Saturday, 27 June 2015 09:25

በተከበረው የረመዳን ወር ላይ የወረደው ቁርአን

Written by  ኑርሁሴን
Rate this item
(22 votes)

       በፈርኦን ዘመን የነበሩ ህዝቦች ለአስማት ጥበብ (Magic) ያላቸው አወንታዊ አመለካከት በጣም ከፍተኛ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን ለአስማተኞች የሚሰጡት አድናቆትና ከበሬታ ሲበዛ ልዩ ነው፡፡ ከዚያም ነበር አምላክ ሙሴን ወደ ህዝቡ ሲልከው፣ ቅድሚያ የአስማት ጥበብን የሰጠው፡፡ አምላክ ይህን ጥበብ ለሙሴ መስጠቱ የወቅቱን ህዝብ ቀልብ ለመግዛት የሚያስችል መሳሪያ መሆኑን በማወቁ ነው፡፡
ሙሴ የተሰጠውን የአስማት ጥበብ ተላብሶ ወደ ፈርኦን ህዝብ ሄደ፡፡ ፈርኦን ግን ማንንም በአስማት ጥበባቸው ማዋረድ የሚችሉ፣ እሳት - የላሱ አስማተኞችን ሰብስቦ ከሙሴ ጋር አጋፈጣቸው። የሙሴ ሀቀኝነት የሚረጋገጠው (አምላክን ተገዙ የሚለው) አስማተኞቹን መርታት ከቻለ ብቻ እንደሆነ ፈርኦን በአደባባይ አወጀ፡፡ በመሆኑን በሙሴና በአስማተኞቹ መካከል ውድድር ለማድረግ ቀጠሮ ተያዘ፡፡ ህዝቡ በዚህ ልዩ ውድድር ላይ እንዲገኝ ግብዣ ተደረገለት፡፡ የቀጠሮው ቀን እንደደረሰ የግብፅ ህዝብ ንቅል ብሎ በመውጣት  ክቡን የውድድር ሜዳ አጨናነቀው፡፡ ፈርኦንና የርሱ የቅርብ ባለስልጣናት የክብር ቦታቸውን ያዙ፡፡ ሙሴና አስማተኞቹ ብትራቸውን እንደያዙ እንደቆሎ በፈሰሰው ህዝብ መሐል ፊት ለፊት ተፋጠጡ፡፡
ሙሴ ጥበባቸውን እንዲያሳዩ ቅድሚያ ለአስማተኞቹ እድሉን ሰጠ፡፡ የፈርኦን አስማተኞች ህዝቡን በኩራት እየተንጎራደዱ ካዩ በኋላ የያዙትን በትር መሬት ላይ ሲጥሉት ከበትርነት              ተለውጠው የሚፍለከለኩ እባቦች ሆነው ታዩ። ይህን ትእይንት አሰፍስፎና አንገቱን አስግጎ ሲመለከት የነበረው ህዝብ በጣም ተደንቆ ጩኸቱን አቀለጠው።
ተራው የሙሴ  ነበርና እሱም የያዘውን በትር ወደ መሬት ጣለ፡፡ ትልቁ ጥበብ የታየው እዚህ ላይ ነበር፡፡ ሙሴ የጣለው በትር ወደ ትልቅ እባብ ተለውጦ የአስማተኞቹን ትንንሽ እባቦች እየለቃቀመ ዋጣቸው፡፡ በአስማተኞቹ ጥበብ ገና ተደንቆ ያልጨረሰው ህዝብ፤ ሙሴ ባሳየው ተአምር አፉን ከፍቶ ቀረ፡፡ ቀጥሎ የፈርኦንን ቆሽት እርር - ድብን ያደረገ ጭብጨባና ፉጨት ህዝቡ አሰማ፡፡ ሙሴ የህዝዱን ቀልብ መግዛት ብቻ ሳይሆን፣ አስማተኞቹ ራሳቸው ለአምላክ ለመገዛት እንዲንበረከኩ አደረገ፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ የህዝቡን ቀልብ ለመግዛት የተጠቀመው ልክ እንደሙሴ የአስማት ጥበብን አልነበረም፡፡ በሙሴ ዘመን የነበረው ጥበብ ለኢየሱስ ዘመን ህዝቦች እንደማይሰራ አምላክ ያውቃል፡፡ በኢየሱስ ዘመን የእስራኤል ህዝቦችን ይዞ ሲፈታተን የነበረው ትልቁ ነገር በሽታ ነበር፡፡ በመሆኑም ኢየሱስ የህክምና ጥበብን ይዞ መጣ፡፡ ለምጣሙን፣ ሽባውን፣ አይነ - ስውራኑን እና በሌሎች ደዌ የሚሰቃዩ በሽተኞችን በመፈወስ ህዝቡን መሳብና ማስደነቅ ቻለ፡፡ ከዚህም በላይ የሞቱ ሰዎችን በማስነሳት ትልቁን የህክምና ፈውስ አሳየ፡፡  ኢየሱስ በዚህ የህክምና ጥበቡ በርካታ ሰዎችን ተከታይ ማድረግ ቻለ፡፡
