Saturday, 04 July 2015 10:43

‹‹የታሪክ መጨረሻ እና የመጨረሻው ሰው››

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(7 votes)

     የቀዝቃዛው ጦርነት ከማክተሙ፤ የበርሊን ግንብ ከመደርመሱ፤ ዓለም ከአንድ የኃይል ዙፋን ሥር ከመውደቋ፤ ሩሲያ ከመፈራረሷ፤ ዓለም ‹‹ለሁለት ጣኦት አልገዛም›› ብላ፤ ‹‹ሊበራልዝም›› ለተሰኘው አማልክት ከመስገዷ በፊት፤ …. ያኔ በፊት፤ ታሪክ የማያቋርጥ ሂደት ሆኖ ይታይ ነበር፡፡ ታሪክ መጨረሻ አልነበረውም፡፡
ሆኖም፤ የቀዝቃዛው ጦርነት ሲያከትም፤ የበርሊን ግንብ ሲፈርስ፤ ዓለም ‹‹ሶሻሊዝም እና ሊበራሊዝም ለተባሉ ሁለት ጣዖታት አልገዛም›› ብላ ስትፈጠም፤ ብቸኛ ልዕለ ኃያል ሐገር ሆና ከወጣችው ከአሜሪካ ዙፋን ሥር ስትነጠፍ፤ አንድ ፍራንሲስ ፉኩያማ የሚሉት ፀሐፊ፤ ‹‹ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ፤ ዓለም የጀመረችው አንድ የታሪክ ጉዞ ከመጨረሻው ምዕራፍ ደረሰ›› የሚል ድፍረትን ተሻግሮ፤ ‹‹ራሱ ታሪክ ከጉዞው የመጨረሻ ምዕራፍ ደረሰ›› ብሎ አወጀ፡፡ ‹‹The end of history›› አለ፡፡ በዘመነ ፉኩያማ፤ ታሪክ መጨረሻ አገኘ።
ፍራንሲስ ፉኩያማ፤ ‹‹አሁን የምንገኘው፤ ከምዕራቡ ዓለም የተወለደው የሊበራል ዲሞክራሲ አገዛዝ፤ የሰው ልጆች ሁሉ በዕድገት ሂደት የሚቀበሉት አማራጭ የለሽ እና አይቀሬ ርዕዮተ ዓለም ወይም የአገዛዝ ስርዓት መሆኑን በሚያስረዳ የታሪክ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ነው›› ሲል በታሪክ ላይ የሞት ፍርድ አሳልፎ ነበር፡፡
ፉኩያማ ‹‹ታሪክ ሞተ›› ባለ ጊዜ (በ1980ዎቹ)፤ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ተፀንሳ፤ በአፄ ዮሐንስ ጎልምሳ፤ በአፄ ምኒልክ ዘመን የመጨረሻ መልኳን ይዛ የተወለደችው እና በአፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን ጠንካራ ማዕከላዊ አስተዳደር መስርታ፣ በኋላም ኤርትራን አካታ የቆመችው ኢትዮጵያ፤ ለረጅም ዘመናት በብዙ ቅራኔዎች ተቀስፋ የቆየችው ኢትዮጵያ፤ በመጨረሻ ከአረመኔው ደርግ እጅ ወድቃ ለ17 ዓመታት የማቀቀችው ኢትዮጵያ፤ የበርሊን ግንብ በፈረሰ ‹‹ሰሞን››፤ የአዲስ ስርዓት ምጥ ይዟት ተፋፍማ ነበር፡፡
ምናልባት፤ ፉኩያማ ‹‹የታሪክ መጨረሻ ሆነ›› ማለቱን የሚቃወሙና የተቃወሙ ሰዎች ቢኖሩም እንኳን፤ በደርግ መንግስት ውድቀት ማግስት የነበረውን የኢትዮጵያን ሁኔታ ያየ ሰው፤ ‹‹አሁን የዘመናዊት ኢትዮጵያ የመጨረሻ ዘመን ደረሰ›› የሚል የታሪክ ፍርድ ለመቀበል የሚቸገር አይመስለኝም፡፡ ወይም ተቃዋሚዎቹ ብዙዎች አይሆኑም ብዬ እገምታለሁ፡፡
