Saturday, 20 June 2015 11:33

ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና አዳዲስ ክዋክብት ትጠብቃለች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ገንዘቤ ዲባባ
በ1500፤ በ3ሺ እና በ5ሺ ሜትር የዓለም የቤት ውስጥ ውድድሮች ሶስት ሪከርዶች ይዛለች፡፡
በ5ሺ ሜትር በኦልአትሌቲክስ የውጤት ደረጃ በ1365 ነጥብ አንደኛ ናት፡፡
2015 ከገባ በአሜሪካ የ5ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ፤ በ5ሺ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድር ስቶክሆልም ላይ እንዲሁም በ5ሺ ሜትር በዩጂን የዳይመንድ ሊግ ውድድር አሸንፋለች፡፡

                   ዮሚፍ ቀጀልቻ
17 ዓመቱ  ነው፡፡
በ5ሺ ሜትር 12.58 39 ፈጣን የግሉን ሰዓት አስመዝግቧል፡፡
በ2013 በዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና በ3ሺ ወርቅ፤ በ2014 በቻይና የኒንግ በተካሄደው የወጣቶች ኦሎምፒክ በ3ሺ ወርቅ እንዲሁም በ2015 በአፍሪካ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በአዲስ አበባ በ5ሺ የወርቅ ሜዳልያ አግኝቷል፡፡ በ1317 ነጥብ 2ኛ ነው፡
በ2015 በ3ሺ ሜትር በኳታር ዶሃ እንዲሁም በ5ሺ በጣልያን ሮም ሁለት የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች አሸንፏል፡፡

                    ሙክታር ኢድሪስ
በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በወጣቶች ውድድር የቡድን የብር ሜዳልያ በ2011 እኤአ ላ ካገኘ በኋላ በተመሳሳይ ዓመት በአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር አራተኛ ደረጃ ነበረው፡፡ በ2012 እኤአ ላይ ደግሞ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በወጣቶች ውድድር የወርቅ ሜዳልያ ያገኘ ሲሆን በዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያም ተጎናፅፏል፡፡
በኦልአትሌቲክስ የአትሌቶች የውጤት ደረጃ በ5ሺ ሜትር 1315 ነጥብ በማስመዝገብ 3ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡

                     ገለቴ ቡርቃ
በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1500 ሜትር በ2008 እኤአ ላይ በሻሌንሽያ የወርቅአንዲሁም በ2010 በኳታር ዶሃ የነሐስ ሜዳልያ ያገኘች ሲሆን በ2012 እኤአ ላይ ኢስታንቡል ላይ በ3ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ ተጎናፅፋለች፡፡ ለሁለት ጊዜያት በዓለም አትሌቲክስ ውድድሮች ፍፃሜ የብር ሜዳልያ፤ በኦል አፍሪካን ጌምስ እና በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች በ1500 አግኝታለች፡፡
በኦልአትሌቲክስ የውድድር ውጤት ደረጃ በ10ሺ ሜትር በ1210 ነጥብ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡

                       አልማዝ አያና
ከሁለት አመት  በፊት  በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ የነሐስ ሜዳልያ፤ በ2014 ደግሞ በማራኬሽ በርቀቱ የአፍሪካ ሻምፒዮን በመሆን የወርቅ ሜዳልያ ተጎናፅፋለች፡፡
በ5ሺ ሜትር በኦልአትሌቲክስ የውጤት ደረጃ በ1323  ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ አላት
በ2015 በሻንጋይ ዳይመንድ ሊግ ስታሸንፍ፤ ከሳምንት በፊት በሞሮኮ በ3ሺ ሜትርም አንደኛ ሆናለች፡፡