ነብዩ መሐመድ አረቦች እንዲከተሏቸው ለማድረግ ልክ እንደ ሙሴ አስማትን፣ እንደ ኢየሱስ የህክምና ጥበብን አልተጠቀሙም፡፡ በነብይ ዘመን የነበሩ አረቦች ለቋንቋና ስነ-ፅሁፍ ያላቸው ፍቅር በጣም የበዛ ነው፡፡ በዚህ ወቅት አረቦች በአደባባይ ላይ እየተሰባሰቡ የውዳሴ ግጥሞችን ያቀርቡ ነበር፡፡ እንዲሁም የንግግር ክህሎት ያላቸው አረቦች በሰዎች ዘንድ ትልቅ ከበሬታ ነበራቸው፡፡ ነብዩ መሐመድ እነዚህን ሰዎች ለመዋጋትና ወደ አምላክ ለማቅረብ የተጠቀሙት በቋንቋና ስነ- ፅሑፍ የበለፀገውን ቁርአን ነበር፡፡ በርካታ አረቦች በቁርአን ተደመው ነብዩ ይዘውት በመጡት እስልምና ውስጥ ገቡ፡፡ በቁርአን ቋንቋ፣ ስነ-ፅሁፍ እና መልእክት የተሸነፉት አረቦች፤ ቁርአን የአምላክ ስራ እንጂ በሰው ልጅ አቅም እንደማይሞከር በማረጋገጣቸው ለነብዩ አገዛዝ እጅ ሰጡ፡፡
ቅዱስ ቁርአን የወረደው አሁን በያዝነው በተከበረው የረመዳን ወር ላይ ነበር፡፡ ሙሴ ከፈርኦን ህዝቦች ጋር በአስማት ጥበብ እንደተዋጋው፣ ኢየሱስ ከበሽታና ከሞት በፈወሰው የህክምና ጥበቡ የህዝቦችን ቀልብ እንደሳበው ሁሉ፣ ነብዩ ሙሐመድም በቁርአን ቋንቋና ስነ - ፅሁፋዊ ጥበብ ከአረቦች ጋር ግብግብ ገጥመዋል፡፡ አምላክ እንደየዘመኑና እንደ ህዝቦች ፍላጎት ለሶስቱም፣ ሶስት የተለያዩ ጥበቦችን ሰጥቷል፡፡
ነብዩ ሙሐመድ በሒራ ዋሻ ውስጥ ለብቻቸው ተገልለው ለብዙ ጊዜ ስለአምላክና ስለሰው ልጆች ያስላስሉ (Meditation) ነበር፡፡ አንድ ቀን በዚህ ዋሻ ውስጥ ሳሉ፣ መላኢኩ ጂብሪል  (ገብርኤል) በሰው አምሳል ተከስቶ ወደ ዋሻው በመግባት፣ አላህ ለነብይነት እንደመረጣቸው አበሰራቸው፡፡ ከዚያም “አንብብ!” አለ ጂብሪል ለነብዩ፡፡ “እኔ ማንበብ አልችልም” ሲሉ ነብዩ በፍርሐት እየተርበተበቱ መለሱ፡፡ ጂብሪል ነብዩን ጭምቅ አድርጎ ከለቀቃቸው በኋላ በድጋሚ “አንብብ!” አላቸው፡፡ በፍርሐት የራዱት ነብዩ፤ “ማንበብ አልችልም” ሲሉ በድጋሚ መለሱ፡፡ ጂብሪል አሁንም ጨምቆና አስጨንቆ ከለቀቃቸው በኋላ ለመጀመሪ ጊዜ የወረዱን አምስት የቁርአን አንቀፆች አንብቦላቸው ተሰወረ፡፡
“አንብብ፤ በዛ ሁሉን በፈጠረው ጌታህ ስም
ሰው ከረጋ ደም በፈጠረው፤
አንብብ፤ ጌታህ በጣም ቸር ሲሆን፤
ያ በብዕር ያስተማረ
ሰውን ያላወቀውን ሁሉ ያሳወቀ፡፡”
(አል - ዐለቅ፣ 1-5)
ቁርአንን ልዩ የሚያደርገው የቋንቋ አጠቃቀሙ፣ መልእክቱና ስነ - ፅሁፋዊ ውበቱ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጅ አቅም እሱን የመሰለ መጽሐፍ ማቅረብና የማይቻልና የማይታሰብ መሆኑ ጭምር ነው። ነብዩን ሲያወግዙና ሲያስተባብሉ የነበሩት ቁረይሾች፣ ቁርአንን የመሰለ አንቀፅ አቅርበው ከነብዩ ጋር መወዳደር እንደሚችሉ አላህ መድረኩን ክፍት አደረገላቸው፤ እንዲህ በማለት፡-
