Saturday, 27 June 2015 09:32

የእስራኤሉ ኬሚካል ኩባንያ አላና ፖታሽን ገዛ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

     ለእርሻ አስፈላጊ የሆኑ ማዕድናት፣ በምግብና በኢንጂነሪንግ ጥበብ ዲዛይን አድርጎ ከፋብሪካ በሚሰራቸው ሸቀጦች አምራችነት በመላው ዓለም የሚታወቀው Israel Camical Limited (አይሲኤል) ኩባንያ በአፋር ክልል በፖታሽ ማዕድን ፍለጋ የተሰማራውን አላና ፖታሽ ኩባንያ መግዛቱን አስታወቀ፡፡
አይሲኤል ኩባንያ በሳምንቱ መጀመሪያ በቴልአቪቭ እስራኤል ባወጣው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ በፖታሽ ምርት ልማት የተሰማራውን የካናዳውን የማዕድን ከባንያ አላና (“Allana”) በእጁ ማስገባቱን ጠቅሶ፣ ሽያጩም በካናዳ ጠቅላይ ፍ/ቤትና በአላና ኩባንያ የአክሲዮን ባለቤቶች መፅደቁን ገልጿል፡፡ አይሲኤል አላናን ንብረቱ ያደረገው ለ83.78 በመቶ ድርሻ 137 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር በመክፈል ሲሆን ቀደም ሲል በ2013 ለ16.22 በመቶ የአላና ድርሻ 25 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር ገዝቶ እንደነበር በመግለጫው ገልጿል፡፡
አላና በአፋር ክልል በደናክል አካባቢ የፖታሽ ማዕድን ለማውጣት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተዋውሎ እንደነበር የሚታቅ ሲሆን በ2013 ፌብሩዋሪ በተጠናቀቀው የአዋጪነት ጥናት መሰረት፣ ፕሮጀክቱ ለ25 ዓመታት በየዓመቱ እስከ አንድ ሚሊዮን ቶንስ ሙሪዬት ፖታሽ ማምረት የሚያስችል ክምችት እንዳለው ገልፆ እንደነበር መግለጫው አመልክቷል፡፡
አይሲኤል አላናን ሙሉ በሙሉ መረከቤ፣ በደናክል የማደርገውን የማዕድን ቁፋሮ ልማት ለማፋጠን ይረዳኛል ብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱን የቴክኒክና ትግበራ ጥናት የጀመረ ሲሆን ጥናቱም፣ ሎጀስቲክስ፣ መሰረተ ልማትና ለምርት አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች የደናክልን የፖታሽ ክምችት በሚገባ መጠቀም የሚቻልበትን ሂደት፣ ክምችቱ ያለበትን ስፍራ እንዴት ማሳደግ እንደሚቻልና አስተማማኝ የገንዘብ ምንጭ የሚገኝበትን መንገድ ያካትታል፡፡
በአገሪቷ ከፍተኛ የማዕድን ቁፋሮ ሲጀመር ለአጠቃላይ የአገሪቷ ጂዲፒ ዕድገት፣ ወደ አገር ለሚገባ የውጭ ምንዛሬ፣ ከታክስ ለሚገኝ ገቢ፣ በቀጥታ፣ ሆነ በተዘዋዋሪ ለአፋር አካባቢ የሚፈጠረውን የሥራ ዕድል… ለረዥም ጊዜ የሚያገለግል መሰረተ - ልማት ለኢኮኖሚው የሚያበረክተውን ጥቅም የኢትዮጵያ መንግስት እንደሚረዳ የጠቆመው አይሲኤል፣ በአፋር ክልል ለምንጀምረው መሰረተ ሰፊ የማዕድን ቁፋሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ውሃ፣ መብራትና መንገድን ጨምሮ የተፈጥሮ ሀብትና መሰረተ ልማት ያሟላል የሚል እምነት አለን ብሏል፡፡  መሆኑን ማወቅ አለበት በማለት አስገንዝቧል፡፡
አይሲኤል የአክሲዮን ድርሻው በኒውዮርክና በቴልአቪቭ ስቶክ ኤክስቼንጅ አስመዝግቦ በመላው ዓለም፣ በእንግሊዝ፣ በስፔይን በእስራኤል፣ በኤስያ ገበያዎችና በአፍሪካ የሚንቀሳቀስ የቢዝነስ ኩባንያ ሲሆን፣ 12,500 ያህል ሰራተኞች እንዳሉት ይገመታል። ባለፈው ዓመት ከምርቶቹ ሽያጭ በአጠቃላይ 6.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱ ታውቋል፡፡

Read 1580 times