ዛሬ - ዛሬ፤ ‹‹ፉኩያማ ‹ታሪክ ሞተ› ሲል፤ ታሪክ በበኩሉ፤ ‹ፉኩያማ ሞተ› አለ›› እያሉ የፉኩያማን ሐሳብ የሚነቅፉ ሰዎች በርክተዋል፡፡ እርሱም ሐሳቡን እንደቀየረ ይነገራል፡፡ ሆኖም በዚህ መጣጥፍ ማንሳት የፈለግኩት፤ የዓለምን የርዕዮተ - ዓለም ታሪክ መተረክ አይደለም። ጨርሶ የፉኩያማን ሐሳብ የመደገፍ ወይም የመንቀፍ ፍላጎት የለኝም፡፡ የኔ ትኩረት፤ ከፀሐፊው ሳይሆን ከቀልብ ሳቢው መፅሐፍ ርዕስ ነው፡፡ የፉኩያማ መፅሐፍ ርዕስም፤ ‹‹The end of history and the last man›› (የታሪክ መጨረሻ እና የመጨረሻው ሰው) የሚል ነው። ታዲያ ፉኩያማ ለመፅሐፉ የሰጠው ይህ ርዕስ፤ የአንድ ኢትዮጵያዊ መሪን ታሪክ፤ በብዙ ጎዳና (በእማሬም ሆነ በፍካሬ) ለመግለፅ የሚያስችል ልዩ አንደበት ወይም ቋንቋ ያለው ሆኖ ታየኝ፡፡
‹‹የታሪክ መጨረሻ እና የመጨረሻው ሰው›› የሚለው ሐረግ፤ የዚህን መሪ እና የሐገሪቱን፤ ምናልባትም የወቅቱን የዓለም ሁኔታ አሟልቶ ለመግለፅ የሚችል ነው፡፡ የፍራንሲስ ፉኩያማ መፅሐፍ ርዕስ፤ የኢትዮጵያ የታሪክ ፀሐፊዎች፤ ‹‹ዘመነ መሳፍንት›› በሚል በሚጠቅሱት የታሪክ ዘመን መጨረሻ ለመጡት እና የ‹‹ዘመነ መሳፍንት›› የመጨረሻው ንጉስ ለሆኑት ለአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት እና ህይወት ተገቢ ርዕስ መሆኑ ይታየኛል፡፡
በትውልድ ጃፓናዊ፣ በዜግነት አሜሪካዊ የሆነው ፍራንሲስ ፉኩያማ፤ ‹‹በታሪክ ላይ ሞት ከመፍረዱ አስቀድሞ›› ከ121 ዓመታት በፊት፤ የኢትዮጵያ የታሪክ ፀሐፊዎች፤ ‹‹ዘመነ-መሣፍንት›› ሲሉ በሚጠቅሱት የታሪክ ምዕራፍ (ከ1769 እስከ 1855 ዓ.ም እኤአ) ብቅ ካሉት አፄ ቴዎድሮስ ጋር ተያይዞ፤ በዓለም የጋዜጠኝነት ታሪክ አንድ አዲስ ነገር ተከስቷል፡፡ ይህ መጣጥፍ ትኩረት የሚያደርገው በዚሁ ጉዳይ ነው፡፡
እስራኤላውያን ጠቅልሎ የሚገዛ ንጉሥ አጥተው፤ የተለያዩ ግዛቶች በተለያዩ መሣፍንት ይገዙ የነበረበትን ሁኔታ መሰረት አድርገው፤ የኢትዮጵያ የታሪክ ፀሐፊዎች ‹‹ዘመነ-መሣፍንት›› ሲሉ በሚጠቅሱት ታሪከ - ዘመን የመጡት እና አንዳንድ ፀሐፊዎች የዘመነ-መሳፍንት የመጨረሻው መሪ አድርገው የሚመለከቷቸው፤ ሌሎች ደግሞ የአዲስ ዘመን ከፋች እና የዘመናዊት ኢትዮጵያ መስራች አባት አድርገው የሚያይዋቸው አፄ ቴዎድሮስ፤ ‹‹በታሪክ መጨረሻ የመጡ፤ የመጨረሻ ሰው›› ናቸው፡፡  
አፄ ቴዎድሮስ፤ በመጨረሻዋ ሰዓት መቅደላ አምባ ነበሩ፡፡ መቅደላ አፋፉ ላይ ቆመው፤ ከእንግሊዝ የኢንዱስትሪ አብዮት ማህፀን ከተወለደው እና ሊቀስሙት ይመኙት ከነበረው የአውሮፓ ስልጣኔ ጋር ተጋጥመው፤ ጠላቶቻቸውን ‹‹አሸነፍነው›› ብሎ ለመፎከር የሚያስቸግር ሁኔታ ውስጥ ከትተው ተሸነፉ። ዝርዝሩን ትተን በዋናው ጉዳይ ካተኮርን፤ በመቅደላ አምባ ጦርነት የገጠሙት ስልጣኔ እና ኋላ ቀርነት ናቸው ማለት እንችላለን፡፡
