Saturday, 04 July 2015 09:27

መድረክ ለጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደብዳቤ ፃፈ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

በምርጫ ማግስት እየተፈፀመ ያለው ወከባና
እንግልት እንዲቆም የሚጠይቅ ነው ተብሏል

     የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ በአባላቱና መድረክን በመረጡ ዜጎች ላይ እየደረሰ ነው ያለው ወከባና እንግልት በአስቸኳይ እንዲቆም የሚጠይቅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መፃፉን አስታወቀ፡፡ ከምርጫው በፊት በሃገራዊ ጉዳይ ላይ ለመወያየት የሚጠይቅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገብቶ ምላሽ እንደተነፈገው ለአዲስ አድማስ የገለፁት የመድረክ ሊቀመንበር ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ የአሁኑ ደብዳቤ በአባላቱና መድረክን በመረጡ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ወከባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ባላቸው ኃላፊነት በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡ በምርጫው ማግስት በኦሮሚያ ክልል አቶ ጊደሳ ጨመዳና አቶ ገቡ ጥቤሶ የተባሉ የመድረኩ አባሎች መገደላቸውንና በክልሉ በርካታ አባላት በየፖሊስ ጣቢያውና በየወህኒ ቤቱ መታጎራቸውን፣ በትግራይም የአረና መድረክ አመራር አቶ ታደሰ አብርሃ እንዲሁም በደቡብ የመድረኩ የምርጫ ታዛዚ የነበሩት አቶ ብርሃኔ ኤረቦ መገደላቸውን የጠቀሰው የመድረክ ደብዳቤ፤ በርካታ አባላትና ደጋፊዎች በየክልሎቹ በእስር ላይ እንደሚገኙ፣ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑ አባሎችም ደሞዛቸው እየታገደና ከስራ እየተባረሩ መሆኑን ይገልፃል፡፡ በብዙ አካባቢዎችም በመድረኩ የምርጫ ተወካዮች ላይ ድብደባ፣ የግድያ ሙከራና ከቤት ንብረት የማፈናቀል እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ደብዳቤው ጠቁሟል፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች “ኢህአዴግን ለምን አልመረጣችሁም” በሚል በዜጎች ላይ ከፍተኛ ወከባ እየተፈፀመ ነው ያሉት ፕ/ር በየነ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባላቸው ከፍተኛ ሃገራዊ ኃላፊነት ድርጊቱን እንዲያስቆሙ በመድረኩ ስም ጠይቀዋል፡፡  “የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ
ሰኔ 15 ይፋ ያደረገውን የምርጫ ውጤት ሰፊው ህዝብ አልተቀበለውም” የሚለው ደብዳቤው፤ መድረክን በመረጡ ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ወከባና እንግልት ለቦርዱ በተደጋጋሚ በደብዳቤ ቢያሳውቁም ቢሞከርም ቦርዱ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ እንዳለፈው ጠቁሟል፡፡ መድረክ ከምርጫው በፊት ከመንግስት ጋር መወያየት እንደሚፈልግ ጠቅሶ ጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የጠየቀው ቀጠሮ በቸልታ መታለፉ፣ ከምርጫው በኋላ ለተከሰቱት ችግሮች አስተዋፅኦ ማበርከቱን ፕ/ር በየነ ተናግረዋል፡፡  

Read 1752 times Last modified on Saturday, 04 July 2015 09:54