Saturday, 20 June 2015 12:31

የWATCH ፕሮጀክት ተጠናቀቀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

  በእናቶችና ህፃናት ጤና እንክብካቤ ላይ አተኩሮ ላለፉት 42 ወራት በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ሲንቀሳቀስ የነበረውና WATCH (Women and their Children Health) የተባለው ፕሮጀክት ተጠናቀቀ፡፡
በካናዳ መንግስት ድጋፍ በፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያና በኢትዮጵያ የፅንስና ማህፀን ሐኪሞች ማህበር የጋራ ትብብር ሲተገበር የቆየውን የዚህኑ ፕሮጀክት መጠናቀቅ አስመልክቶ በጁፒተር ሆቴል በተዘጋጀ ፕሮግራም ላይ የፕላን ኢንተርናሽናል ሲኒየር ማኔጀር የፕሮጀክቱ ኃላፊ ወ/ሮ አይናለም አሸብር እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቱ በሶስቱ የአገሪቱ ክልሎች ማለትም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በሲዳማ ዞን ሸበዲኖ፣ ጐርቼና ቦና ዙሪያ፣ በኦሮሚያ ክልል በጅማ ዞን ቀርሳ ወረዳና ጢሮ አፍታ ወረዳዎች እንዲሁም በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በመቂት፣ ላስታና ቡግና ወረዳዎች ላይ ላለፉት 3 ዓመታት ከስድስት ወራት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ፕሮጀክቱ በእናቶችና ልጆቻቸው ጤና እንክብካቤ በተለይም እርጉዝ እናቶች በእርግዝና፣ በወሊድና ከወሊድ በኋላ የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመቅረፍ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የሚሰራ ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ፍላጐትና አቅርቦትን ባጣጣመ መልኩ የእናቶችና ልጆቻቸውን ጤና በመንከባከብ ተግባር ላይ አተኩሮ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን የተናገሩት ወ/ሮ አይናለም፤ የፕሮጀክቱ መጠናቀቂያ ጊዜ በመድረሱ ምክንያት ከወረዳዎቹ መውጣቱን ጠቁመው ወደፊት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ሌሎች ፕሮጀክቶች እንደሚኖሩም ገልፀዋል፡፡

Read 3252 times