ኢትዮጵያ ከስልጣኔ ማማ ወርዳ ከኋላ ቀሮች መንድር ስትገባ፤ እንግሊዝ ወይም ጠቅላላው የአውሮፓ ህዝብ፤ ያልሰለጠነ የ‹‹ከፊል አውሬ›› ደረጃ ሊባል ከሚችል አዘቅት ወጥተው ዕድገትን ተቀዳጁ፡፡ እንግሊዝ ‹‹ባርባር›› በነበረች ዘመን፤ ህንድ እና ቻይና - በእስያ አህጉር፤  ኢትዮጵያ እና ግብፅ ደግሞ በአፍሪካ አህጉር የላቀ የስልጣኔ ደረጃ ላይ ደርሰው ነበር፡፡ ሆኖም፤ ወደ ኋላ፤ የተቀረው ዓለም መራመድ ተስኖት ቆሞ ሲቀር እና በታሪክ ጫማ እንደ በረዶ ተንኮታኩቶ ሲቀበር ወይም ምስጥ እንደበላው ውዳቂ ግንድ በታሪክ ደንታ ቢስ እግር እየተረጋገጠ ሲሰባበር፤ በኢንዱስትሪ አብዮት ከመሬት ተነስታ ጥበብን የታጠቀችው እንግሊዝ፤ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት የነበረችውን ህንድን፤ ጥበብን መሰረት ባደረገ ወታደራዊ ኃይል አንበርክካ ቅኝ ግዛቷ አደረገቻት።
የቻይናም ዕጣ ከዚህ ብዙ የራቀ አልነበረም፡፡ ቻይና በቀጥታ በቅኝ ግዛት ሥር ባትወድቅም፤ በእጅ አዙር የኃያላን መጫወቻ ሆናለች፡፡ ቻይና፤ ልክ እንደ ኢትዮጵያ፤ በየአካባቢው የተነሱ የጦር አበጋዞች ‹‹ዘመነ መሳፍንት›› ሰርተውባት፤ እንደ ቅርጫ ተቀራምተዋት ፍፁም ደክማ፤ የኃያላኑ መጫወቻ ሆናለች፡፡ በቴዎድሮስ ዘመን፤ ሌላዋ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት ግብፅ፤ በኃያላኑ እጅ ከወደቀች ብዙ ቆይታለች፡፡ የቀረችው ኢትዮጵያ ነች፡፡ ኢትዮጵያም ዙሪያዋን በቅኝ ገዢዎች ተከባ ቀኗን የምትጠብቅ መስላለች፡፡
በዚህ ጊዜ፤ እንደ አፄ ቴዎድሮስ ሁሉ፤ በወቅቱ የሚታየው ነገር አላምር ብሏት ጭንቀት ወርሷት የነበረችው ጃፓን፤ አዝማሚያውን ካየች በኋላ፤ ህልውናዋን ለማረጋገጥ የምትችለው የምዕራቡን ዓለም ቴክኖሎጂ በመቅዳት እንደሆነ ተረድታ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መሳፍንት በአንድ ንጉስ መተዳደርን እምቢ ብለው ጦርነት ያደርጉ ነበረ፡፡ በዚያ ጊዜ፤ የጃፓን መኳንንት  እና ህዝቡ በአንድ ንጉስ ሥር ጠንካራ አንድነት በመመስረት፤ በፍጥነት የአውሮፓን ስልጣኔ መቅሰም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ስለተረዱ፤ መኳንንቱ ሁሉ አውሮፓን ዞሮ ለማየት ተንቀሳቀሱ፡፡
‹‹የጃፓን መሳፍንት ይህን ውሳኔ እንዴት ሊወስኑ ቻሉ?›› የሚለው ጥያቄ፤ እንቆቅልሽ ሆኖ፤ የማህበራዊ ሳይንስ ጠቢባንን እስከዛሬ ያከራክራል፡፡ ሆኖም፤ ጃፓናውያን ነባር የፖለቲካ እና ባህላዊ አወቃቀራቸውን እንዳለ ጠብቀው፤ የኢኮኖሚ ስርዓታቸውን በካፒታሊዝም ለመቃኘት መነሳታቸው የማያከራክር እርግጠኛ ታሪክ ነው፡፡
