Saturday, 20 June 2015 12:25

የኢጣሊያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቬስት ማድረግ ይፈልጋሉ ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ላይ ነው የከተመችው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሳምንት በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው 3ኛው ሆቴል ሾው ኢትዮጵያ 2007 ከተሳተፉት 145 ኩባንያዎች የኢጣሊያዊው የቢዝነስ ፕሮሞሽንና ኤክስፖርት ኖቫ ኮንሰልቲንግ አንዱ ነበር፡፡ የኖቫ ኮንሰልቲንግ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚ/ር ፋብዮ ሳንቶኒ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደሉም - ከ15 ዓመት በፊት ነው የሚያውቋት፡፡ ለአቃቂ ጨርቃ ጨርቅ፣ ለጅማ፣ ለባህርዳር፣ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎችና ለአንዳንድ የግል ድርጅቶች መሳሪያዎች ያቀርቡ ስለነበር ኢትዮጵያን በደንብ እንደሚያውቋት ይናገራሉ፡፡
ሚ/ር ሳንቶኒ፣ በአሁኑ ወቅት ሥራቸው የኢጣሊያ ኢንቨስተሮች በአፍሪካ በካሜሩንና በኢትዮጵያ ኢንቬስት እንዲያደርጉ ማግባባት እንደሆነ በሚሊኒየም አዳራሽ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ውይይት ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በጣም ተለውጣለች ያሉት ሚ/ር ሳንቶኒ፤ “ኢትዮጵያ ከየትኛውም የአፍሪካ አገር ለኢንቬስትመንት በጣም ምቹና ተስማሚ ከመሆኗም በላይ በጥሩ እድገት ላይ ትገኛለች፡፡ የኢጣሊያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቬስት ለማድረግ ፈልገዋል፡፡ እኛ መሥራት የምንፈልገው ከመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር ነው፡፡ ኢንተርፕራይዞቹ የእኛን ቴክኖሎጂ፣ ገንዘብ፣ እውቀት፣ ገበያ፣ ይጠቀማሉ፡፡ የእኛ ባለሀብቶች የአገሪቷን ገበያ ይጠቀማሉ፡፡ ሁለቱ አገሮች በጋራ የ50፣50 ተጠቃሚነት ዕድገታቸው ተቀራራቢ ይሆናል፡፡ የሕዝቦችም ታሪካዊ ግንኙነት ይጠናከራል” ብለዋል፡፡
ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ ኢንቬስት እንዲያደርጉ ይዘው የመጡት 72 የኢጣሊያ ኩባንያዎች ሲሆኑ የኩባንያዎቹ ፍላጐት ሆቴል ወይም በሌላ ኢንዱስትሪ ግንባታ ሳይሆን ኢትዮጵያውያኑን በእውቀትና ልምዳቸው በሆቴል፣ በሪዞርት፣ በመሳሪያ አቅርቦት፣ ዲዛይንና አርክቴክቸር፣ የአዋጭነት ጥናት፣ በሆቴል ማኔጅመንት (አመራር) ሆቴልና ሪዞርቶች ዓለምአቀፍ ደረጃ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ ሌሎች ደግሞ በመስኮትና በር፣ በጣሪያ ክዳንና በሶፋ አቅርቦት መሳተፍ ሲፈልጉ አንዳንዶች ደግሞ በስብሰባና ሲኒማ ቤት አዳራሾች ግንባታ የማማከር እውቀት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
