Print this page
Saturday, 28 January 2012 13:49

የዘንድሮ ኦስካር እጩዎች ታወቁ የመጥፎዎቹ ሽልማት በ”አፕሪል ዘ ፉል” ይሆናል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

በዘንድሮ የኦስካር ሽልማት የሚወዳደሩ እጩዎች በሳምንቱ መጀመርያ ላይ ይፋ የተደረጉ ሲሆን በማርቲን ስኮርሴሲ ዳይሬክት የተደረገው “ሁጎ” በ11 እንዲሁም “ዘ አርቲስት” በ10 ዘርፎች እንደታጩ ታውቋል፡፡ ብራድ ፒት መሪ ተዋናይ የሆነበት “መኒ ቦል” እና ስቲቨን ስፒልበርግ ያዘጋጀው “ዋር ሆርስ” በስድስት፤ እንዲሁም ጆርጅ ኩልኒ የሚተውንበት “ዘ ዲሴንዳንትስ” እና “ዘ ገርል ዊዝ ዘ ድራጎን ታቱ” በአምስት የሽልማት ዘርፎች ታጭተዋል፡፡ “ሁጎ” የተሰኘው ፊልሙ በ11 ዘርፎች መታጨቱ አድናቆትን ያተረፈለት ዳይሬክተሩ ማርቲን ስኮርሴሲ በምርጥ ፊልምና ዲያሬክተር የሽልማት ዘርፎች ኦስካር ሊሸለም እንደሚችልም እየተገለፀ ነው፡፡ ሎስ አንጀለስ ታይምስ “ኦስካር ሜትር” በሚል በሰራው ትንበያ፤ የኦስካር ምርጥ ፊልም ሽልማትን ”ዘ አርቲስት”፣ የምርጥ ተዋናዮች ሽልማትን ደግሞ ጆርጅ ኩለኒ እና ሜሪል ስትሪፕ እንደሚያሸንፉ ገምቷል፡፡በጎልደን ግሎብ የዓመቱ ምርጥ ፊልም የተባለው “ዘ አርቲስት” ከሽልማቱ በኋላ ገቢው በ99 በመቶ ያደገ ሲሆን ኦስካር የመሸለሙ እድል የሰፋ እንደሆነም ይገለፃል፡፡

ሆኖም ግን ከማርቲን ስኮርሴሲ “ሁጎ” ፊልም ከባድ ትንቅንቅ ይጠብቀዋል ተብሏል፡፡ የሁለቱ ፊልሞች ትንቅንቅ በምርጥ ዲያሬክተርነት ዘርፍ በቀረበው ሽልማትም የሚቀጥል ሲሆን በአካዳሚው ብዙም የማይታወቀው ፈረንሳዊው የፊልም ዳይሬክተር ማይክ ሃዛናፊከስ ከሆሊውዱ አንጋፋ ባለሙያ ማርቲን ስኮርሴሲ ጋር ይፎካከራል፡፡ የምርጥ ፊልም ተፎካካሪዎቹ “ዘ አርቲስት”ና “ሁጎ” ቀደምት የሆሊውድ ፊልሞችን ጭብጦች መያዛቸው ቢያመሳስላቸውም በተሰሩበት በጀት ይለያያሉ፡፡ “ዘ አርቲስት” በ13.5 ሚሊዮን ዶላር ሲሰራ “ሁጐ” ደግሞ በ170 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተሰርቷል፡፡ በምርጥ ሳውንድ ትራክ ዘርፍ ለመወዳደር 39 ሙዚቃዎች ቀርበው ሁለት ብቻ በእጩነት መመረጣቸው ለብዙዎች ያልተጠበቀ ሲሆን የመጨረሻው የሃሪ ፖተር ፊልም በሁለት የኦስካር ቴክኒካል የሽልማት ዘርፎች ብቻ መታጨቱ የፊልሙን መሸለም ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል፡፡

በዘንድሮው ኦስካር በእጩነት ሳይመረጡ ከተዘለሉ ተዋናዮች ውስጥ ሊዮናርዶ ዲ ካርፒዮ ተጠቃሽ ሲሆን ምርጥ የአኒሜሽን ፊልም ተብሎ የጎልደን ግሎብን ሽልማት የወሰደው የስፒልበርግ “ዘ አድቬንቸር ኦፍ ቲን ቲን” በምርጥ ፊልም ዘርፍ ለኦስካር ሳይታጭ ቀርቷል፡፡ከፍተኛ ግምት በሚሰጠው የኦስካር የዓመቱ ምርጥ ፊልም ምርጫ ላይ ዘጠኝ ፊልሞች በእጩነት የቀረቡ ሲሆን “መኒ ቦል”፤ “ዘ ዲሴንዳንትስ”፤ “ትሪ ኦፍ ላይፍ”፤ “ሚድ ናይት ኢን ፓሪስ”፤ “ዘ ሄልፕ”፤ “ሁጎ” እና “ኤክስትሪሚሊ ላውድ ኤንድ ኢንክሬደብሊ ክሎዝ” ናቸው፡፡ በምርጥ ተዋናይ ዘርፍ ዴሜያን ቢቸር በ”ኤቤተር ላይፍ”፤ ጆርጅ ኩለኒ በ”ዘ ዲሴንዳንትስ”፤ ዢን ዱዋይርዲን በ”ዘ አርቲስት”፤ ጋሪ ኦልድማን በ”ቲንከር ቴይለር ሶልጀር ስፓይ” እና ብራድ ፒት በ”መኒ ቦል” ፊልሞቻቸው ለኦስካር ይወዳደራሉ፡፡ በምርጥ ተዋናይት ዘርፍ ደግሞ ግሌን ክሎዝ በ”አልበርት ኖብስ”፤ ቫዮላ ዴቪስ በ”ዘ ሄልፕ”፤ ሩኒ ማራ በ”ዘ ገርል ዊዝ ዘ ድራጎን ታቱ”፤ ሜሪል ስትሪፕ በ”ዘ አይረን ሌዲ” እና ሚሸል ዊልያምስ በ”ማይ ዊክ ዊዝ ማርሊን” ታጭተዋል፡፡በተያያዘ በኦስካር ምሽት ዋዜማ ይደረጋል ተብሎ የታሰበው የመጥፎ ፊልሞችና ባለሙያዎች ሽልማት “ራዚ አዋርድስ” ፕሮግራም ተለውጦ “አፕሪል ፉል” በሚከበርበት ቀን እንደሚከናወን ተገለፀ፡፡

በኦስካር የሽልማት ስነስርዓት ምሽት ዋዜማ ላይ የራዚ አዋርድስ እጩዎች  ይታወቃሉ ተብሏል፡፡ በጎልድ ራስፕቤሪ የሚዘጋጀውና 600 አባላቱ በሚሰጡት ድምፅ የዓመቱን መጥፎ ፊልሞችና ባለሙያዎች መርጦ የሚሸልመው ራዚ አዋርድስ ዘንድሮ ለ23ኛ ጊዜ ይካሄዳል፡፡

 

 

Read 1597 times Last modified on Saturday, 28 January 2012 13:52