Saturday, 27 June 2015 10:17

የብሩንዲ ም/ፕሬዚዳንት አገር ጥለው ተሰደዱ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 መንግስት ም/ፕሬዚዳንቱ ከአገር የወጡት ለስራ ጉዳይ ነው ብሏል

   የብሩንዲው ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ፤ ህገ መንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጭ በቅርቡ በሚካሄደው የአገሪቱ ምርጫ ለሶስተኛ ዙር ለመወዳደር መወሰናቸውን በመቃወማቸው ከመንግስት አካላት ማስፈራሪያ እየተደረገባቸው እንደሆነ የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጌርቪያስ ሩፊኪሪ፣ ለህይወታቸው በመስጋት አገር ጥለው መሰደዳቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የአገሪቱ መንግስት ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ምክትል ፕሬዚዳንቱ ከአገር የወጡት ለስራ ጉዳይ ነው፤ ምንም አይነት ማስፈራሪያ አልተደረገባቸውም ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ዘንድሮም በምርጫ እንደሚወዳደሩ መግለጻቸውን ተከትሎ፣ በአገሪቱ የተቀሰቀሰው ግጭት እየተባባሰ ነው፤ የህዝቡ ተቃውሞም እንደቀጠለ ነው፤ ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጌሪያስ ሩፊኪሪ፣ መንግስት በሌሎች ተቃዋሚዎች ላይ እንደሚያደርገው ሁሉ በእኔ ላይም ዛቻና ማስፈራሪያ እያደረገብኝ ስለሆነ አገሬን ጥዬ ተሰድጃለሁ ብለዋል ከፍራንስ24 የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፡፡
በቅርቡም የብሩንዲ የህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ፍርድ ቤት ዳኛ እና የምርጫ ኮሚሽን አባልን ጨምሮ ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛን ውሳኔ በመቃወም አገር ጥለው መሰደዳቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ በመጪው ሐምሌ ወር አጋማሽ ላይ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የብሩንዲ ምርጫ ሳቢያ የተቀሰቀሰውን ግጭትና የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ፣ የብሩንዲን ገዢ ፓርቲና ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማደራደር እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ዘገባው ጨምሮ ገልጧል፡፡
የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶችም ላለፉት ሁለት ወራት በአገሪቱ ፖሊስና በተቃዋሚዎች መካከል በተደረጉ ግጭቶች፣  ከ70 በላይ ዜጎች መሞታቸውንና 500 ያህልም መቁሰላቸውን አስታውቀዋል ብሏል ዘገባው፡፡

Read 3187 times