“ሰዎችም፣ ጋኔኖችም የዚህን ቁርአን ብጤ ለማምጣት
ቢሰበሰቡ፤ ከፊላቸው ለከፊሉ ረዳት ቢሆኑም እንኳ፤
ብጤውን የመሰለ አያመጡም በላቸው፡፡”
(አል - ኢስራእ፣ 88)
ቁርአንን የመሰለ መጽሐፍ ማቅረብ ለአረቦች ከባድ መሆኑን ያወቀው አላህ፤ ውድድሩን ወደ አስር ምዕራፍ በማውረድ ያቀለዋል፡፡
“ይልቁንም ቁርአንን ቀጣጠፈው ይላሉን?፡- እውነተኞች እንደሆናችሁ ብጤውን የሆነ አስር የተቀጣጠፉ ምዕራፎች አምጡ፤ ከአላህ ሌላ የቻላችሁትን ረዳት ጥሩ በላቸው፡፡”
(ሁድ፣ 13)
አስር ምዕራፎችን ማቅረብ ለአረቦች ከባድ በመሆኑ አላህ አሁንም ውድድሩን የበለጠ አቅልሎ፣ አንድ ምዕራፍ አምጥታችሁ ነብዩን ተወዳደሩ ይላቸዋል፡፡
“በባሪያችን ላይ ካወረድነው (አንቀፆች) በመጠራጠር ውስጥ ከሆናችሁ ከብጤው አንዲት ምዕራፍ አምጡ፤ እውነተኞች ከሆናችሁ ከአላህ ሌላ መስካሪዎቻችሁን ጥሩ።”
(አል-በቀራህ፣23)
ጥንታዊ አረቦች በቋንቋና ስነ - ፅሑፍ የተካኑ በመሆናቸው ነብዩ ካመጡት ቁርአን ጋር ለመወዳደር ሲሉ በርካታ ስነ - ፅሑፎችን ፈብርከዋል፡፡ አልተሳካላቸውም እንጂ፡፡ ከነዚህ መካከል አንዱ ራሱን እንደ ነብይ አድርጎ በርካታ አረቦችን ያጭበረበረው ሙሳይሊማህ ይገኝበታል። ሙሳይሊማህ ልክ እንደ ሙሐመድ ለኔም ራዕይ ወርዶልኛል በማለት ስንኞችን ይቋጥር ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ የቁርአን አንቀፆችን ወስዶ በራሱ ቃላት እየተካ ያቀርባቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ የአል-ከውስር ምዕራፍን ተጠቅሞ የራሱን “ራዕይ” ፈብርኮ ነበር፡-
“እኛ በጣም ብዙ፣ በጎ ነገሮችን ሰጠንህ (የጀነት ወንዝ - አል - ከውስር) ስለዚህ ለጌታህ ስገድ፤ (በስሙ) መስእዋትም አቅርብ”
(አል - ከውስር፣ 1-3)
ሙሳይሊማህ ከላይ የቀረበችውን የቁርአን አንቀፅ እንዲህ አድርጎ ቀየራት፡-
“በእርግጥ እኛ የጀነት ቁልፎችን ሰጠንህ
ስለዚህ ለጌታህ ስገድ፣ እረፍትም አድርግ”
አንድ ቀን ጨመር ኢብን አል - አስ የተባለ የአረብ ቁረይሽ ወደ ሙሳይሊማህ ዘንድ በመሄድ “እኔ ትክክለኛው ነብይ ማወቅ ስለምፈልግ ላንተ የወረደ ራዕይ ካለ ንገረኝ?” ይለዋል፡፡ ሙሳይሊማህ፤ “በአሁን ሰዓት ለሙሐመድ የወረደ አንቀፅ ይኖር ይሆን?” ሲል ዐመርን ጠየቀው፡፡ ዐመር፤ “በጣም አጭር እና እጥር - ምጥን ያለች ምዕራፍ ወርዳለታለች” በማለት ሱራ አል-ዐስርን ያነብለታል፡-
በጊዜያት እምላለሁ
ሰው ሁሉ በእርግጥ በኪሳራ ውስጥ ነው፡፡
ከነዚያ ያመኑትና መልካም ከሰሩት፤ በእውነትም
አደራ የተባባሉት፤ በመታገስም አደራ የተባባሉት ብቻ ሲቀሩ፡፡”
     (አል - ዐስር)
ብልጣ - ብልጡ ሙሳይሊማህ ለቅፅበት አእምሮውን ካሰራ በኋላ “ለኔም እኮ ራዕይ ወርዶልኛል” አለው፡፡ የሙሳይሊማህ “ራዕይ” በግርድፍ ትርጉም ይህን ይመስላል፡-
አንቺ ዋበር ሆይ!