አሁን በአገሪቷ የሚታየው ዕድገት ጥሩ ቢሆንም የበለጠ የሀብቷ ተጠቃሚ ሆና ዕድገቷ እንዳይፋጠን የሚያደርጉ ፈታኝ ችግር ቀፍድዶ እንደያዛት አልደበቁም፡፡ በእኔ አስተያየት ይላሉ ሚ/ር ሳንቶኒ፤ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች ከፍተኛ እምቅ ሀብት አላት፡፡ እንዲያውም ከደቡብ አፍሪካ የበለጠ የቱሪዝም ሀብት እንዳላት አምናለሁ፡፡ ችግሩ፣ ግን ብዙ ኢትዮጵያውያን እኔ የበለጠ አዲስ ነገር መፍጠር እፈልጋለሁ ብሎ ሲተጋ አይታይም፡፡ የአገልግሎት አሰጣጤን፣ የሆቴልን፣ የምርቴን፣ የጥራት ደረጃ ወደላቀ ደረጃ አደርሳለሁ አይሉም ብለዋል፡፡
ሌላው ከፍተኛ ችግር የአገሪቷ ዕድገት በአዲስ አበባ ብቻ መሆኑ ወይም ኢትዮጵያ አዲስ አበባ ላይ መከተሟ ነው፡፡ በአገሪቷ የተመጣጣነ የዕድገት ደረጃ የለም፡፡ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ችግር አለው። አክሱም፣ ላሊበላ ወይም ጐንደር ስንሄድ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ሆቴል ማግኘት በጣም ከባድ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ አገሪቷ ከቱሪዝም የምታገኘውን ገቢ በእጅጉ እየተፈታተነ ነው፡፡ ከአንዳንድ የታሪክ ሰዎች ጋር ስንወያይ “ታሪክ ሲባል በተጀመረበት ሁኔታ መቆም (መቆየት) አለበት” ይላሉ፡፡ ነገር ግን እውነታው እንደዚያ አይደለም፡፡ ዓለም በእያንዳንዱ ደቂቃ በለውጥ ጐዳና እየተንደረደረች፣ እየሮጠች፣ እየተለወጠች፣ እያደገችና እየተመነደገች ነው፡፡ ኢትዮጵያም እርምጃዋን ከዓለም ጋር ማስተካከልና መለወጥ አለባት፡፡
ለለውጥና ዕድገት ያለመፍጠን በቱሪዝም ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የሚታይ ነው፡፡ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች የሉም ማለት ይቻላል። ጥቂት ቢኖሩም ከቁጥር የሚገቡ አይደሉም፡፡ አንድ ምሳሌ ልጠቀስ፡፡ አገሪቷ ማንጐ አብቃይ ሆና ጥሬ ዕቃው በእጃቸው እያለ በአግሮ ኢንዱስትሪ ማቀነባበር ሥራ የተሰማሩ ድርጅቶች የሉም ማለት ይቻላል፡፡ ለእኔ ይኼ ሞኝነት ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ለሥራ ያላቸው ግንዛቤ መለወጥ አለበት፡፡ ሥራ ማለት ወደ ቢዝነስ መግባትና ያፈሩትን ምርት ወይም ያዘጋጁትን አገልግሎት የሚገዛ ደንበኛ ማፍራት ነው፡፡
በቢዝነስ ዓለም ዋናው አስፈላጊ ነገር ቢዝነስ ፕላን ነው፡፡ የቢዝነስ ሰው የፈጠራ ሰው (ኢንተርፕሪነር) መሆን አለበት፡፡ አንድ ሰው ገንዘብ ስላለው ብቻ ዝም ብሎ ቢዝነስ መጀመር የለበትም፡፡ ፈጠራ ሲባል አዲስ ነገር መፈልሰፍ ብቻ አይደለም። ቢዝነስ ከመጀመር በፊት ያለኝ ገንዘብ ምን ሊያሠራኝ ይችላል? እዚህ አካባቢ ምን ብጀምር ነው የሚያዋጣኝ? ሕዝቡ በጣም የሚፈልገው ነገር ምንድነው? የመግዛት አቅሙስ? ጥሬ ዕቃውስ እንዴት ነው በቀላል ማግኘት የሚቻለው?... ብሎ ማጥናት የሚችልበት እውቀት ሊኖረው ይገባል፡፡
