Saturday, 20 June 2015 12:22

የፕሪንቲግና የሌብሊንግ ፋብሪካዎች ተመረቁ ግንባታቸው በ5 ወር ነው የተጠናቀቀው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአገር ውስጥ ባለሀብት በአቶ አዲስ ገሠሠና በሆላንዳዊው ባለሀብት በሚ/ር ሚሪያም ቫን አልፈን በአክሲዮን በዱከም ከተማ ኢንዱስትሪ ዞን በ2.5 ሚሊዮን ዶላር ያቋቋሙት ቢ ኮኔክትድ ፕሪንቲንግና ቢ ኮኔክትድ ሌብሊንግ የተባሉ ፋብሪካዎች ሰሞኑን ተመረቁ፡፡
ፋብሪካዎቹን የመረቁት የኢንዱስትሪ ሚ/ር ዴኤታ ዶ/ር መብራህቱ መለስ፣ ፋብሪካዎቹ በኢትዮጵያ በዓይነታቸው የመጀመሪያ እንደሆኑ ጠቅሰው ሁሉም የአገር ውስጥ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች በምርት ሰንሰለት ሂደት የጎደላቸውን ፕሪንትና ሌብል በማድረግ እሴት ጨምረው ኤክስፖርት የሚያደርጉትን መጠን እንዲጨምሩ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡
ፕሪንቲንግ ማለት በነጭ ቲ -ሸርት ላይ የተለያየ ምስልና ጽሑፍ በማተም ወደ ውጭ መላክ ሲሆን ሌብሊንግ ደግሞ ከውጭ በሚገቡ ሸሚዞች አንገት ላይ ተሰፍቶ የምናገኘውን የሸሚዙን ቁጥር፣ የተሰራበትን አገር፣ ስሙና (ሞዱን) እንዲሁም በሸሚዙ የጎን ስፌት ላይ የሚገኘውን ሸሚዙ ከምንና ምን ድብልቅ እንደተሰራ፣ እንዴት መታጠብ፣ መድረቅ መተኮስ፣ … እንዳለበት የሚገልፀው የፀሐይ፣ የዳመና፣ የካውያ … ምልክቶች ያሉበት ጨርቅ ማለት ነው፡፡
ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ አገር የሚልኩ ሁሉም ፋብሪካዎች ሌብሉን ከውጭ አገር በውጭ ምንዛሪ እንደሚገዙ የጠቀሱት የቢ ኮኔክትድ ኢንዱስትሪየል ጀኔራል ማናጀር ሚ/ር ቫን አልፈን፣ የፋብሪካቸው አጠቃላይ የኤክስፖርት መጠን እንደሚጨምር እናምናለን ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመላው ዓለም ከሚሸጡ ቲ-ሸርቶች ውስጥ ከመቶ 70 ህትመት ያለባቸው ሲሆኑ በነጭነታቸው የሚሸጡት ከመቶ 30 መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
እጅግ ዘመናዊ የሆነው የህትመት ፋብሪካችን 800 ሜትር ርዝመት ባለው ስክሪን ጠረጴዛና ከፍተኛ ደረጃ ባለው እንግሊዝ ሰራሹ ሞላላ መሳሪያ በቀን 80, 000 ያትማል ያሉት ጀነራል ማናጀሩ፣ የሌብሊንግ መሳሪያቸው ደግሞ በዓለም ታዋቂ በሆነው ስዊዘርላንድ ሰራሹ ሙለር መሳሪያ የተለያዩ የሽመና ሌብሎች እንደሚያመርቱ ተናግረዋል፡፡
የፋብሪካዎቹ ዋና ዓላማ ከትርፍ ባሻገር የእውቀት ሽግግር ነው ያሉት አቶ አዲስ፣ በተለያዩ የኢንጂነሪንግ ዘርፎች በኤሌክትሪካል፣ በኬሚካል፣ በማሽነሪ፣ … ዘጠኝ ኢንጂነረች ወደ ቤልጂየም፣ ስዊዘርላንድና ቻይና ልከው ስለመሳሪያዎቹ አጠቃቀምና ጥገና በሚገባ ሰልጥነው ወደ አገራቸው ተመልሰው እየሰሩ ስለሆነ በቀሰሙት እውቀት ሌሎች 400 የፋብሪካው ሰራተኞች እንደሚያሰለጥኑ ገልፀዋል፡፡
አቶ አዲስ፣ ሸሪካቸው ሚ/ር ቫን አልፈን የሚያንቀሳቅሱት የቤተሰብ ኩባንያ እንደሆነ ጠቅሰው በተለያዩ የኤስያ አገራት ሰባት ፋብሪካዎች እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ይህኛው በአፍሪካ የመጀመሪያው ሲሆን ባለሀብቶቹ ኢትዮጵያን ስለወደዱ ከባንክ ሳይበደሩ በራሳቸው ገንዘብ በ5 ወራት የፋብሪካዎቹን ግንባታ አጠናቀው ማስመረቃቸውን አስረድተዋል፡፡
ሚ/ር ቫን አልፈን በተለያዩ ኩባንያዎች ከ50 በላይ ፈቃድ ስላላቸው ቢ ኮኔክትድ ኢንዱስትሪያል እቅዱ መቶ ፐርሰንት ኤክስፖርት ቢሆንም የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች በቀጥታም ባይሆን የምርቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡

Read 1860 times