አንቺ ዋበተር ሆ!
ሁለቱ ጆሮ ‘ቺሺ
እንዲሁም ደረትሺ
መኖሪያ መመኪያዎችሺ
በተቀረው ኋላሺ
ከመቆፈር በቀር ምንም መላ የለሺ  
የመሳይሊማህ አጭበርባሪነት ግልፅ የሆነለት ዐመር ደንግጦ ዝም አለ፡፡ ሙሳይሊማህ ግን “ስለወረደልኝ ራዕይ ምን ታስባለህ?” ሲል የደነገጠውን ዐመር ጠየቀው። ዐመር እንዲህ አለ፡- “በጌታ ይሁንብኝ ውሸትህን ማወቄን፣ አንተ ራስህ ታውቃለህ፡፡ ወንድሜን ትቼ ወዳንተ መምጣቴ ጥፋቱ የኔ ነው፡፡” በማለት ወደ ነብዩ ሄዶ እስልምናን ተቀበለ፡፡
በእርግጥ ዐመር ቢደነግጥ ያንሰዋል፡፡ ሙሳይሊማህ በግጥሙ ውስጥ ያነሳው፣ ዋበር ስለምትባል ድመት መሳይ እንስሳ ነበር፡፡ ዋበር ትላልቅ ጆሮዎች ያሏት፣ ከኋላዋ ግን አስቀያሚ የሆነች የዱር እንስሳ ነች፡፡ ለነብዩ የወረደችው ሱራ አል - አስር ግን ስለሰው ልጆች እጣ - ፈንታ የምትናገር ነበረች። አላህ ብዙ ጊዜ ራሱ በፈጠራቸው ነገሮች ሲምል በቁርአን ውስጥ እናነባለን፡፡ ለምሳሌ፡- “በተራራዎች እምላለሁ … በፀሐይ እምላለሁ … በንፋስ እምላለሁ …” የሚሉ ገለፃዎች በሌሎች ምዕራፎች ውስጥ ተጠቅሰው እናገኛለን፡፡ በአል - አስር ምዕራፍ ውስጥም በተመሳሳይ መልኩ “በጊዜያት እምላለሁ” ሲል ይጀምራል፡፡ የተቀሩት አንቀፆች ደግሞ የሰው ዘር መዳኛ መንገዶችን ይጠቁማሉ፡፡ በተዘዋዋሪ የጀነት መግቢያ ቁልፎች አራት መሆናቸውን አል - አስር ትናገራለች፡፡
ማመን  
ማመን ብቻ ሳይሆን በተጨማሪም መልካም ስራ መስራት
እውነታን አጥብቆ መያዝ (ለሐቅ ሟች መሆን)
ትዕግስት (ፅናት) ማሳየት (በመከራና ስቃይ ወቅት አምላክን ሳንክድ በትዕግስት መፅናት)
የተጠቀሱትን ያላሟላ ማንኛውም ሰው በኪሳራ ውስጥ መሆኑን አላህ የተናገረበት ምዕራፍ ነች - ሱራ - አል ዐስር፤
“በጊዜያት እምላለሁ
ሰው ሁሉ በእርግጥ በኪሳራ ውስጥ ነው፡፡
ከነዚያ ያመኑትና መልካምን ከሰሩት፤ በእውነትም አደራ የተባባሉት፤ በመታገስም አደራ የተባባሉት ብቻ ሲቀሩ፡፡”
ታዋቂው የእስልምና ህግ ተንታኝ ኢማም ሻፊ‘ኢ ስለዚህች ምዕራፍ እምቅነት ሲገልፁ፤ “አላህ ሌሎቹን የቁርአን ምዕራፎች ባያወርድ እንኳን ሱራ አል - ዐስር ብቻ ለሰው ልጆች መመሪያነት በቂ ነበረች፡፡” በማለት ነው፡፡