ስለዚህ አዲስ ኢንተርፕሪነሮች በጥናት ላይ የተመሠረተ እውነተኛ ቢዝነስ ፕላን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ያለ ጥናት ዝም ብሎ የሚጀመር ቢዝነስ ብዙ ጊዜ ውጤቱ መጥፎ ሊሆን ይችላል - ትርፍ ጠብቆ ኪሳራ ማፈስ እንዳይሆን፡፡
አንድ ዋነኛ ነጥብ ደግሞ ቢዝነስ የግድ ከትልቅ ወይም ከፍ ካለ ደረጃ መጀመር የለበትም ይላሉ ሚ/ር ሳንቶኒ፡፡ የብዙ ኢትዮጵያውያን አስተሳሰብ ሼክ ሙሐሙድ አሊ አላሙዲንን መሆንና እሳቸው እንደሠሩት ትልቅ ነገር ሥራት ነው፡፡ እንደዚያ መሆን የለበትም፡፡ በትንሽ ቢዝነስ ጀምረው የራሳቸውን ገበያና ደንበኛ በማፍራት በሂደት ደረጃ በደረጃ፣ የሥራ አመራር ክህሎት በማዳበር፣ የምርትና አገልግሎትን ጥራት በማሳደግ ማደግና ካሰቡት ደረጃ መድረስ ይቻላል፡፡ በአገሬ ቢዝነስ የሚሠራው እንደዚህ ነው፡፡ አባት ትንሽ ቢዝነስ ይጀምራል፡፡ ሲደክመው ልጅ ይረከባል፣ ከዚያም ትልቅ የቤተሰብ ቢዝነስ ይሆናል በማለት ገልፀዋል፡፡
የስኬት ሁነኛው ቁልፍ ጥራት ቢሆንም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ለጥራት ቦታ (ግምት) እንደማይሰጥ ይናገራሉ፡፡ ጥራት ሲባል ብዙ መለኪያዎች አሉት ያሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ እኔ ወደ አንድ ሆቴል ስገባ ደንበኛ ወይም ተገልጋይ ነኝ፡፡ ደንበኛ ደግሞ ንጉሥ ስለሆነ ከሆቴሉ አስተናጋጆች የንጉሥ መስተንግዶ እጠብቃለሁ፡፡ ይህን መስተንግዶ ማግኘት ያለብኝ መኝታ ክፍል ስጠይቅ ብቻ አይደለም፡፡  በሁሉም የሆቴሉ አገልግሎት መስጫዎች፣ ባር፣ ሬስቶራንት፣ የመኝታ ክፍል…ሁሉ የተሟላ አገልግሎት ማግኘት አለብኝ። ክፍሌ ውስጥ የሚያስፈልጉኝ ነገሮች ሁሉ ውሃ፣ መብራት፣ ስልክ፣ ፍሪጅ፣ ቲቪ፣ ንፁህ አንሶላና ፎጣ፣ ንፁህና ጣፋጭ ምግብ፣ ማግኘት የሆቴሉን ጥራት ያመለክታል፡፡
አስተናጋጆችም ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ ያለው መስተንግዶ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥሩ ሥልጠና ሊሰጣቸው ይገባል። ወደ ሆቴሉ የሚመጡት የተለያየ አገር ዜግነት ያላቸው እንግዶች ናቸው፡፡
የአሜሪካ የጣሊያን፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣… ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የየአገሩ እንግዳ ወይም ቱሪስት የሚፈለገው ዓይነት አገልግሎትና አቀባበል የተለያየ ነው፤ ስለዚህ አንድ እንግዳ ሲመጣ የየት አገር ዜጋ እንደሆነ ለይቶ የሚፈልገውን ዓይነት አገልግሎት መስጠት ነው ጥራት ማለት፤ ለጀርመኑ ቱሪስት የሚደረገው አቀባበልና የምግብ ዝግጅት ለአሜሪካዊው አይመቸውም፡፡
ለኢጣሊያው የሚዘጋጀው ምግብና የሚደረግለት መስተንግዶ ለፈረንሳዩ፣ ለአረቡ፣ ለጃፓኑ፣ ለቻይናው፣ አይስማማም፡፡ ፈረንጅ ሁሉ አንድ ነው በማለት አንድ ዓይነት ምግብ አዘጋጅቶ ማቅረብ ትክክል አይደለም፡፡
በአገሩ የለመደውና የሚወደው የምግብ አይነት ነው መዘጋጀት ያለበት በማለት የጥራትን ፅንሰ - ሐሳብ አስረድተዋል፡፡

Read 1961 times