Saturday, 27 June 2015 08:24

መንግሥት በአገሪቱ የ5 ዓመት እቅድ ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አወያያለሁ አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

ህብረተሰቡ ለ10 ቀናት በእቅዱ ላይ ይወያያል ተብሏል

    መንግሥት የመጀመሪያውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መቶ በመቶ አለማሳካቱን ገልፆ ለ5 ዓመት በሚዘልቀው በሁለተኛው የእቅድ ዘመኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አንደሚወያይና ተጨማሪ እቅዶችንም በማከል ዕቅዱን እንደሚያሳካ አስታውቋል፡፡ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን ትናንት በፅ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 10 ቀናት በየክልሉና በፌደራል ደረጃ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ ከህብረተሰቡ ጋር ጠንካራ ውይይት ይደረጋል ብለዋል፡፡ “በእቅዱ ላይ መንግስት በፌደራል ደረጃ ሁሉንም የሃገሪቱን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅድሚያ ሰጥቶ ያወያያል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ በያንዳንዱ መድረክ እስከ 600 የሚደርሱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀጣይ 5 ዓመት በሚተገበረው የመንግስት የልማት እቅድ ላይ ይመክራሉ ብለዋል፡፡ የደቡብ፣ የኦሮሚያ፣ የአማራና ጋምቤላ ክልል መንግስታት በጉዳዩ ላይ ዛሬና ነገ ከህብረተሰቡ ጋር የሚወያዩ ሲሆን የአዲስ አበባ ሰኞ እና ማክሰኞ ይሆናል ተብሏል፡፡ በፌደራል ደረጃ በሚካሄደው ውይይት የሲቪክ ማህበራት፣ የግል ባለሀብቶች እና የተለያዩ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ይሳተፋሉ፤ ለእቅዱም ግብአት ያመነጫሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አውስተዋል፡፡
ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን የኢኮኖሚ ሽግግር ማቀላጠፍ ዋነኛው የሁለተኛው ዘመን እቅድ የመንግስት ግብ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዓመታዊ ሀገራዊ እድገት (GDP) ላይ ግብርናው አሁን ያለው 40 በመቶ ድርሻ ወደ 36 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጎ፣ ኢንዱስትሪው አሁን ካለበት 14 በመቶ ወደ ላይ ከፍ እንዲል ይደረጋል ብለዋል። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አሁን ካለው 5 በመቶ ድርሻ ወደ 8 በመቶ ማሳደግም ዋነኛው እቅድ ነው ተብሏል፡፡ በሃይል ልማቱም የህዳሴ ግድብ ግንባታን ማቀላጠፍ ጨምሮ የተለያዩ የኃይል ምንጮችን በመገንባት ወደ 17 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በሁለተኛው የእቅድ ዘመን ማጠናቀቂያ አመርታለሁ ብሏል - መንግስት፡፡ ባለፉት 5 ዓመታት ሲተገበር የነበረው የመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በአጠቃላይ ተለጥጦ የተዘጋጀ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መንግስት ሙሉ ለሙሉ ማሳካት አለመቻሉን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በተለይ በስኳር ልማት፣ ባቡር መስመር ግንባታና የወረዳ - ቀበሌ መንገድ ግንባታዎች ከእቅዱ በታች የሆነ አፈፃፀም ተመዝግቦባቸዋል ብለዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክትና ከጅቡቲው የባቡር መስመር በተጨማሪ ሌሎች እንዳይተገበሩ ዋነኛው እንቅፋት የገንዘብ እጥረት መሆኑ ተጠቁሟል። እያንዳንዱን የገጠር ቀበሌ ከወረዳ የሚያገናኙ 71ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ ለመስራት ታቅዶ 40 ሺህ ያህሉ መሰራቱን ያወሱት ሚኒስትሩ፤ ለእቅዱ ሙሉ ለሙሉ አለመሳካት የሎጀስቲክና የሰለጠነ
ሰው ኃይል እጥረት ምክንያት ነው ብለዋል፡፡ “ግብርናውም 8 በመቶ እንደሚያድግ ታስቦ የነበረ ሲሆን በአማካይ 6.6 በመቶ አድጓል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ አፈፃፀሙ መልካም ነው ብለዋል፡፡ በአጠቃላይም በመጀመሪያው የእቅድ ዘመን ያልተሳኩት የሁለተኛው የእቅድ ዘመን አካል ሆነው ይጠናቀቃሉ ብለዋል፡፡ ለቀጣይ እቅዱ ማስፈፀሚያ የሃገር ውስጥ ቁጠባን ከማሳደግ የሚገኝ ገቢ አንዱ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በመጀመሪያው  የእቅድ ዘመን ወደ ምርት ገብተው ለሁለተኛው እቅድ ገቢ ያመነጫሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት ሁሉም የስኳር ፕሮጀክቶች ምርት ባለመጀመራቸው ሃገሪቱ አገኛለሁ ብላ አስባ የነበረውን በዓመት 600 ሚሊዮን ዶላር (12 ቢሊዮን ገደማ) ማጣቷን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ ፕሮጀክቱን አጠናቆ የተጠቀሰውን ያህል ገቢ ማመንጨትም የሁለተኛው እቅድ አካል ይሆናል ተብሏል፡፡

Read 2787 times