ሙሳይሊማህ አንቀፆችን መፈብረክ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ነገሮችም እስልምናን ተፈታትኗል። ነብዩ የመጨረሻ ህመማቸው በጠናባቸው ወቅት ሙሳይሊማህ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ላከላቸው፡-
ከሙሳይሊማህ - የአላህ መልዕክተኛ
ለሙሐመድ - የአላህ መልዕክተኛ
“መልካም ዜና ልንገርህ፡፡ እኔም እንዳንተ ነብይ በመሆኔ ግማሹን የአረቢያ ምድር ለኔ፣ ግማሹን ደግሞ ላንተ ይሁንና እንከፋፈል፡፡ …”
ነብዩ ሙሐመድ የሚከተለውን መልስ ላኩለት፡-
ከአላህ መልዕክተኛ - ሙሐመድ
ለውሸታሙ - ሙሳይሊማህ
“ምድር የአምላክ ነች፡፡ እርሱ ለሚፈልገው ይሰጣል፤ ሁልጊዜም አሸናፊ የሚሆኑት ደግሞ እርሱን የሚገዙ እማኞች ብቻ ናቸው፡፡ …”
ሁሉንም የነብዩ ደብዳቤ ሳናነብ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ቃላት ብቻ መሳይሊማህን የሚያንኮታኩቱ ነበሩ። “ምድር - የአምላክ - ነች፡፡”
“ምድርን እንከፋፈል” እና “ምድር የአምላክ ነች” በሚሉት ቃላቶች መካከል ሁለት ተቃራኒ አለሞችን እናያለን፡፡ ይኸውም የሙሳይሊማህ ቁሳዊነትንና የነብዩ መንፈሳዊነትን ናቸው፡፡
ነብዩ ሙሐመድ ከሞቱ በኋላ ቢሆን የሙሳይሊማህ አደገኛነት ጨምሮ ለእስልምና አገዛዝ ትልቅ ራስ ምታት ሆኖ ነበር፡፡ አል - ያማማህ በተባለ ታሪካዊ ጦርነት ላይ የቁርአን ሀፊዞችን እየመረጠ በመግደል፤ ቁርአን ለቀጣይ ትውልዶች እንዳይተላለፍ ለማድረግ ሞክሮ ነበር፡፡ ይህ የሙሳይሊማህ ክፉ ተግባር ቁርአን በጥራዝ መልክ መቀመጥ እንዳለበት የመጀመሪያውን የሙስሊሞች ከሊፋ ጠቁሞታል፡፡ ከሊፋ አቡበከር በሙሐመድ 23 የነብይነት ዓመታት ውስጥ ቁርአንን በአእምሯቸው የሸመደዱ (ሐፊዞች) ሱሐባዎች፤ በጦርነት ከማለቃቸው በፊት ቁርአንን በመጽሐፍ መልክ እንዲያዘጋጁ ትእዛዝ ሰጠ። 114ቱንም ምዕራፎች የሸመደዱት እነኝህ ሱሐባዎች ነብዩ በህይወት ሳሉ በድንጋይ፣ በቆዳ፣ በቅጠሎች ላይ የፃፏቸውን አንቀፆች አሰባስበው አሁን የምናየውን ቅዱስ ቁርአን ማዘጋጀት ቻሉ፡፡
ሙሳይሊማህ፣ ከሊፋ አቡበከር ከላከበት የሙስሊሞች ጦር ጋር ከፍተኛ ተጋድሎ ካደረገ በኋላ በመጨረሻ በካሊድ ጦር ተደመሰሰ፡፡ እሱም ተገደለ። ነገር ግን ሙሳይሊማህ፣ በአል - ያማማህ ጦርነት ላይ 450 ሐፊዞችን፣ 300 የነብዩ የልብ ጓደኞችን ገድሎ ነበር፡፡

Read 7704 times