Saturday, 20 June 2015 10:49

ከበጀት ዓመቱ ጋር የሚዘጉ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በጀት መዝጊያ ደረሰ አይደል! የምር ግን ከበጀቱ ጋር ሌሎች ነገሮች አብረው ቢዘጉልን አሪፍ ነበር። ልክ ነዋ…ከዓመት ዓመት ‘አልዘጋ’ ያሉ ነገሮች ኑሯችንን እያመሳቀሉብን ነው!
ስሙኝማ…እግረ መንገዴን የበጀት መዝጊያ ነገር ካነሳን አይቀር… አለ አይደል… በዓመት ለአንድ ወር ምናምን በሰኔ ‘ሲቪል ሰርቨንት’ መሆን አሪፍ ይሆን ነበር፡፡ አሀ… ዕቃው በገፍ ነዋ! አስራ ስድስት ‘ሶፍት ፔፐር’፣ አሥራ ሦስት ሳሙና፣ አሥራ ምናምን ስክሪፕቶ… ምናምን በትላልቅ ፌስታል እየሞሉ ወደቤት ነበር፡፡
ኮሚክ ነገር እኮ ነው…ልክ እኮ ‘ወገብ ፍተሻ’ በፓኬጅ የሚካሄድ ነው እኮ የሚመስለው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… እናማ…በሦስት ወር አንዴ አንድ ጥቅል ‘ሶፍት ፔፐር’ ለመስጠት “በጀት የለም…” ምናምን ሲባል ይከርመና ሰኔ ላይ አሥራ ምናምን! እንደሱ ከሆነ አይቀር… አለ አይደል… የጤፍንም ዋጋ ቢያንስ ለክረምቱ ወራት በግማሽ መቀነስ ነዋ! አሀ…የምግብ ፍጆታ እያነሰ ‘ሶፍት ፔፐር’ ቢቆለል…ግድግዳ አንለጥፍበት! (እኔ የምለው…በሰኔ አሥራ ምናምን ‘ሶፍት ፔፐር’ አሁንም አለ እንዴ!)
እናላችሁ…ዋናው በጀት በየዓመቱ ሲዘጋ ‘መዝጊያ’ ያልተደረገላቸውና ሌላኛውን ሚሌኒየም የሚጠብቁ የሚመስሉ መአት ነገሮች አሉ፡፡
ከዓመቱ በጀት ጋር ክፋትም አብሮ ይዘጋልንማ!
የምር እኮ ዘንድሮ የሚያነጋግረው መክፋት አለመክፋታችን ሳይሆን የክፋታችን አይነትና መጠን ነው። “እከሌ ክፉ ሰው ነው…” ለማለትም እያስቸገረ ነው። ልክ ነዋ…ጠቅላላችን በየፊናችን ክፉ እያሰብንና እየሠራን ማን ማንን ሊወነጅል ይችላል!
ጓደኛ ስለጓደኛው የሚያስበው… “እንዴት ላግዘው እችላላሁ!” በማለት ሳይሆን… አለ አይደል… “እንዴት አድርጌ እገዘግዘዋለሁ…” አይነት የሆነበት የክፋት ዘመን፡፡
የአንድ እናት የአንድ አባት ልጆች… “የወላጆቻችንን ንብረት እንዴት በፍትሀዊነት እንከፋፈላለን?” ሳይሆን… “እንዴት አድርጌ ኬሎቹ በላይ ድርሻ እወስዳለሁ…” አይነት የሆነበት የክፋት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡
በሽርክና የሚሠሩ የንግድ ሰዎች… “እንዴት አብረን ከፍተኛ ደረጃ እንደርሳለን…” ከማለት ይልቅ “እንዴት እነሱን ፈንግዬ ድርጅቱን እጠቀልላለሁ…” አይነት የሆነበት የክፋት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡
እኔ የምለው… አብረን እንብላ ምናምን አለመባባል ከክፋት ነው ከብልጥነት የሚመደበው፡፡ ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ካፌ ቁጭ ብሎ ኬክ እየበላ ሳለ አንድ ጓደኛው ይመጣል፡፡ ሰላም ብሎት አጠገቡ ይቀመጣል። ሰውየውም “ከዚች ትንሽ ቅመስ…” የለ፣ “እዚህ ሌላ ኬክ አምጪ…” ብሎ ትእዛዝ የለ… ዝም ብሎ መብላቱን ይቀጥላል፡፡ ጓደኝየውም…
“የምትበላው ኬክ ጣፋጭ ይመስላል፣” ይለዋል።
“አዎ፣ በጣም ይጣፍጣል፡፡”
“ትልቅ ነው፣ አይደል?”
