Saturday, 20 June 2015 11:32

ዋልያዎቹ ከሐራምቤ ኮከቦች ለ35ኛ ጊዜ ከመገናኘታቸው በፊት

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 ኢትዮጵያ ከኬኒያ ወደ 4ኛውን የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ (ቻን) ለማለፍ በመጀመርያ ዙር ማጣሪያ ጨዋታ በባህርዳር ስታዲየም ይገናኛሉ፡፡ ቻን የአፍሪካ ክለቦች የሊግ ውድድሮች የሚፈተሹበት፤ ከአገራቸው ወጥተው ለመጫወት ያልቻሉ እና የፕሮፌሽናል ተስፋ ያላቸው የሚታዩበት፤ የውድድሩ አዘጋጅ ለአፍሪካ ዋንጫ መስተንግዶ ያለውን ብቃት የሚለካበት አህጉራዊ ሻምፒዮና ነው፡፡ በመጀመርያ ዙር ማጣርያው ከኢትዮጵያ እና ኬንያ ጥሎ የሚያልፈው ከጅቡቲ እና ብሩንዲ አሸናፊ ጋር ለመጨረሻው ማጣርያ ይገናኛል፡፡
በአትሌቲክሱ ዓለም የቅርብ ተቃናቃኞች የሆኑት ኢትዮጵያ እና ኬንያ በእግር ኳስም የረጅም ጊዜ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡ ነገ ባህርዳር ላይ በአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ የመጀመርያ ዙር ማጣርያ የሚገናኙት ለ35ኛ ጊዜ ይሆናል፡፡ ሁለቱ  ቡድኖች በታሪክ በሁሉም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ግጥሚያዎች በድምሩ 34 ጊዜ ተገናኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያ 14 ስታሸንፍ፤ ኬንያ 12 አሸንፋ በስምንት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡  
ባለፈው ሳምንት በተጀመረው የ31ኛው አፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታቸው ኢትዮጵያ በሜዳዋ 2ለ1 በሆነ ውጤት ሌሶቶን አሸንፋለች፡፡ ኬንያ ደግሞ ከሜዳዋ ውጭ ከኮንጎ  ጋር አንድ እኩል አቻ ተለያይታለች፡፡
በመጀመርያ የነጥብ ጨዋታቸው ድል የቀናቸው አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ  ስለቡድናቸው በሰጡት አስተያየት ‹‹በጣም ጥሩ አጀማመር ነው፡፡ ወደ ጋቦን ለምናደርገው ጉዞ በሩን ከፍተናል ማለት ይቻላል፡፡ ከኋላ ተነስተው ማሸነፋቸው ልጆቼ ከፍተኛ የማሸነፍ ስነልቦና እና ቁርጠኝነት እንዳላቸው አረጋግጦልኛል›› ብለዋል። በአፍሪካ ዋንጫው የምድብ 10 ሌላ ጨዋታ አልጄርያ ሲሸልስን 4ለ0 አሸንፋለች፡፡ ምድቡን አልጄርያ በ3 ነጥብ እና በአራት ግብ ክፍያ ስትመራ ኢትዮጵያ በእኩል 3 ነጥብ እና 1 የግብ ክፍያ ሁለተኛ ሆና ጀምራለች፡፡ ሌሴቶ በባዶ ነጥብ እና 1 የግብ እዳ ሶስተኛ እንዲሁም ሲሸልስ በ4 የግብ እዳ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡
ከኢትዮጵያ ጋር ለሚደረገው ጨዋታ 20 ምርጥ የኬንያ ፕሪሚዬር ሊግ ተጨዋቾችን 2 ቀን ሰርተው  ትናንት ገብተዋል፡፡ ከተጨዋቾች ስብስቡ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያው ከኮንጎ ጋር 1ለ1 ከተለያየው ቡድን 10 ይገኙበታል ከኤፍሲ ሊዮፓርድስ  ከማታሬ ዩናይትድ ከታስከር ኤፊሲ ክለቦችም ተካትተዋል፡፡ በተለይ ለጎሮማሃያ ክለብ የሚጫወተው ግብ ጠባቂው ቦኒፌስ ኦሉዉች እና በአጥቂ መስመር የሚጫወተው እና በኬንያ ፕሪሚዬር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢነት ተፎካካሪ በሆነው አሊ አቦንዶ ብዙ እንደሚጠበቅ ዘገባዎች ጠቁመዋል፡፡
የኬንያ ቡድን የቀድሞ አሰልጣኞች የሃራምቤ ኮከቦች ለአፍሪካ ዋንጨጫ እና ለቻን ውድድር በሚያልፉበት ብቃት ፍፁም እምነታቸውን አየገለፁ ናቸው፡፡ ስኮትላንዳዊው ቦቢ ዊልያምሰን፤ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያው ከኮንጎ ጋር ባደረጉት ጨዋታ አቻ መለያየታቸውን አድንቀው በምናደርጋቸው የማጣርያ ውድድሮች በተለይ በሜዳችን በጭራሽ መሸነፍ የለብንም ብለዋል፡፡  አሰልጣኝ ቦቢ  ኬንያ ጎረቤቷን ኢትዮጵያ ጥላ በማለፍ ለቻን ውድድር እንደምታልፍ ከፍተኛ እምነት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡ የኬንያ ፕሪሚዬር ሊግ በዞኑ እና በአፍሪካ ደረጃ ምርጥ መሆኑን ማስመስከር የሚችለው ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርገው ጥሎ ማለፍ በድል በመወጣት ነው ብለው ኢትዮጵያዎች ኳስን ተቆጣጥሮ የመጫወት ብቃት አላቸው ስለዚህም ከሜዳችን ውጭ ስንገጥማቸው ኳስ እንዳይዙ ማድረግ ስትራቴጂን እንከተላለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

Read 1938 times