Saturday, 20 June 2015 09:59

የአልፋ ባለ አክሲዮኖችና አመራሮች እየተወዛገቡ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

ትርፉ ከ30 ሚ. ወደ 1.5 ሚ አሽቆልቁሏል ተብሏል
ካፒታሉን በአስተማማኝ ደረጃ እያሳደገ ነው - አመራሩ

    አልፋ የትምህርትና ስልጠና አክሲዮን ማህበር በአስተዳደር ድክመት ለኪሳራና ለውድቀት እየተዳረገ ነው ሲሉ አንዳንድ ባለአክሲዮኖች ስጋታቸውን የገለፁ ሲሆን የማህበሩ ስራ አመራር ቦርድ በበኩሉ፤ አክሲዮኑ ቋሚ ንብረት እየፈራ በመሆኑ የኪሣራና የውድቀት ስጋት የለበትም ብሏል፡፡ ኩባንያው ባለፉት 7 አመታት አመታዊ ትርፉ፣ የተማሪዎች ቁጥርና ተደራሽነቱ እያሽቆለቆለ መምጣቱን የሚገልፁት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ ኩባንያውን ከገባበት ቀውስ ለማውጣት አሁን ያለው ቦርድም ሆነ ስራ አመራር ጥረት ሲያደርግ አይታይም ብለዋል፡፡ አሁን ያሉት የስራ አመራሮችም ሆኑ የቦርድ አባላት በሌላ መተካት እንደሚገባቸው በተደጋጋሚ ማመልከታቸውን የሚጠቅሱት ከቅሬታ አቅራቢዎቹ አንዱ አቶ ሽፈራው ተስፋዬ፤ አሁን ያለው የስራ አመራርም ሆነ የቦርድ አባላት በአክሲዮኑ ላይ ለደረሰው ኪሣራና ውድቀት ተጠያቂ ናቸው ይላሉ፡፡
አመራሩ በኩባንያው ላይ አድርሷል ያሉትን ጉዳትም ይጠቅሳሉ - አቶ ሽፈራው፡፡ ባለሀብቱን በማሳተፍና የቢዝነስ አማካሪዎችን በማስጠናት የኩባንያው ችግሮች ታውቀው መፍትሔ እንዲፈለግ ባለማድረጉ፣ የተማሪ ቁጥር እንዳይቀንስ ከተቻለም እንዲጨምር ምንም ዓይነት ጥረት አለማድረጉን ቅሬታ አቅራቢው ገልፀዋል፡፡
ኩባንያው በፊት ከነበረው በአመት 30 ሚሊዮን ትርፍ ወደ 1.5 ሚሊዮን ብር አመታዊ ትርፍ መውረዱን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ አዳዲስ ተማሪዎችን ወደ አልፋ ለመሳብ ምንም አይነት ጥረት ባለመደረጉ በ2000 ዓ.ም ከነበረው የርቀት ተማሪ ቁጥር ከ20ሺህ በላይ ቀንሷል ይላሉ፡፡ ብዙ ሺህ ተማሪ መያዝ በሚችል ህንፃ በአሁን ወቅት 141 ተማሪዎች ብቻ በመደበኛ የድግሪ ፕሮግራም እየተማረ ነው የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ የኩባንያው የሠራተኛ ቁጥርም እየቀነሰ ነው፤ እስከ 100 የሚደርሱ ሠራተኞች የተባረሩበት ሁኔታም አለ ብለዋል፡፡ አንዳንድ የትምህርት መስኮችም እስከመዘጋት መድረሳቸውን የሚጠቅሱት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ይህ ሁሉ ሲሆን አመራሩ ምንም አይነት የማስተካከያ እርምጃ አለመውሰዱን ጠቁመው አመታዊ የአክሲዮን ክፍፍል ድርሻችንም እጅግ አሽቆልቁሏል ይላሉ፡፡ የኩባንያው የስራ አመራር ሰብሳቢ ዶ/ር ብርሃኔ አስፋው ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ለቅሬታዎቹ በሰጡት ምላሽ፤ አክሲዮን ማህበሩ 1960 ባለአክሲዮኖች