“አዎ ዳቦ ነው የሚያክለው” ብሎ ቡጢ፣ ቡጢ የሚያካክል ጉርሻውን በሹካ እየዛቀ መክተት ይቀጥላል። ጓደኛ ሆዬም…
“ታውቃለህ፣ አንተ በጎረስክ ቁጥር ከንፈሮቼ ይረጥባሉ…” ይለዋል፡፡ (ኸረ የእኛንም አንጀት ‘አንዘፈዘፍከው!’) ይሄኔ ሰውየው ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው… “እንካ አፍህን በዚህ ጥረግ” ብሎ መሀረብ ሰጠውና አረፈ፡፡
ለጓደኞቻችሁ ኬክ መጋበዝ የማትፈልጉ መሀረብ ይዛችሁ ከቤት መውጣታችሁን አትርሱማ!
እኔ የምለው…ምን ዙሪያ ጥምጥም ያስፈልጋል! በቃ… “ከኬኩ አካፍለኝ…” ማለትን የመሰለ ቀጥታ ንግግር እያለ!
ከዓመቱ በጀት ጋር ፍረጃም አብሮ ይዘጋልንማ!
የምር ግን አንዳንድ ጊዜ ሳስበው…ዘንድሮ ‘የማይፈረጅ’ ሰው ካለ ገና ያልተፈጠረ መሆን አለበት፡፡ (ቀሺም አባባል ነው፣ አይደል!) አንድ ጊዜ ትንሽ ልጁ መዋዕለ ህጻናት ያለች ወዳጃችን ልጁ እቤት መጥታ ትምህርት ቤቷ ስለ ዘር ምናምን የሰማችውን ስትነግረው እንዴት እንዳስደነገጠው ሲነገረን ነበር። እናላችሁ… በሙያችሁ ትፈረጃላችሁ፣ በዘራችሁ ትፈረጃላችሁ፣ የእነ እከሌ ዘመድ በመሆናችሁ ትፈረጃላችሁ፣ በትዳር ጓደኛችሁ ትፈረጃላችሁ፣ በምትውሏቸውና በምታመሿቸው ሰዎች ትፈረጃላችሁ፣ በምትሰጡት ሀሳብ ትፈረጃላችሁ፣ በምታነቡት ጋዜጣና መጽሔት ትፈረጃላችሁ፣ ዝም በማለታችሁ ትፈረጃላችሁ…ብቻ ምን አለፋችሁ ዘንድሮ የማንፈራረጅበት ነገር የለም፡፡
ከዓመቱ በጀት ጋር አሉባልታም አብሮ ይዘጋልንማ!
አሉባልታ በዝቷል፡ የምር…አሉባልታ ከመብዛቱ የተነሳ እውነትና ውሸቱን ለመለየት አስቸጋሪ ሆኗል። በ‘ቦተሊካ፣’ በማህበራዊ፣ በሥራ፣ በፍቅር ግንኙነት፣ በጓደኝነት…ብቻ በሁሉም ነገር አሉባልታ በዝቷል። እናላችሁ… የብዙዎቻችን ‘ታሪክ’ እንደ ‘ታሪክ ነጋሪው’ ሆኗል፡፡
የአሉባልታ ነገር ከተነሳ አይቀር ይቺን ቀልድ ቢጤ ስሙልኝማ፡፡ ሁለት ጓደኛሞች እያወሩ ነው፡፡
“እሷ ልጅ ቦይ ፍሬንድ የማይቆይላት ለምንድነው?”
