Saturday, 27 June 2015 10:16

በፓኪስታን በሙቀት ሳቢያ ከ700 በላይ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 በፓኪስታን በተከሰተው ከመጠን ያለፈ የሙቀት አደጋ ከሰባት መቶ በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ሲኤንኤን ከዋና ከተማዋ ካራቺ የዘገበ ሲሆን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ናዋዝ ሸሪፍ የአስቸኳይ የአደጋ ጊዜ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ሙቀቱ በድንገት የመታት የመጀመሪያዋ ከተማ፣ ከፓኪስታን በደቡባዊ አቅጣጫ የምትገኘዋን የሲንድ ግዛትን ነበር፤ ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ ላይ፡፡ ወሩ በእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ የሮመዳን ፆም  የተያዘበት እንደመሆኑ አደጋው እጥፍ ድርብ ችግሮችን እንዳስከተለ ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡  ህይወታቸውን በሙቀቱ ያጡት ሰለባዎች ቁጥር የአስከሬን ማቆያዎች ከሚቀበሉት በላይ በመሆኑ ሆስፒታሎች በሬሳ ተጨናንቀው በዜና ማሰራጫዎች ታይተዋል፡፡  እስከ ትላንት በስቲያ ድረስ ወደ 750 የፓኪስታን ዜጎች ሲሞቱ፣ ከሺ በላይ የሚገመቱት ደግሞ ከሙቀቱ ጋር በተያያዘ እንደ ሀይለኛ ትኩሳትና የሰውነት ፈሳሽ ድርቀት (Dehydration) መሰል የጤና ቀውሶች ተጠቅተው፣ አስከፊ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሙቀቱ አደጋ ከፍተኛ የህይወት መጥፋት ያስከተለው በሀገሪቱ ትልቅ በምትባለው የካራፒ ከተማ ሲሆን ወደ ስድስት መቶ ነዋሪዎችም ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
ከአደጋው ጋር በተያያዘ በተከሰተ የትራፊክ መጨናነቅ ሳቢያ ነዋሪዎች  የሟች ዘመዶቻቸውን አስከሬን ወደ ቀብር ቦታ ለማድረስ መቸገራቸውን ገልፀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሀይል እጥረት ምክኒያት እየተዛባ ይዳረስ የነበረው የውሀ አቅርቦት ጊዜያዊ መፍትሄዎች እንዳይወሰዱ አድርጓል። አንዳንድ ነዋሪዎች የተከሰተውን ሙቀት በውሀ ለማብረድ ቢፍጨረጨሩም  … በከተማው ያሉ የውሀ መስመሮች በመሰባበራቸው መፍትሄ ሊሆኑዋቸው አልቻሉም፡፡ የፓኪስታን ክልል አስተዳዳሪ ከዌም አሊ ሻህ፤ የሙቀቱ አደጋ ጋብ እስከሚልበት ጊዜ ድረስ ትምህርት ቤቶችና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተዘግተው እንዲቆዩ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ አስተዳዳሪው ለተቀጠፉት ነፍሶች ተጠያቂው መንግስት እንደሆነም ሲገልጹ፤ “ሀይል ማሰራጫ መስመሮች እንዲታደሱ አስቀድመን ብንወተውትም፣ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ምላሽ ባለመስጠታቸው አደጋው ከመጠን ያለፈ ጥፋት አድርሷል” በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

Read 1904 times