የጃፓን ገዢ መደብ በ1868 ዓ.ም ይህን አቋም ወስዶ፤ ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ልማት›› ብሎ መረባረብ በጀመረ ጊዜ፤ ምናልባት ከጃፓን ቀድመው የአውሮፓን ስልጣኔ መቅሰሙ አስፈላጊ መሆኑን የተረዱት አፄ ቴዎድሮስ፤ መቅደላ አፋፍ ላይ ከእንግሊዝ ወራሪ ጦር ጋር ባልሞት ባይ ተጋዳይነት ፍልሚያ ገጥመው፤ እርሳቸው አጥብቀው ይመኙት የነበረውን ጥበብ ከታጠቀ ኃያል ጦር ጋር ተናንቀው፤ ሞታቸውን ከመንጋጋው መንጭቀው፤ እዚያች አምባ ላይ ወደቁ፡፡ አፄ ቴዎድሮስ በሞቱ ዓመት 1868 ዓ.ም (እኤአ)፤ ጃፓን አውሮፓውያን ሳያስቡት ሹልክ ብላ በማምለጥ የኢንዱስትሪ አብዮት ማካሄድ ቻለች፡፡ አውሮፓውያን ሳይገምቱት፤ የኢንዱስትሪ አብዮት ማካሄድ የቻለች ብቸኛዋ የቢጫ ህዝቦች ሐገርም ለመሆን በቃች፡፡
አፄ ቴዎድሮስ፤ ኢትዮጵያ የምዕራቡን ስልጣኔ በፍጥነት ካልያዘች፤ ነፃነቷን ጠብቃ እንደ ሐገር መቆየት እንደማትችል ተረድተውት ወይም ተገልጦላቸው ነበር፡፡ እናም አጥብቀው የሚመኙትን ስልጣኔ ለማግኘት ዕረፍት አጥተው ሲማስኑ እና ጥበብን በመሻት አውሮፓውያንን ደጋግመው ሲማፀኑ እናያለን፡፡ ንጉሱ በነበራቸው ከፍተኛ ጉጉት እየተሳቡ፤ ሳያስቡት ከእንግሊዝ ጋር ጦር የሚያማዝዝ ችግር ውስጥ ገቡ፡፡  
አፄ ቴዎድሮስ፤ ሐገሪቱ ዙሪያዋን በጠላት የተከበበች ሆኖባቸው፤ እንደ ጃፓን የራሳቸውን ሰዎች ወደ አውሮፓ በመላክ የምዕራቡን ስልጣኔ ለመቅሰም አልቻሉም፡፡ ለእንግሊዝ ንግስት በፃፉት ደብዳቤ፤ የሐገራቸውን ሰው ወደ አውሮፓ ለመላክ እንዳልቻሉ ጠቀሰው፤ ‹‹የእኔን ሰዎች እንዳልክም ጠላት አላሳልፍ አለኝ›› በማለት፤ እንግሊዝ ሙያተኞችን እንድትልክላቸው ይጠይቁ ነበር፡፡ ለህዝባቸው ጥበብን የሚያካፍል ሙያተኛ እንዲልኩላቸው የእንግሊዝ እና የፈረንሳይ መንግስታትን ተማፅነዋል፡፡ ሆኖም፤ ከእንግሊዝም ሆነ ከፈረንሳይ  ቀና ምላሽ አጡ፡፡ እንደ ጃፓኑ ንጉስም፤ የመኳንንቱን እና የህዝቡን ድጋፍ ማግኘት አልቻሉም፡፡
መኳንንቱን እና ህዝቡን በዓላማው ዙሪያ ለማሰለፍ ያልቻለው፤ እንዲሁም ዙሪያውን በጠላት የተከበበው መንግስታቸው፤ እንደ ጃፓን የአውሮፓን ስልጣኔ አይቶ የሚመጣ ቡድን ወደ አውሮፓ መላክ የሚችል አልነበረም። እናም ኢትዮጵያ እንደ ጃፓን የሥልጣኔ ምድር የሆነውን የአውሮፓ አህጉር አይታ መመለስ የምትችልበት ዕድል አላገኘችም፡፡ በየአካባቢው ያለው ሽፍታ ከሚጥለው አደጋ በተጨማሪ፤ ቱርክ እና ግብፅ፤ የኢትዮጵያ መልዕክተኞች በሰላም ግዛታቸውን አቋርጠው እንዲሄዱ  ለማድረግ ፈቃደኞች አልነበሩም። ስለዚህ የኢንዱስትሪ አብዮት፤ ኢትዮጵያን እንዳማራት ቀረ፡፡ ለዚህ መጣጥፍ መነሻ ያደረግኩት ጥናት አለ፡፡ ኖራ ኬ. ሁቨር (NORA K. HOOVER) የተባሉ አንድ ምሁር፤ በፍሎሪዳ ስቴት ዩኒቨርስቲ፤ የሥነ ጥበባት እና የሳይንስ ኮሌጅ፤ ለሦስተኛ ድግሪ (PhD) ትምህርታቸው ማሟያ አድርገው ባቀረቡት፤ ‹‹የቪክቶሪያ ዘመን የጦርነት ዘገባ›› በተሰኘ ጥናታቸው፤ የጦርነት ዘገባ እንደ አንድ የጋዜጠኝነት የሥራ ዘርፍ ብቅ ያለው፤ እንግሊዝ አፄ ቴዎድሮስን ለመውጋት ባደረገችው ዘመን መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡      በእንግሊዝ የመቅደላ ዘመቻ ላይ ያተኮረውን ይህን ጥናት አግኝቼ ባነበብኩ ጊዜ፤ ከመነሻ የጠቀስኩት ‹‹የታሪክ መጨረሻ እና የመጨረሻው ሰው›› የሚለው የፍራንሲስ ፉኩያማ የመፅሐፍ ርዕስ የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ በትክክል ለመግለፅ የሚያስችል ሆኖ ተሰምቶኝ አነሳሁት፡፡ ከዚህም አልፎ፤ የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ በጥሞና ሳስተውል፤ በእኛ ዘመን እና በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን መካከል ጥሩ ንፅፅር ለመፍጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ጉዳዮችን እያሰብኩ ተብሰልስያለሁ። የኢትዮጵያ ታሪክ፤ በማለፊያ ደራሲ እንደ ተነደፈ ድንቅ የተውኔት ሥራ ሴራ ትልሙ በጉልህ ወጥቶ፤ በጡዘት እና ልቀት ተሰናስሎ የተደራጀ ትረካ በማየቴ፤ ለጋዜጣው አንባቢ ለመናገር ሳይሆን ለራሴ የታሪካችንን ውል በደንብ ለመረዳት በማሰብ መፃፍ ጀመርኩ፡፡ እናም፤ ታሪካችንን በደንብ ለመረዳት የሚያግዝ ምቹ ፉካ አግኝቼ፤ በዚያ እየተደነቅኩ መፃፉን ተያያዝኩት፡፡
የከሸፈ ጥረት
ጥንት ጀምሮ ከአውሮፓም ሆነ ከእስያ የተለያዩ ግንኙነቶችን እንዳትመሰርት እንቅፋት የነበሩት ምክንያቶች ለረጅም ዘመናት ሳይወገዱ ቆይተዋል። ግብፅ፤ በድሮው ዘመን የኢትዮጵያ መልዕክተኞች ወደ አውሮፓ እንዳይሻገሩ ስታደርግ ኖራለች፡፡ ይህን በማድረግ ቢያንስ-ቢያንስ 70 በመቶው የውሃ ሐብታችን በአባይ ተፋሰስ የሚገኝ በመሆኑ በዚህ ሐብታችን እንዳንጠቀም አድርጋን ቆይታለች፡፡  በነገራችን ላይ፤ አሁን የግብፅ መንግስት እና ህዝብ እያሳዩት ላሉት የተለየ ዝንባሌ አክብሮቴ ክፍ ያለ መሆኑ እንደተጠበቀ፤ ግብፅ መንገድ መከልከል የማይቻልበት ዘመን ከመጣ በኋላም፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የፋይንስ ምንጭ ሊሆኑ ከሚችሉ አበዳሪ ተቋማት እና ሐገራት በር ላይ ቆማ እንደ ውሻ እየተናከሰች አላሳልፍ ብላ ቆይታለች፡፡ ኢትዮጵያ የድረሱልኝ ጥሪም ሰሚ እንዲያጣ በማድረግ ‹‹የተሳካ ሥራ›› ሰርታለች፡፡
