Saturday, 04 July 2015 10:26

ጀርባችን ሳይሰበር፣ ሰማይ የወጣውን…

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ብዙ የናፈቁን ዜናዎች አሉ!

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሁለቱ ልጆች እያወሩ ነው፡፡ አንደኛው ልጅ ምን ይላል… “አባዬ የሁሉም ነገር ዋጋ እየጨመረ ነው ሲል ሰማሁት፡፡”
“ምንድነው የጨመረው?”
“የምግብ፣ የልብስ፣ የቤት ኪራይ ሁሉ ጨምሯል አለ፡፡ ደግሞ ምን አለ መሰለህ!”
“ምን አሉ?”
“የሆነ ነገር ቁጥሩ ቀንሶ ማየት ጓጉቻለሁ አለ፡፡”
ጓደኝየው ምን ቢለው ጥሩ ነው… “ግዴለም፣ የአንተን ሰርተፊኬት ሲያዩ በደንብ የሚቀንስ ቁጥር ያገኛሉ፡፡
ሀሳብ አለን…የኑሮ ማስተካከያ ይደረግልን፡፡ ልክ ነዋ…ለምንም ነገር ማስተካከያ ይደረግ የለም አንዴ!
እናላችሁ…ሥጋ እንኳን በሩብ ኪሎ መሸጥ መጀመሩን ወዳጄ ሲያጫውተኝ ነበር፡፡ እየደረስን ያለንበትን ዘመን እዩልኝማ፡፡ ገና በኪሎና በግራም መለካቷ ቀርቶ በጉርሻ ሊሆን ይችላል፡፡ “ሁለት ጉርሻ ሥጋ ስጠኝ…” ማለት እንጀምር ይሆናል! አይሆንም የሚባል ቃል እየጠፋ ያለባት አገር ነቻ!
እናማ…የኑሮ ማስተካከያ ይደረግልን፡፡
ስሙኝማ…በቲቪ ላይ እኮ የምግብ አሠራር እያየን መጎምጀት ከተውን ከረምን፡፡ ልክ ነዋ… ቦምቦሊኖ ባረረብን ዘመን የምናየው ሁሉ እንቁልልጭ ሆነብና!
የምር ግን… አለ አይደል… የፈጠራ ጊዜ አሁን ነው። በሬድዮና በቲቪ ስለምግብ አሠራር የምታስተምሩን ፈጠራ ቢጤ ጨምሩበታ፡፡ ለምሳሌ ‘ያለበርበሬ ቀይ ወጥን መሥሪያ ዘጠኝ ዘዴዎች’ አይነት ነገር። ደግሞላችሁ… ‘ሹሮ ሽንኩርትና ዘይት ሳይገባባት ውሀና ሹሮዋ ብቻ ተበጥብጠው ጣት የሚያስቆረጥም ወጥ የመሥሪያ ምስጢሮች…’ የሚል ፈጠራ፡፡ ልክ ነዋ…ትንሸ ቆይተን ጣት የምንቆረጥመው ምግብ ስለጣፈጠን ሳይሆን ጉርሻችን ከማነሷ የተነሳ ጣት እየተቀላቀለችብን ሊሆን ይችላል፡፡
ሀሳብ አለን…የምግብ አሠራር የቲቪ ትምህርቱ በመደብ ይከፋፈልልን፡፡ አለ አይደል…
‘በወር አንዴ ሥጋ ለሚበሉ…’
‘በወር አንዴ ሥጋ በህልማቸው ለሚያዩ…’
‘በወር አንዴ ሥጋ የሚባለው ቃል መዝገበ ቃላት ላይ መኖሩ ትዝ ለሚላቸው…’  በሚል መደብ ይከፋፈልልን። ወይንም እንደ ግብር ከፋዮች ‘ሀ’ ‘ለ’ እና ‘ሐ’ ተብለን እንከፋፈል፡፡፡ “የዛሬው የምግብ አሠራር ለ‘ለ’ ምድቦች ብቻ የሚሆን ነው…” ስንባል ቁርጣችንን አውቀን አርፈን እንቀመጣለና!
