እንግሊዛዊቷ የፖፕ ሙዚቃ ኮከብ አዴሌ ዘንድሮም የዓለም የሙዚቃ ገበያን በበላይነት ተቆጣጥራ እንደቀጠለች ታወቀ፡፡ “21” በተባለው አልበሟ የቢልቦርድ ምርጥ 200 አልበሞች ሳምንታዊ ደረጃን ለ16ኛ ጊዜ በአንደኛነት በመምራት ሪከርድ መስበሯን ቢልቦርድ አመልክቷል፡፡ አልበሟ በቢልቦርድ ታሪክ ለ16 ሳምንታት አንደኛ ደረጃ በማግኘት የተሳካለት 20ኛው አልበም ሆኖ ሲመዘገብ በ1998 እ.ኤ.አ የታይታኒክ ሳውንድትራክ የሆነው አልበም ያስመዘገበውን ክብረወሰንም ተጋርቷል፡፡ አልበሙ ባለፈው ዓመት በሰሜን አሜሪካና በእንግሊዝ ብቻ ከዘጠኝ ሚሊዮን ቅጂ በላይ በመሰራጨት የዓመቱን ከፍተኛ ሽያጭ አስመዝግቧል፡፡ “21” ባለፈው ሳምንት 104ሺ ቅጂ የተሸጠ ሲሆን ለ33 ሳምንታት ከ100ሺ በላይ ተቸብችቦ የአዴሌን የበላይነት ማረጋገጥ ችሏል፡፡