የታሪክ ፀሐፊዎች እንደሚሉት፤ በጥንታዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ለታየው ስልጣኔ ምንጭ የነበረው እና በቀይ ባህር አካባቢ ለነበረው ንግድ ዋነኛ ሞተር ሆኖ ያገለግል የነበረው የምፅዋ ወደብ ነው፡፡ ይህ ወደብ በኢትዮጵያ እጅ በነበረበት ጊዜ፤ ሐገሪቱ ከዓለም ጋር የጠበቀ ትስስር እንደነበራት የሚገልፁት እነኚህ የታሪክ ፀሐፊዎች፤ የምፅዋ ወደብን በእጇ ማቆየት በተሳናት እና በተለያዩ ኃይሎች በተነጠቀች ጊዜ፤ ከዓለም ተነጥላ ኋላ ቀር ሐገር እየሆነች እንደመጣችም ይናገራሉ፡፡
ስለዚህ፤ በጠላት ዓይን በሚመለከቷት ጎረቤቶች ዙሪያዋን የተከበበችው ኢትዮጵያ፤ ከሥልጣኔ ማማ ወርዳ የድህነት እና የኋላ ቀርነት ማጥ ውስጥ ተዘፈቀች፡፡ ነባሩ የሐገሪቱ የአስተዳደር ህግ እና ስርዓት ፈርሶ፤ በምትኩ ስርዓት አልበኝነት ነገሰባት፡፡ የህግ እና ስርዓት እጦቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው ደግሞ በዘመነ-መሳፍንት ወቅት ነበር፡፡ ለብዙ ዘመናት፤ ሐይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ መነሻ ባለው የእርስ እርስ ጦርነት እየደቀቀች፤ ህዝቧም ኋላ ቀር እና ድሃ ሆኖ ዘመናትን ገፋ፡፡
በዚህ ሁኔታ፤ የዘመናዊት ኢትዮጵያ መስራች ከሚባሉት አፄ ቴዎድሮስ ዘመን የደረሰችው ኢትዮጵያ፤ በእሳቸው ዘመን፤ በእኔ እበልጥ - እኔ እበልጥ ይፋለሙ በነበሩ መሣፍንት ጦርነት በእጅጉ የተዳከመች እና እንደ ተራበ አንበሳ አፍሪካን በቅኝ ግዛት ለመቀራመት ባሰፈሰፉ ኃያላን መንግስታት የተከበበች ሐገር ሆነች። ታዲያ ለዘመናዊት ኢትዮጵያ ፈተና የነበሩት ችግሮች፤ በቅርፅ ወይም በመከሰቻ መልክ የተለያዩ መስለው ቢቀርቡም፤ በመሠረታዊ ይዘት ሳይለወጡ ሐገሪቱን ሰንገው እንደያዟት እስከ ሃያኛው ምዕተ ዓመት ማብቂያ ድረስ ዘልቀዋል፡፡
አንዳንዴ፤ ተፈጥሞ ለመናገር የማያመች ነገር ሲያጋጥመን፤ ‹‹እንዳልምል ይህን አድርጎልኛል ወይም እንዲህ ሆኗል›› እንደምንለው፤ በጥቅል መናገርን የሚከለክሉ በዓይን የሚታዩ የታሪክ ቅርሶች ቢኖሩም፤ ያለፈውን ‹‹ሻመት›› (ጋዜጠኞች ‹‹ምለኒየም›› ወይም ሺህ ዓመቱን (ሻመቱን) ምዕተ ዓመት አሉት፤ እናም በስህተት ሁሉም የMGDን ግቦችን ‹‹የምዕተ ዓመቱ ግቦች›› ይላል)፤ ያለፈውን ‹‹ሻመት›› እንደ ገደል ናዳ ከሥልጣኔ አምባ ቁልቁል እየተንከባለልን ወርደን፤ ከውርደቱ የመጨረሻ ዝቅታ የደረስነው፤ ዘመነ-መሣፍንት በምንለው የታሪካችን ምዕራፍ ነው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ፤ የቁልቁለት ጉዞውን ሊገቱት ባይችሉም፤ ቢያንስ ቁልቁል እየተጓዝን መሆኑን በመረዳት፤ የሚያስቆጭ እና ልብን የሚያደማ፤ እንደ ተውኔት ለሚመለከተው ሰው አሳዛኝነቱ ጎልቶ የሚታይ ትራጀዲያዊ ፍፃሜ ያለው ጥረት አድርገዋል። አፄ ቴዎድሮስ፤ ‹‹ኤዲፐስ ንጉስ›› በተሰኘው ተውኔት ውስጥ እንደምናየው ያለ እንቆቅልሽ ገጥሟቸው ነበር፡፡