      ከ2 ወራት በኋላ በቻይናዋ ቤጂንግ ከተማ በሚካሄደው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ  አዳዲስ ክዋክብት ልትጠብቅ ነው፡፡ ከ7 ዓመታት በፊት ኦሎምፒክን ባስተናግደውና እስከ 54ሺ ተመልካች  በሚይዘው የቤጂንጉ ምርጥ ስታድዬም bird nest  የወፍ ጎጆ በሚካሄደው ሻምፒዮና፤ ከ203 የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር አባል አገራት በመወከል 2567 አትሌቶች እንደሚገኙበት መገለፁ በውድድሩ ታሪክ በሪከርድነት የሚመዘገብ የተሳትፎ ብዛት ይሆናል፡፡   
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ከፍተኛ ውጤት ያላቸው ትልልቅ የኢትዮጵያ አትሌቶች በተለያዩ ምክንያቶች ላይገኙበት ይችላሉ፡፡ በውድድር ዘመኑ የልጆች እናት የሆኑት በ10ሺ ሜትር የወቅቱ  ሻምፒዮን ጥሩነሽ ዲባባና  በ5ሺ ሜትር የወቅቱ ሻምፒዮን መሰረት ደፋር ከአራስነት ተነስተው ለሻምፒዮናው የሚደርሱበት ሁኔታ የለም፡፡ ከ2 አመት በፊት  በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሞስኮ ላይ ሁለቱ አትሌቶች በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ያስመዘገቡትን ክብር የሚያስጠብቁላቸው አዳዲስ ክዋክብቱ ናቸው። በ10ሺ ወንዶች ከ2 አመት በፊት የተነጠቀውን ክብር ለማስመለስም ቀነኒሳ በቀለ፤ ስለሺ ስህንና እና ሌሎችም ልምድ ካላቸው አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮናው አይሰለፉም፡፡
በ15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ ልምድ ባላቸው አትሌቶች የምትወከለው ምናልባት በማራቶን ውድድሮች ላይ ይሆናል፡፡ በተጨማሪ  በ800 ሜትር የወቅቱ የዓለም ሻምፒዮን መሃመድ አማን ብቻ ክብሩን ለማስጠበቅ ተሳታፊ ይሆናል፡፡ በኦልአትሌቲክስ የአትሌቶች ውጤት ደረጃ  በ800 ሜ በ1334 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው መሐመድ፤ 2015 ከገባ በኋላ በፈረንሳይ በልዩ 1ሺ ሜትር ሩጫ ከማሸነፉም በላይ  በሮም በተካሄደ  የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ800 ሜትር አሸንፏል፡፡
በሻምፒዮናው አዳዲስ ክዋክብት እንደሚሆኑ ከሚጠበቁት መካከል በዳይመንድ ሊግ በ5ሺ ሜትር አስደናቂ ውጤት ላይ የሚገኙት ገንዘቤ ዲባባና አልማዝ አያና እንዲሁም በ1500 የትራክ ውድድር ከፍተኛ ልምድ ያላትና በ10ሺ ሜትር የምትገባው ገለቴ ቡርቃ በሴቶች በኩል ይጠቀሳሉ፡፡ በወንዶች ደግሞ ሐጎስ ገብረህይወት፤ ዮሚፍ ቀጀልቻ እና ሙክታር ኢድሪስ ናቸው፡፡
አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ለዓለም ሻምፒዮናው ሚኒማ ለማምጣት የሰጠው ጊዜ አምስት ሳምንታት ይቀሩታል። ከሁለት ዓመት በፊት ተደርጎ በነበረው በየውድድር መደቡ ሻምፒዮን የሆኑት፤ የ2014 የዳይመንድ ሊግ ያሸነፉት በቀጥታ ያለ ሚኒማ ተሳትፎ ማግኘት ይችላሉ፡፡ያለፈው የዓለም ሻምፒዮኖች እና የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ አትሌቶች ያሏቸው አገራት ከዋናው የ3 አትሌት ኮታ በተጨማሪ በየውድድር መደቡ አራት አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮናው እንዲያሳትፉ ፈቃድ አግኝተዋል፡፡
የተቀዛቀዘው 44ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና
44ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና  ከሰኔ 3 እስከ ሰኔ 7 ቀን በአዲስ አበባ ስታድዬም የተካሄደ ሲሆን ከ37 ክለቦች፣ ከሁለት ከተማ መስተዳድሮችና ከ7 ክልሎች የተውጣጡ 1 ሺህ 282 አትሌቶች ተሳትፈውበታል፡፡ በሻምፒዮናው የመከላከያ ክለብ በ460 ነጥብ አንደኛ ሆኖ አጠናቅቋል፡፡ የኦሮምያ ክልል በ316 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ሲወስድ የባንክ ክለብ በ135 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ በማግኘት ጨርሷል፡፡ ዘንድሮ ሻምፒዮናውን  የሚደግፉ ስፖንሰሮች አለመኖር ትልቅ ፈተናና ክፍተት እንደፈጠረበት ያሳወቀው ፌደሬሽኑ፤ ትልልቅ አትሌቶችን በተለያዩ ምክንያቶች እንዳያሳትፍ መገደዱ መጠነኛ መቀዛቀዝ  እንደተፈጠረበት አመልክቷል፡፡ ባለፉት ዓመታት ሻምፒዮናዎች በቁሳቁስና በገንዘብ ደረጃ ለተወዳዳሪዎች ድጋፍ ሲያቀርብ የቆየው አገር በቀሉ ኩባንያ ጋራድ ሲሆን  ኩባንያው የዘንድሮውን ሻምፒዮና ስፖንሰር እንደማያደርግ ከገለፀ በኋላ ፌደሬሽኑ ሌላ ስፖንሰር ማግኘት አልቻለም። በሌላ በኩል ታዋቂ አትሌቶች በዓለም ዓቀፍ  የዲያመንድ ሊግ፣ የማራቶን ውድድሮች ላይ ለመካፈል ወደ ተለያዩ አገራት በመሄዳቸው ያልተሳተፉበት ሲሆን ሁኔታው የሻምፒዮናውን የፉክክር ደረጃ እንደቀነሰውና  የተመልካቹን ድባብ መቀዛቀዝ እንዳመጣ ተገልጿል፡፡
በሻምፒዮናው በ400፤ 800፤ 1500 ሜትር የመካከለኛ ርቀት ውድድሮች የኢትዮጵያ ተስፋ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ወጣት አትሌቶች ታይተዋል፡፡  አትሌቶቹ በመስከረም ወር በዲሪ ኮንጎ በሚዘጋጀው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ተሳታፊ የሚሆነው የኢትዮጵያ ቡድን አካል ይሆናሉ፡፡ ፌደሬሽኑ በሻምፒዮናው  ለ2008 የውድድር ዓመት ብሔራዊ አትሌቶችን ለመምረጥ ታሳቢ ያደረገ ቢሆንም ሌሎች ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ያገኘበት ሆናል፡፡ በአትሌቲክስ ሻምፒዮናው በክልሎች፣ በከተማ አስተዳድሮች፣ በክለቦችና በማሠልጠኛ ማዕከላት ለሚገኙ አትሌቶች የውድድር ዕድል ለመፍጠር፤ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት፤ ለብሔራዊ አትሌቲክስ ስልጠና አትሌቶችን ለመምረጥ፤ አመቺ መድረክ ሆኖለታል። በዘንድሮው የ44ኛው አትሌቲክስ ሻምፒዮና አስር ያህል አዲስ ክብረወሰኖች ሲመዘገቡ ጉኑ ሲሆን ብዙዎቹ ክብረወሰኖች በሜዳ ላይ ስፖርቶች የተገኙ ናቸው ተብሏል፡፡ በውርወራ ስፖርት በአሎሎ፣ በዲስከስና መዶሻ፣ በከፍታ ዝላይ፣ በዱላ ቅብብል  እንዲሁም በአጭር ርቀት የመሰናክል ሩጫ የተሻሻሉ ክብረወሰኖች ወደፊት አገሪቱ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ከረጅም ርቀት እና ከመካከለኛ ርቀት ባሻገር ሊኖራት የሚችለውን ተሳትፎ የሚያነቃቃ ሆኗል፡፡
ለ10ሺ ሚኒማ በሄንግሎ
በ15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10 ሺህ ሜትር ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፉ አትሌቶችን ለመለየት የማጣርያ ውድድር የተደረገው ባለፈው ሐሙስ በሆላንዷ ከተማ ሄንግሎ ነበር፡፡ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኑ ሄንግሎ ላይ ለ10ሺ ሜትር ሚኒማ ማግኛ የማጣርያ ውድድር  ለአትሌቶች ሲያዘጋጅ የዘንድሮው ለሶስትኛ ጊዜ ነው፡፡ 28 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታዎች የማጣሪያ ውድድሩን ሲሳተፉበት አትሌቲክስ ፌደሬሽኑ በውድድሩ ከአንድ እስከ ሶስተኛ የወጡ አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮና በዚሁ ርቀት እንዲሳተፉ ከመወሰኑም በላይ ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ የወጡ አትሌቶች ደግሞ በኮንጎ ብራዛቪል በሚካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ እንዲሳተፉ ያደርጋል፡፡
