ሆኖም ግን ከማርቲን ስኮርሴሲ “ሁጎ” ፊልም ከባድ ትንቅንቅ ይጠብቀዋል ተብሏል፡፡ የሁለቱ ፊልሞች ትንቅንቅ በምርጥ ዲያሬክተርነት ዘርፍ በቀረበው ሽልማትም የሚቀጥል ሲሆን በአካዳሚው ብዙም የማይታወቀው ፈረንሳዊው የፊልም ዳይሬክተር ማይክ ሃዛናፊከስ ከሆሊውዱ አንጋፋ ባለሙያ ማርቲን ስኮርሴሲ ጋር ይፎካከራል፡፡ የምርጥ ፊልም ተፎካካሪዎቹ “ዘ አርቲስት”ና “ሁጎ” ቀደምት የሆሊውድ ፊልሞችን ጭብጦች መያዛቸው ቢያመሳስላቸውም በተሰሩበት በጀት ይለያያሉ፡፡ “ዘ አርቲስት” በ13.5 ሚሊዮን ዶላር ሲሰራ “ሁጐ” ደግሞ በ170 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተሰርቷል፡፡ በምርጥ ሳውንድ ትራክ ዘርፍ ለመወዳደር 39 ሙዚቃዎች ቀርበው ሁለት ብቻ በእጩነት መመረጣቸው ለብዙዎች ያልተጠበቀ ሲሆን የመጨረሻው የሃሪ ፖተር ፊልም በሁለት የኦስካር ቴክኒካል የሽልማት ዘርፎች ብቻ መታጨቱ የፊልሙን መሸለም ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል፡፡
በዘንድሮው ኦስካር በእጩነት ሳይመረጡ ከተዘለሉ ተዋናዮች ውስጥ ሊዮናርዶ ዲ ካርፒዮ ተጠቃሽ ሲሆን ምርጥ የአኒሜሽን ፊልም ተብሎ የጎልደን ግሎብን ሽልማት የወሰደው የስፒልበርግ “ዘ አድቬንቸር ኦፍ ቲን ቲን” በምርጥ ፊልም ዘርፍ ለኦስካር ሳይታጭ ቀርቷል፡፡ከፍተኛ ግምት በሚሰጠው የኦስካር የዓመቱ ምርጥ ፊልም ምርጫ ላይ ዘጠኝ ፊልሞች በእጩነት የቀረቡ ሲሆን “መኒ ቦል”፤ “ዘ ዲሴንዳንትስ”፤ “ትሪ ኦፍ ላይፍ”፤ “ሚድ ናይት ኢን ፓሪስ”፤ “ዘ ሄልፕ”፤ “ሁጎ” እና “ኤክስትሪሚሊ ላውድ ኤንድ ኢንክሬደብሊ ክሎዝ” ናቸው፡፡ በምርጥ ተዋናይ ዘርፍ ዴሜያን ቢቸር በ”ኤቤተር ላይፍ”፤ ጆርጅ ኩለኒ በ”ዘ ዲሴንዳንትስ”፤ ዢን ዱዋይርዲን በ”ዘ አርቲስት”፤ ጋሪ ኦልድማን በ”ቲንከር ቴይለር ሶልጀር ስፓይ” እና ብራድ ፒት በ”መኒ ቦል” ፊልሞቻቸው ለኦስካር ይወዳደራሉ፡፡ በምርጥ ተዋናይት ዘርፍ ደግሞ ግሌን ክሎዝ በ”አልበርት ኖብስ”፤ ቫዮላ ዴቪስ በ”ዘ ሄልፕ”፤ ሩኒ ማራ በ”ዘ ገርል ዊዝ ዘ ድራጎን ታቱ”፤ ሜሪል ስትሪፕ በ”ዘ አይረን ሌዲ” እና ሚሸል ዊልያምስ በ”ማይ ዊክ ዊዝ ማርሊን” ታጭተዋል፡፡በተያያዘ በኦስካር ምሽት ዋዜማ ይደረጋል ተብሎ የታሰበው የመጥፎ ፊልሞችና ባለሙያዎች ሽልማት “ራዚ አዋርድስ” ፕሮግራም ተለውጦ “አፕሪል ፉል” በሚከበርበት ቀን እንደሚከናወን ተገለፀ፡፡
በኦስካር የሽልማት ስነስርዓት ምሽት ዋዜማ ላይ የራዚ አዋርድስ እጩዎች ይታወቃሉ ተብሏል፡፡ በጎልድ ራስፕቤሪ የሚዘጋጀውና 600 አባላቱ በሚሰጡት ድምፅ የዓመቱን መጥፎ ፊልሞችና ባለሙያዎች መርጦ የሚሸልመው ራዚ አዋርድስ ዘንድሮ ለ23ኛ ጊዜ ይካሄዳል፡፡