እናላችሁ… ዘንድሮ… አለ አይደል… “አንተ ምነው ባለቤትህ ከሳችብኝ!” ብሎ አስተያየት አሪፍ አይደለም። አሀ…ነገርዬው ሁሉ ‘ጣራ ነክቶ’ እንዴት ትወፍር! በፊት እኮ “በሽታ እንኳን ያወፍራል…” ይባል ነበር፡፡ ዘንድሮ ኩሽናው ሁሉ ምነዋ ይሄን ያህል መአዛ የለውሳ!
እናማ… “አንተ ምነው ባለቤትህ ከሳችብኝ!” ብሎ አስተያየት ‘ወቅቱን ያላገናዘበ’ ይሆናል፡፡ አሀ… በብር ሦስትና አራት ይገዛ የነበረ እንቁላል አንዱ ሦስት ብር ከሀምሳ ሳንቲም ምናምን ሲሆን እንዴት ሆና ‘ሥጋ’ ታውጣ፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ባል ራሱ ‘አርፎ አይቀመጥ’!  ቂ…ቂ…ቂ….
እኔ የምለው…“ዳየት ላይ ነኝ…” ምናምን የምትሉ እንትናዬዎችን ሌላ ሰበብ አምጡማ፡፡ ኑሮ ራሱ ሁላችንንም ‘ዳየት ላይ’ አድርጎናላ! እናማ…‘ዳየት ላይ’ መሆኑ የግዴታ እንጂ የውዴታ ባልሆነበት…“ዳየት ላይ ነኝ…” አይነት ምክንያት አይሠራም፡፡
ስሙኝማ…በፊት የሆነ ነገር ዋጋው ጣራ ነካ ሲባል የሆነ መሥሪያ ቤት ለ‘ፐብሊክ ኮንሰምሺን’ ለሚሉት ነገርም ቢሆን… “የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ሥራዎች እየተሠሩ ነው…” ምናምን  የሚባለው ‘ልብ አንጠልጣይ ልብ ወለድ’ እንኳን አሁን፣ አሁን እየቀነሰ ነው፡፡
“እነሱ አንድ ነገር ያደርጉልናል…ዋጋውን ወደ ቦታው መልስው ያረጋጉልናል…” ስንል ተስፋ ቆረጡ እንዴ! አሀ…ወንበር ብቻ ሳይሆን ዋጋም ይረጋጋልና!
እናማ…“በተለይ በምግብ ሸቀጦች ላይ የሚደረገውን ምክንያተ ቢስና ኢፍትሀዊ ዋጋ ንረት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስተካከል የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ሊጀመር ነው…” አይነት ዜና መስማት ናፍቆናል፡ ልከ ነዋ…በሆዳችን ‘ድንቄም ተወሰደ!’ ብንል እንኳን ለጊዜውም ቢሆን ለጆሯችን አሪፍ ዜማ ይሆናላ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ልንሰማቸው የናፈቁን ዜናዎች መአት ናቸው…
‘ከወሩ መግቢያ ጀምሮ በመላ አገሪቱ የጤና አገልግሎት ሙሉ፣ ለሙሉ ነጻ ሆኗል…’
‘ከመጪው ሰኞ ጀምሮ አንድ ኩንታል ጤፍ ከአምስት መቶ ብር በላይ ሲሸጥ የተገኘ ነጋዴ ፈቃዱ ተነጥቆ ከመፋቂያ በላይ የሆነ ምርት እንዳይሸጥ የአራተ ዓመት እገዳ ይጣልበታል…’
‘በበዓላት ወቅት ቀበሌዎች ቤት ለቤት እየዞሩ ኪሎ ቅቤ በሀያ አምስት ብር ማከፋፈል ይጀምራሉ…’
‘የአንድ ኪሎ በርበሬ ከፍተኛ ዋጋ አሥራ አምስት ብር ከሃያ አምስት ሳንቲም እንዲሆን እንትን መሥሪያ ቤት ወሰነ…’
‘ከፍተኛ ባለስልጣኖች በአሥራ አምስት ቀን አንድ ጊዜ መርካቶና ሾላ ገበያ እየሄዱ ራሳቸው እንዲገበዩ የውዴታ ግዴታ ተጥሎባቸዋል…’ (ያን ጊዜ…አለ አይደል…“እንዲህም የሚኖር ሰው አለ!” ይሉ ነበር፡፡)
እንደ እነዚህ አይነት ‘ዜናዎች’− “ካልተረጋገጡ የወሬ ምንጮች…” እንኳን− የምንሰማበት ዘመን ይመጣ ይሆን! መመኘትም የ‘ክላስ’ ጉዳይ እስኪሆን ድረስ እኛም እንመኝ እንጂ!