በሄንግሎው የዓለም ሻምፒዮና የ10ሺ ሜትር ሚኒማ ለማምጣት በተደረገው የማጣርያ ውድድር በሴቶች ምድብ የመካከለኛ ርቀት ሯጯ ገለቴ ቡርቃ የዓመቱን ፈጣን ሰዓት በ30 ደቂቃዎች ከ53.69 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ አስመዝግባ አሸንፋለች፡፡ በመካከለኛ ርቀት ከፍተኛ ልምድ ያላት ገለቴ ቡርቃ በርቀቱ ገና ለሁለተኛ ጊዜ መወዳደሯ ነበር፡፡  በ2012 እኤአ በለንደን ኦሎምፒክ ላይ በ5ሺ ሜትር ተሳትፋ የነበረችው ገለቴ ቡርቃ አምስተኛ ደረጃ ነበር ያገኘችው፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በ1500 እና በ3000 ሜትር እና በአገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ከፍተኛ ልምድ ያላት ቢሆንም ኢትዮጵያን በመወከል በ10ሺ ሜትር በዓለም ሻምፒዮና ስትሳተፍ ለመጀመርያ ጊዜ ይሆንላታል፡፡ በሄንግሎ የ10ሺ ማጣርያ ለመጀመርያ ጊዜ ርቀቱን በትራክ ላይ የሮጠችው አለሚቱ ሃሮዬ በ30 ደቂቃዎች ከ50.83 ሰከንዶች ሁለተኛ እንዲሁም በርቀቱ ከ2 ዓመት በፊት የነሐስ ሜዳልያ ያገኘችው በላይነሽ ኦልጅራ በ30 ደቂቃዎች ከ53.69 ሰከንዶች በማስመዝገብ የቤጂንግ ቲኬታቸውን ቆርጠዋል፡፡
በወንዶች ደግሞ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና የነሐስ ሜዳልያ ተሸላሚ የነበረው ሙክታር ኢድሪስ በሩጫ ዘመኑ ለሁለተኛ ጊዜ በሮጠው የ10ሺ ሜትር ውድድር የግሉን ፈጣን ሰዓት በ27 ደቂቃዎች ከ17.18 ሰከንዶች በማስመዝገብ ሊያሸንፍ በቅቷል፡፡ በ2011 እኤአ ላይ በርቀቱ የዓለም ሻምፒዮን የነበረውና ከ2 ዓመት በፊት ሞስኮ ላይ በርቀቱ የብር ሜዳልያ አግኝቶ የነበረው ኢብራሂም ጄይላን ውድድሩን አቋርጦ ወጥቷል፡፡ ባለፉት ሶስት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያን ወክሎ የተሳተፈው እና በ2011 እኤአ ላይ የብር ሜዳልያ የወሰደው ኢማና መርጋ በ27 ደቂቃዎች ከ17.63 ሰከንዶች እንዲሁም ሞሰነት ገረመው በ27 ደቂቃዎች ከ18.86 ሰከንዶች በማስመዝገብ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ደረጃ የዓለም ሻምፒዮና ትኬታቸውን ቆርጠዋል፡፡
ለማራቶን  ጊዜያዊ ቡድን በማራቶን
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በቤጂንጉ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በማራቶን ውድድር የሚሳተፉ አትሌቶችን ከሁለት ወር በፊት በመምረጥ ጊዜያዊ ዝርዝሩን ይፋ አድርጓል፡፡ የማራቶን ቡድኑ በሁለቱም ፆታዎች 9 አትሌቶችን የያዘ ሲሆን የቦስተን ማራቶን አሸናፊው እና ከሁለት ዓመት በፊት በዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ የወሰደው ሌሊሳ ዴሲሳ እና የለንደን ማራቶን አሸናፊዋ ትዕግስት ቱፋ ይገኙበታል፡፡ በወንዶች ሌሎቹ አትሌቶች የማነ አዳነ፤ እንደሻው ንጉሴ፤ ጥላሁን ረጋሳ እና ለሚ ብርሃኑ ሲሆኑ በሴቶች ደግሞ ማሬ ዲባባ፤ ትርፌ ፀጋዬ፤ ትግስት ቱፋ እና ብርሃኔ ዲባባ ናቸው፡፡

Read 2759 times