Saturday, 20 June 2015 11:38

ገጣሚው “የግጥም ባለውለታ” ያላቸውን አመሠገነ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   ባለፈው ረቡዕ “ያልታየው ተውኔት” የተሰኘ የግጥም ሲዲውን በሒልተን ሆቴል ያስመረቀው ገጣሚ ደምሰው  መርሻ፤ የግጥም ባለውለታ ያላቸውን ሁለት ተቋማትና አራት ግለሰቦች የክብር ዋንጫ በመሸለም ምስጋናውን አቀረበ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነጽሁፍ መምህሩ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘና ገጣሚና ጸሃፌ-ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ምስጋናው ከቀረበላቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የግጥም ሲዲውን መርቀው የከፈቱት የቀድሞ ኢምፔሪያል ሆቴል ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጸጋዬ፤ ለግጥምና ሥነጽሁፍ ፕሮግራሞች ለረዥም ጊዜያት አዳራሽ በነጻ በመፍቀድ ላደረጉት በጎ አስተዋጽኦ የምስጋና ዋንጫ የተበረከተላቸው ሲሆን ሸበሌ ሆቴል ግጥም በጃዝ ሲጀመር አዳራሹን ለመስጠት ሳይሳሳ ለጥበብ ላሳየው ቸርነት፣ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ደግሞ ለግጥም ዕድገት በተለያዩ መንገዶች ለተጫወተው ሚና  የምስጋና ዋንጫ ተሸልመዋል፡፡
ገጣሚና ጸሃፌ-ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፤ ለወጣት ገጣሚያን የፑሽኪን አዳራሽን በመፍቀድ ተሰጥኦዋቸውን የሚያወጡበት ዕድል በመስጠታቸው፣ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ እንዲሁ ለጀማሪ ገጣሚያን መንገድና አቅጣጫ በማመላከት ላበረከቱት ጉልህ ድርሻ የምስጋና ዋንጫው የተበረከተላቸው ሲሆን እስክንድር ሃይሉም ለገጣሚያን የመድረክ ንባብ ክፍያ ባልተለመደበት ጊዜ ገንዘብ በመክፈል ለጥበቡ ክብር ሰጥቷል በሚል ከገጣሚው የምስጋና ሽልማቱን አግኝቷል፡፡
ገጣሚ ደምሰው መርሻ ምስጋናውን ለማቅረብ ምን እንዳነሳሳው ለአዲስ አድማስ ሲገልጽ፤ “ለእኔ የግጥም ህይወት እዚህ መድረስ የየራሳቸውን ድርሻ አበርክተዋል የምላቸውንና ለግጥሙም ክብርና ማዕረግ መቀዳጀት ተግተዋል ብዬ ያሰብኳቸውን ለማመስገን በማሰብና ዕውቅና ሊሰጣቸው ይገባል በሚል ግላዊ እምነቴ ነው” ብሏል፡፡ ምስጋናውና ዕውቅናው ከተበረከተላቸው ግለሰቦች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት፤ በገጣሚው አርአያነት ያለው ተግባር መደመማቸውን ገልጸው ምስጋና እና ዕውቅና ለሚገባው ሁሉ መስጠት ሊዳብር የሚገባው ባህል ነው ብለዋል፡፡  

Read 2033 times