Saturday, 13 June 2015 15:18

የሙጋቤ ʻየእንጀራ ልጅʼ በግድያ ተከስሶ 800 ዶላር ተቀጣ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የዚምባቡዌው ፕሬዚደንት ሮበርት ሙጋቤ፤ የእንጀራ ልጅ ረስል ጎሬራዛ ባለፈው የካቲት በመዲናዋ ሃራሬ ማንነቱ ያልተገለጸን ግለሰብ በመኪናው ውስጥ ገድሏል በሚል ተከሶ ፍርድ ቤት መቅረቡንና ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ 800 ዶላር እንዲከፍል እንደተፈረደበት ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ የበኸር ልጅ የሆነው የ31 አመቱ ጎሬራዛ፣ በሃራሬ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ ድርጊቱን መፈጸሙን በማመን እንደተጸጸተ ገልጾ፣ ይቅርታ እንዲደረግለት ጠይቋል። ፍርድ ቤቱም የመንጃ ፈቃዱን ነጥቆ እስር ቤት ሊወረውረው ቢያስብም፣ መጸጸቱን አይቶ በገንዘብ ቅጣት ብቻ እንዳለፈው አስታውቋል፡፡
ግለሰቡ በእስር አለመቀጣቱ በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎችን እንዳስደነገጠ የገለጸው ዘገባው፣ በተመሳሳይ ወንጀል የተከሰሱ ሌሎች ወንጀለኞች በሁለት አመታት እስር እንደተቀጡ አስታውሷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ማስተላለፉን ተከትሎ የእስር ቤቱ ሃላፊዎች ተከሳሹን በደንቡ መሰረት ከፍርድ ቤቱ ወደ ነበረበት እስር ቤት በመውሰድ የተቀጣውን የገንዘብ ቅጣት ከከፈለ በኋላ እንዲለቀቅ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ፣ የመንግስት የደህንነት አካላት ሊከላከሏቸው እንደሞከሩም ዘገባው አክሎ ገልጧል።

Read 1274 times