ካነሳነው አይቀር…ሌሎች የናፈቁን ዜናዎች አሉ…
‘እንትንና እንትን ድርጀቶች ከእንግዲህ መዘላላፍና ትርፍ ቃላት መወራወር ትተው ቁም ነገር ላይ ለማተኮር ተስማምተዋል…’
‘ባለስልጣኖች ለሜዲያ መግለጫ በሚሰጡበት ጊዜ የማስፈራሪያና የንቀት ቃላት ሲናገሩ ቢገኙ የተሰጣቸውን ወንበርና የተሰጣቸውን ቤተ ይነጠቃሉ…’ (ቂ…ቂ…ቂ…. ታየኝ!)
‘በሆነ ባልሆነው ትንሹንም ትልቁንም የሚዠልጡ ስነ ስርአት አስከባሪዎች በእጃቸው አርጩሜ እንኳን እንዳይዙ ይከለከላል…’
አሪፍ አይደል! ያኔ እንዴት አይነት ‘ነፍስ የሆንን’ ሰዎች ይወጣን ነበር፡፡
ደግሞላችሁ ሌሎች የናፈቁን ዜናዎች አሉ…
‘የሰው ሚስት የሚያማግጥ ጭቃ ሹም ሆነ ምስለኔ አይደለም ሴት፣ የሴት ፎቶ የማያይበት በረሀ ለአምስት ዓመት እንዲቀመጥ ይገደዳል…’
‘ሥራ አስኪያጆች ኤክሲኪዩቲቭ ሴክሬታሪዎችን ፊት ለፊት በአካል ሳይሆን በስልክ ብቻ እንዲያገኙ ተወሰነ…’ (ቂ…ቂ…ቂ…)
‘በየመጠጥ ቤቱ መቶና መቶ ምናምን ብር ለመክፈል የመለስተኛ መሥሪያ ቤት ተከፋይ ደሞዝ የሚመስል የብር መአት የሚመዙ ሰዎች ሌላው ተገልጋይ ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም የብሽቀት፣ የመጎምጀት፣ የደም ብዛት ችግር ሁሉ ተጠያቂ ይሆናሉ…’
‘ከእንትናዋ ጋር የምትሄደውን እንትናዬ ከሦስት ሰከንድ በላይ ትክ ብለው የሚያዩ ባለመኪኖች መኪናቸውን ተነጥቀው ለአሥራ አንድ ወር በእግራቸው ብቻ እንዲሄዱ ይደረጋሉ…!’ የሚል ዜና ናፍቆናል፡፡ (እግረኞቹ ሁሉ እየተሳቀቁ አሳዘኑና!)
መአት ልንሰማቸው የምንፈልጋቸው ዜናዎች አሉ፡፡ “ሰበር ዜና…ዋጋዋ አልቀምስ ብሎ ሃያ ምናምነኛ ፎቅ ላይ የወጣችው ቲማቲም አንድ ኪሎ በብር ተሀምሳ እንደገባች ተገለጸ…” አይነት ዜና መስማት ናፍቀናል፡፡
“ከፍተኛ የአገሪቱ ባለስልጣናት በመርካቶ፣ በአትክልት ተራና በሾላ ገበያ ባደረጉት ጉብኝት ባዩት የምግብ ግብአቶች ዋጋ ከፍተኛ ድንጋጤ እንዳደረባቸው ምንጮቻችን ገለጹ፡፡ በተለይ አንዱ ባለስልጣን… ‘ኑሮ ይህን ያህል መክበዱን በህልሜም ጠርጥሬ አላውቅም፡፡ ዕንባዬ ነው የመጣው…’ ማለታቸው ተዘግቧል…” አይነት ዜና ናፍቆናል፡፡
የኑሮ መክበድን በተመለከተ ብዙ ልንሰማቸው የምንፈልጋቸው ዜናዎች አሉ፡፡
የከበደውን ኑሮ የሚያቀልልን ዘመን ያፍጥልንማ!
ጀርባችን ሳይሰበር፣ ሰማይ የወጣውን የሸቀጦች ዋጋ የሚሰብር ተአምር ይላክልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2806 times