እናም፤ ታሪክ እያንከባለለ አምጥቶ ከፊታቸው የጣለውን ያን እንቆቅልሽ እንዲፈቱ ሲጠየቁ፤ ልዩ ችሎታ እንዲላበስ እንደ ተደረገ ጀግና ገፀ ባህርይ፤ ከዘመኑ ማህበረሰብ ላቅ ያለ አመለካከት እና መንፈስን ተላብሰው እንቆቅልሹን ለመፍታት ሲክሩ እናያለን፡፡
አፄ ቴዎድሮስ፤ የብዙ ታሪክ ፀሐፊዎችን እና የሐገራችንን ደራሲያን ልብ መማረክ የቻሉት በታላቅ ራዕያቸው እና ለህዝባቸው በነበራቸው ፍቅር የተነሳ ነበር። አፄ ቴዎድሮስ የሐገሪቱ አንድነት ማጣት፣ የተንሰራፋው ድንቁርና፣ መሣፍንቱ የሚያደርሱት በደል፣ የህዝቡ ሞራል መውደቅ፣ በዙሪያቸው ያንዣበበው ሐገራዊ ህልውናን የሚያጠፋ አደጋ በሙሉ ታይቷቸው ነበር። ሐገሪቱ ይህን ከባድ ፈተና ማለፍ የምትችለው በአንድ ብቸኛ መንገድ መሆኑንም ተረድተው ነበር፡፡ በአጭሩ፤ መንገዱ ሥልጣኔ እና ጥበብ በሚል ሊገለፅ ይችላል፡፡
ከፍ ሲል የጠቀስኳቸው የጋዜጠኞችን የጦርነት ዘገባ አቀራረብ ታሪክን ለመመርመር የሞከሩት ምሁር፤ በአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ምዕራፍ የያዘውን እና ሰባት ወራት የፈጀውን የመቅደላ ዘመቻ መሠረት አድርገው ካቀረቡት ጥናት የተረዳሁት ነገር፤ አፄ ቴዎድሮስ፤ ችግሩ እና መፍትሔ ፍንትው ብሎ ቢታያቸውም፤ መፍትሔ ካሉት ነገር የሚያደርሳቸውን ጎዳና መለየቱ አልተሳካላቸውም፡፡
ነገሩን፤ ከግል ባህርይ እንከን የመጣ ውድቀት አድርጎ ለማየት የሚገፋፉ ጉዳዮች ብዙ ቢሆኑም፤ እንደኔ አስተሳሰብ የወቅቱ ሐገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች፤ በ‹‹ፈላስፋ ንጉስ›› ብህልነት እና አስተዋይነት ላይ የማፌዝ ብቃት የነበራቸው ከባድ ችግሮች መሆናቸውን መዘንጋት አይኖርብንም፡፡ ሐገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶቹ፤ ድንቃይ እንደሚሉት የተውኔት ዘውግ፤ በሰው ህይወት የመዘባበት ብቃት የያዙ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡
የሆነ ሆኖ፤ ፕላውዴን ስለ አፄ ቴዎድሮስ ሰብዕና እና የመሪነት ባህርይ ያለውን ግምገማ በገለፀበት ደብዳቤ፤ ‹‹...ምናልባት አንዳንድ ሐሳቦቻቸው ላይ ችግር ሊስተዋል ይችላል፡፡ አንዳንዶቹም ተፈፃሚ ሊሆኑ የማይችሉ ከንቱ ቀዠቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሆኖም፤ ከሐበሻ የድንቁርናና የልጅነት ደመና ውስጥ ብቅ ያለው ይህ ሰው፤ አንዳች ረዳት እና መካሪ ሳይኖረው ብዙ ትላልቅ ጉዳዮችን ማከናወን የቻለ ሰው ነው፡፡ አሁንም ሊሰራቸው የሚያስባቸው ትላልቅ ዕቅዶች እና ውጥኖች ያሉት በመሆኑ፤ ሰውዬው የተለመደ ተራ ሰብዕና ያለው አይደለም›› በማለት ፅፎ ነበር፡፡      (ይቀጥላል)

Read 5421 times