Saturday, 04 July 2015 10:46

የማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣን ከአፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን እየሠራሁ ነው አለ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

የማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣን የቀድሞውን ዕቅድ መነሻ በማድረግ፣ አፈጻጸሙን ጐዶሎ ያደረጉትን ትላልቅ ጉዳዮች ለይቶ በማውጣት የሚቀጥለው 5 ዓመት እቅድ የተሻለ እንዲሆን ከደንበኞችና ባለድርሻ አካላት ጋር ከትናንት በስቲያ በኢሊሌ ሆቴል ባደረገው ምክክር፤ በዕቅዱ 5 ዓመት መጨረሻ ከአፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የዓለም ባንክ ባለፈው 2014 ባወጣው ሪፖርት፤ የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ዕቃዎች የትራንዚት ጊዜ 44 ቀናት ይፈጃል ቢልም ባለሥልጣኑ የመረጃ ምንጭ ስህተት ነው በማለት አስተባብሏል፡፡
ባንኩ የኢትዮጵያ የገቢና ወጪ ዕቃዎች የትራንዚት ጊዜ በአማካይ 44 ቀናት ነው የሚለውን መረጃ ያገኘው ከእኛ ሳይሆን ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ አፈጻጸም ትክክለኛ መረጃ ከሌላቸው ዓለም አቀፍ አስተላላፊዎች (Forwarders) ነው ያሉት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ፣ “ከባንኩ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተን ብንወያይ እንግባባ ነበር፡፡ እኛ ገቢና ወጪ ዕቃዎች ለማስተላለፍ የሚወስድብን ጊዜ በአማካይ ከ15-20 ቀን ሲሆን ይህም በዛ ብለን በቀጣዩ ዕቅድ መጨረሻ 50 በመቶ ለመቀነስ እየጣርን ነው” ብለዋል፡፡
44 ቀን ይፈጃል ማለት ለአንድ ኤክስፖርተር የሚሰጠው ትርጉም የተለየ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ገንዘብ ኖሮት (ለጭነት፣ ለማጓጓዣ፣ ለጉምሩክ፣ ለወደብ፣ ለባንክ…) ከፍሎ አስፈላጊ ሰነዶችን ያሟላ ሰው ከ15 ቀን በላይ አይወስድበትም፡፡ ይኼ የመረጃ ክፍተት የውጭ ኢንቬስተሮችን በጣም ያስደነግጣል፡፡ አሁን ካለን አፈጻጸም አኳያ አንዳንድ ነጥቦች ከባንኩ ጋር አያስማሙንም፡፡ ምክንያቱም እኛ የምንለው በሐሳብ ላይ ተመስርተን ሳይሆን በተጨባጭ በተግባር እየተሰራ ያለውን ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
ይህን የምንለው ሪፖርቱን ለመቃወም አይደለም፤ የኢትዮጵያ ሎጀስቲክስ ችግር አለበት በሚለው ነጥብ ላይ ከእነሱ በላይ እኛ እናምናለን፡፡
ምክንያቱም ልማታችን ከሚጠይቀው ፍጥነት አኳያ፣ ባጠረ ጊዜ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ኢምፖርት/ኤክስፖርታችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ካልሆን ውጤት አናመጣም፡፡ ቁጥሩን ትተን “የኢትዮጵያ ሎጀስቲክስ ችግር አለበት” የሚለው በጣም ይስማማናል በማለት ገልጸዋል፡፡
በዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ አፈጻጸም መለኪያ መሰረት የኢትዮጵያ የዚህ ዓመት አፈጻጸም በአማካይ 2.59 ነጥብ፣ ከዓለም የአገሮች ደረጃ 104ኛ መሆኗን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡  አቶ መኮንን በዓለም ባንክ መለኪያ መስፈርት መሰረት መካከለኛ ገቢ ላይ የደረሱ አገሮች ደቡብ አፍሪካ፣ ማላዊ፣ ዙንባብዌ፣ ሩዋንዳ፣ ታይላንድ፣ ቦሊቪያ፣ … በማሪታይምና በሎጅስቲክ የደረሱበትን ደረጃ በመገምገም ከ5 ዓመቱ ዕቅድ የአፈፃፀም አገራዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መልካም አጋጣሚዎችና ስጋቶችን በጥልቀት ፈትሸውና አገናዝበው በ2012 መጨረሻ ከቪየትናም፣ ኢንዶኔዥያ፣ ህንድና ፊሊፒንስ ተርታ ለማሰለፍ አሁን በአማካይ 2.59 የሆነውን አፈጻጸም በአማካይ 3.07 ለማድረስ፣ ደረጃውን ደግሞ ከ104ኛ ወደ 57ኛ ከፍ በማድረግ ከአፍሪካ 1ኛ ለማድረግ መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡
ዕቃዎች ወደብ ላይ የሚቆዩበትን ጊዜ ከ40 ቀን በላይ ወደ 3 ቀን ለመቀነስ፣ በኮንቴነር ታሽገው ሊጓጓዝ የሚችሉ ዕቃዎችን ከ7 በመቶ 100 ፐርሰንት ለማድረስ፣ የገቢ ዕቃ ፎርማሊቲዎችን ከ10 ወደ 4 ለመቀነስ፣ አሁን በእጅ የሚሰራውን ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም  100 ፐርሰንት አውቶማቲክ ማድረግ፣ ብቁ ባህረኞችን ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር መርካቦች በማሰልጠን አሁን ያለውን 6000 ወደ 30,000፣ በውጭ አገር መርከቦች ላይ ተቀጥረው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን መርከበኞች ከሚያገኙት ገቢ 80 በመቶ ለቤተሰቦቻቸው ከሚልኩት 72 ሚሊዮን ዶላር ሬሚታንስ ወደ 0.3 ቢሊዮን ዶላር ማሳደግ፣ … የማሪታይም ጉዳይ ባለሥልጣን የ5 ዓመት ዕቅድ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የራሳቸው የንግድ መርከቦች ካላቸው አገሮች አንዷ በመሆንዋ ቀደም ሲል በህንድና በጋና ይሰለጥኑ የነበሩትን መርከበኞችን ራሷ ከማሰልጠኗም በላይ በዓለም ላይ 450 ሺህ የባህረኞች እጥረት ስላለ ቀሪዎቹን በውጭ ምንዛሪ በአውሮፓ መርከቦች ላይ በመቀጠር ወደ አገር በሚልኩት ገንዘብ (ሬሚንታስ) ለአገራቸው የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስገኙ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በመካከለኛ ምስራቅ አገሮች የሚሰሩትን ሳይጨምር ከባህርዳር ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካልና በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ በዲግሪ የተመረቁ ከአንድ ሺህ በላይ መርከበኞች በትላልቅ መርከቦች ላይ በኦፊሰርነት ተቀጥረው እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡  ከፍተኛ ሥራ መሠራት አለበት ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በአምስት ዓመቱ እቅድ መጨረሻ ከ10ሺህ እስከ 30ሺህ መርከበኞች ይሰለጥናሉ ብለዋል፡፡
አቶ መኮንን፣ ባለሥልጣኑ ያዘጋጀው እቅድ ሙሉ በሙሉ የሚሳካው፣ በባልሥልጣኑ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል (ጉምሩክ፣ ባንክ፣ ወደብ፣ ማጓጓዣ፣ ማሪታይም፣ ኢምፖርተርና ኤክስፖርተር…) ሁሉም ድርሻቸውን አውቀው በኃላፊነትና በተጠያቂነት በጋራ ሲሰሩ መሆኑን ጠቅሰው እቅዱን ስኬታማ ለማድረግ እንዲረባረቡ ጠይቀዋል፡፡   

Read 1454 times