እንዳሉት ጠቁመው፣ “ኩባንያው ለረጅም ጊዜ ትርፋማ ሆኖ ዘልቋል፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የተለያዩ የግል ህንፃዎችንና ት/ቤቶችን በመገንባት ቋሚ ንብረቶቹን አስተማማኝ አድርጐ ካፒታሉን ወደ 125 ሚሊዮን ብር አሳድጓል” ብለዋል፡፡ አልፋ የተቋቋመው በዋናነት ትምህርትን ለማስፋፋት ነው ያሉት ዶ/ር ብርሃኔ፤ በዚያው ልክ ባለድርሻዎቹን ተጠቃሚ ለማድረግ በየጊዜው አዳዲስ ፕሮጀክቶችን እየቀረፀ ካፒታሉን በማሳደግ
ላይ መሆኑን ተናግረዋል። የተማሪዎች ቁጥር አሽቆልቁሏል፣ ትርፉም ቀንሷል የሚለውን ቅሬታ በተመለከተም በየአመቱ የተማሪ ቁጥር ሊያሽቆለቁል የቻለው በፊት ብቸኛው የርቀት ትምህርት ሰጪ ስለነበር ነው ያሉት ዶ/ር ብርሃኔ፤ አሁን የግልና የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በአማራጭነት በገበያው በመቀላቀላቸው የተፈጠረ የገበያ ድርሻ ማጣት መሆኑን ተናግረዋል - ዶ/ር ብርሃኔ፡፡ አልፋ እነዚህ አዳዲስ የገበያ ተጋሪዎቹ በመምጣታቸውም ደስተኛ ነው፤ ገበያዬን ተሻሙኝ የሚል ቅሬታ የለውም ያሉት ዶ/ር ብርሃኔ፤ “እኛ ባለአክሲዮኖች አስተማማኝ ሃብት እንዲኖራቸው በየቦታው ህንፃዎችን በመገንባት፣ ከመማር ማስተማር ጐን ለጐን ቋሚ ንብረት እያፈራን ነው” ብለዋል፡፡ የተማሪ ቁጥር አነስተኛ ለመሆኑ ሌላው ምክንያት ብለው ሃላፊው ያቀረቡት “ኩባንያው ከብዛት ይልቅ ለጥራት ቅድሚያ መስጠቱ ነው፤ አላማውም ጥራት ያለው የሠለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት በስራው ዓለም ተመራጭ የሆኑ ተማሪዎችን ማፍራት ነው” ይላሉ፡፡ “የተማሪ ቁጥር በመቀነሱ ትርፋችን ቀንሷል ብለን አልተደናገጥንም” ያሉት ዶ/ር ብርሃኔ፤ ብዙ ቋሚ ሃብት መፍጠራችን ሌላው ስኬታችን ነው ብለዋል፡፡ የአንዳንድ ባለአክሲዮኖች ቅሬታ የመነጨውም በፊት ሲገኝ የነበረው ትርፍ አሁን በመቀነሱ ነው ያሉት የቦርዱ ሊቀመንበር፤ ኩባንያው ግን አዳዲስ ፕሮጀክቶችን እየቀረፀ በየጊዜው ካፒታሉን በአስተማማኝ ደረጃ እያሳደገ ነው ብለዋል። ትርፉም ቢሆን በአስጊ ደረጃ እየቀነሰ አለመሆኑን ያስረዱት ዶ/ር ብርሃኔ፤ አሁንም ኩባንያው አትራፊ መሆኑንና ከስሮ እንደማያውቅ ተናግረዋል፡፡ “የትምህርት ዘርፍ እንደሌላው ንግድ አይደለም፤ ብዙዎቻችን በዚህ ዘርፍ የተሠማራነው ጥራት ያለው ትምህርት ከሠጠን፣ ለወደፊት አትራፊ መሆን እንደምንችል በማሰብ ነው” ብለዋል - ዶ/ር ብርሃኔ፡፡   

Read 4018 times