትን መሪ እቅድ (ስትራቴጂክ ፕላን) ቀርፆ በመተግበር እንዲያማክረው ዓለም አቀፍ የቢዝነስ አማካሪ ለመቅጠር በመወሰን በዓለም ታዋቂ የሆኑ 4 የቢዝነስ አማካሪ ድርጅቶችን አወዳድሮ አሸናፊ ከሆነው ዲሊዮት (Deloitte) ኩባንያ ጋር ለመስራት በሳምንቱ መጀመሪያ በሂልተን ሆቴል ተፈራርሟል፡፡
አማካሪ ድርጅቱ ከሳምንት በፊት ስራውን በይፋ መጀመሩንና በ6 ወራት ውስጥ የስትራቴጂ እቅዱን ሰርቶ ለመጨረስ መስማማቱን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አስማረ ጠቅሰው፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የስተራቴጂውን አፈጻጸም (Organizational Transformation) በቅርበት በመከታተልና በመተግባር እንደሚያማክራቸው ተናግረዋል፡፡
ባንኩ ከዚህ ቀደም 3 የአምስት ዓመት ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ተግባራዊ ማድረጉን፣ በባንክ የሥራ ዘርፍ ያለውን ውድድር በብቃት ለመወጣትና ከዘመኑ ጋር በመራመድ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን በመግዛት በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ የበኩሉን ሚና ሲያበረክት መቆየቱን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፣ እየሰፋ የመጣውን የባንክ አገልግሎት ፍላጎት ለማርካት፣ በመስኩ ያለውን ውድድር በብቃት ለመወጣት፣ የባንኩን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላትን ፍላጎት በሚገባ ለማርካትና ዘመኑ የሚጠይቀውን የባንክ አሰራር ለመከተል ዲሊዮት እንዲያማክራቸው መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡
በፊርማው ሥነ - ሥርዓት ላይ የተገኙት የዲሊዮት ኩባንያ ሥራ አስፈፃሚዎች ሁለት ነገር ይዘው መቅረባቸውን ጠቅሰው፣ ኩባንያቸው ኢትዮጵያን ጨምሮ በ6 የምስራቅ አፍሪካ አገሮች የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ዓለም አቀፍ የባንክ አሰራር ልምድ እንዳለው፣ በኢትየጵያ ወቅታዊ የባንክ አሰራር ላይ ጥናት በማድረጉ፣ ሁለቱን በማቀናጀትና በቴክኖሎጂ በመታገዝ የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ እርካታ፣ የባንኩን ዕድገትና የገበያ ተወዳዳሪነት፣ … ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡
አቢሲኒያ ባንክ ከ20 ዓመት በፊት የግል ባንኮች ወደ ኢንዱስትሪው ገብተው እንዲሰሩ በተፈቀደ ማግስት ከተቋቋሙ 3 ባንኮች አንዱ ነው፡፡ 131 ግለሰቦች በከፈሉት የአክሲዮን ድርሻና 18 ሚሊዮን ብር ባልሞላ ካፒታል የተመሰረተው ባንክ፤ በአሁኑ ወቅት  ካፒታሉ 1.5 ቢሊዮን ብር፣ የደንበኞች ቁጥር 462 ሺህ፣ የቅርንጫፎች ብዛት 130 መድረሱንና የባንኩ ተቀማጭ ሀብት ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ታውቋል፡፡   

Read 2434 times