“መቼም ታውቃለህ ቦይ ፍሬንድ ገርል ፍሬንድ ‘ኪሶሎጂ’ ምናምን አለ፡፡”
“አዎ፣ ግን ይሄ ከእሷ ጋር ምን ግንኙነት አለው?”
“ቀኑን ሙሉ ያለማቋረጥ ስለምትለፈልፍ ቦይፍሬንዶቻቸው ምን ሰዓት ይሳሟት!”
አትታያችሁም! እንዲህ ከመባልስ ለምን አንድ ዓመት ሙሉ ዝም ጭጭ አይባልም! እንትናዬዎች ወሬያችሁን ቀንሱማ፡፡
የወሬ ነገር ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሁለቱ ጓደኛሞች ሲያወሩ አንደኛው…
“ጓደኛዬ ሚስቱን ለሦስት ዓመት አንድም ነገር ብሏት አያውቅም፣” ይላል፡፡ ያኛውም…
“ለምን?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“እሷ አውርታ ስላልጨረሰች ተራውን እየጠበቀ ነዋ!”
እኔ የምለው ሀሳብ አለን….እንትናና እንትናዬዎቹም ይሄ የአሮጌ በጀት መዝጋትና አዲስ በጀት መንደፍንም ቢያስቡበት አሪፍ ነው፡፡ ልክ ነዋ… አሀ ሁልጊዜ ‘ጉልበት’ የለ….! ይኸው ዌይን ሩኒ እንኳን ጉልበት እያነሰው አይደል! ቂ…ቂ…ቂ…
ስለዚህ እንትናና እንትናዬዎች የአዲሱን ዘመን በጀት ስታወጡ እንደ መነሻ ሀሳብ ሊሆን የሚችል ጥቆማ… “እነሆ በረከትን በተመለከተ አዲስ የበጀት ቀመር ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም በአቅም መዳከም የተነሳና ጉልበት ለመመለስ የጤፍና የቅቤ ዋጋ ይወርዳል ተብሎ ስለማይታሰብ… እነሆ በረከት በወር አንድ ጊዜ ብቻ ይሆናል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜም በሦስት ወር አንዴ ሊሆን ይችላል…” ምናምን ማለት ይቻላል፡፡
ከዓመቱ በጀት ጋር በ‘አገር ልጅ መቧደን’ አብሮ ይዘጋልንማ!
“የወንዜ ልጅ…” “የአገራችን ልጅ…” እየተባለ ‘የቡድንና የቡድን’ አባቶች በዝቷል፡፡
“እሱ መሥሪያ ቤትማ እንትኖች ብቻ ናቸው የተሰበሰቡበት…”
“ጠቅላላ እኮ የቅርብና የሩቅ የሥጋ ዘመድ ነው ድርጅቱን የያዘው…”
“ሥራ አስኪያጁ እኮ በችሎታ ሳይሆን የአገር ልጅነት እያየ ነው የሚቀጥረው…”
አይነት አስተያየቶችን መስጠት የለመደብን ወደን አይደለም፡፡ በርካታ ሰዎችን የሚያስተዳድሩ ድርጅቶች እንኳን ክፍት ቦታዎች የሚሞሉት በ‘ወንዜ ልጅነት’ ሲሆን አሪፍ ‘ስልጣኔ’ አይደለም፡፡
የምር እኮ… በምግብ ቤቶች እንኳን በ‘አገራቸው አፍ’ ሲያናግሯቸው ባዶው ሜዳ እንኳ ‘እስኪያደናቅፋቸው’ የሚሯሯጡ አስተናጋጆች ይገጥማሉ፡፡ “እንትናዬ…ሥራ አስኪያጁ የአገራችን ሰው ነው አሉ፡፡ ለምን ሄደሽ አታናግሪውም!” ተብለሽ አታውቂም!
እናላችሁ… ከዓመቱ በጀት ጋር አብረው ቢዘጉልን የምንመኛቸው መአት ነገሮች አሉ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2845 times