Saturday, 27 June 2015 08:41

ንግድ ባንክ በ10 ዓመት ዓለማቀፍ ባንክ ለመሆን አልሟል

Written by  መንግስቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

    ከ10 ዓመት በኋላ ደረጃውን የጠበቀ ዓለም አቀፍ ባንክ ለመሆን ወጥኖ እየተንቀሳቀሰ ነው - በፋይናንስ ኢንዱስትሪው በአገሪቷ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፡፡ ህልሙን ለማሳካት እየፈጸማቸው ከሚገኙት ተግባራት አንዱ ባለፈው ሳምንት መገናኛ አካባቢ ያስመረቀው ባለ 17 ፎቅ የልህቀት ማዕከል (ሴንተር ኦፍ ኤክሰለንስ) ተጠቃሽ ነው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በባላንስድ ስኮር ካርድ የእቅድ አወጣጥ ስልት ባደረገው የሀብት ማሰባሰብ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትግበራና በሰው ሀብት ልማት ስትራቴጂ አማካይነት አመርቂ
ውጤቶች ማስመዝገቡን በልህቀት ማዕከሉ ህንፃ ምረቃ ወቅት ፕሬዚዳንቱ አቶ በቃሉ ዘለቀ ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ከአምስት ዓመት በፊት በ2010 ከነበረው ብር 55 ቢሊዮን ተቀማጭ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ብር 223 ቢሊዮን፣ ከ220 ቅርንጫፎች ወደ 956፣ የደንበኞችን ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን ወደ 10.1 ሚሊዮን፣ ጠቅላላ ሀብቱ ደግሞ ከ74 ቢሊዮን ወደ 297 ቢሊዮን ብር ማደጉን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ ባንኩ አሰራሩን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመለወጥ በየቅርንጫፎቹ በየቀኑ በአማካይ 700ሺህ የገንዘብ ልውውጦች እንደሚደረግ እንዲሁም በካርድ፣ በሞባይል ባንኪንግና በኢንተርኔት ባንኪንግ በየቀኑ በአማካይ ከ80ሺህ በላይ የገንዘብ ቅብብሎሽ እንደሚፈጸም አስረድተዋል፡፡ በአምስት ዓመቱ እቅድ ወቅት የባንኩ አጠቃላይ ሰራተኞች ቁጥር 8,726 ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በብዙ እጥፍ ጨምሮ 22,475 መድረሱን ጠቅሰው፣ ይሄም ባንኩ ለሰው ሀብቱ ስትራቴጂ የሰጠውን ትኩረት ያመለክታል ብለዋል፡፡ ይህን ዕቅዱን የሚያስፈጽመው ደግሞ ብቻውን አይደለም፡፡
ከጀርመኑ ፍራንክፈርት ስኩል ኦፍ ፋይናንስ ኤንድ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ነው፡፡
ካለፉት 3 ዓመታት ጀምሮ የሰው ኃይል ልማት ስትራቴጂን ከነማስፈጸሚያ ስልቱ ቀርፆ ሥራ ላይ በማዋሉ የተቀናጀ የአሰራር ስልት እንዲኖረው መደረጉ ታውቋል፡፡ በዚሁ መሰረት ባንኩ በዓለም ምርጥ (ወርልድ ክላስ) ንግድ ባንኮች የሚያከናውኑ ሰባት የስራ ዘርፎች፣ በዘመናዊ የሰው ኃይል ትራንዛክሽን፣ ኢምፕሎይመንት ኢንጌጅመንትና ኮሙኒኬሽን ካርየር ማኔጅመንትና  የኤች አር ቢዝነስ ፓርትነሪንግ ስራዎች በማዕከልም ሆነ በዲስትሪክት ጽ/ቤቶች እየተሰራበት እንደሆነ አቶ በቃሉ አመልክተዋል፡፡
አንድ ድርጅት የቱንም ያል በዘመናዊ መሳሪያዎች ቢደራጅ በራሱ አይንቀሳቀስም፡፡ የተማረ (የሰለጠነ)፣ የላቀ ችሎታና ከፍተኛ የሙያ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ይፈልጋል፡፡ በሰው ሀብት ልማት ስትራቴጂ ስልጠናው ከወትሮው የተለየ፣ ጥልቀት ያለው፣ ለለውጥና ለፈጠራ ዝግጁ የሆነ የሰው ኃይል ማፍራት የሚያስችል መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ለስልጠና ቦታዎች አመቺነትና ምቹነት ተገቢው ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡
በዕለቱ የተመረቀው የልህቀት ማዕከልም ለዚህ የሰው ኃይል ልማት ስትራቴጂ ዋነኛ አጋዥ እንዲሆን ታቅዶ የተሰራ ነው፡፡ በምድር ቤቱ ካለው ቅርንጫፍ ባንክ በስተቀር ለሥልጠናና ተያያዥነት ላላቸው የአዕምሮ ማበልጸጊያ ተግባራት እንዲያመች ተደርጎ መሰራቱን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ የተመረቀው ህንፃ 17 ፎቆች ያሉት ሲሆን ሁለቱ ፎቆች ለመኪና ማቆሚያ የተመደቡ ናቸው፡፡ 1ኛው ፎቅ ለባንኩ ሰራተኞችና ባንኩን አገልግለው ጡረታ ለወጡ ሰራተኞች የጂምናዚየም ገልግሎት ይሰጣል፡፡ የህንፃው ምድር ቤትና መዳረሻ የተቀላጠፈ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በባንክ ኢንዱስትሪ ዕድገት ታሪክ ውስጥ ባበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ትልቅ ስፍራ በያዙትና የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራ አስኪያጅ በነበሩት (በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል)  በክቡር ዶ/ር ተፈራ ደግፌ ስም የተሰየመ ነው፡፡ የህንፃው 1ኛ ፎቅ ከጂምናዚየም በተጨማሪ ለሰልጣኞች የሬስቶራንት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ 2ኛው ፎቅ ቤተ-መፃህፍት ሲሆን ከ3ኛ እስከ 12ኛ ፎቅ ያሉት ክፍሎች የስልጠና አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ “ሕዳሴ” የሚል ስም የተሰጠው ህንፃው፤ አንድ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ የስልጠና ክፍሎች አሉት፡፡   

Read 2924 times