Saturday, 13 June 2015 15:04

በግብጽ ስቴዲየም ብጥብጥ ያስነሱ 11 ሰዎች ሞት ተፈረደባቸው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

- በብጥብጡ ከ70 በላይ ሰዎች ሞተዋል
ከሁለት አመታት በፊት አልማስሪ እና አልሃሊ በተባሉት የግብጽ እግር ኳስ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል በፖርት ሲቲ ስቴዲየም የተከሰተውንና ከ70 በላይ ሰዎች የሞቱበትን ብጥብጥ በማነሳሳት የተከሰሱ 11 ግብጻውያን የሞት ቅጣት እንደተጣለባቸው ሲ ኤንኤን ዘገበ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በካይሮ የተሰየመው ችሎት በግብጽ የእግር ኳስ ታሪክ አስከፊው የተባለለትንና ህጻናትን ጨምሮ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉበትን ይህን ብጥብጥ በማነሳሳታቸው የሞት ቅጣት ከጣለባቸው ከእነዚሁ 11 ግለሰቦች በተጨማሪ፣ በብጥብጡ ተሳትፈዋል ባላቸው ሌሎች 40 ሰዎች ላይም የእስር ቅጣት ጥሏል፡፡
ተመልካቾቹ እርስበርስ በድንጋይ፣ በካራና በገጀራ በአስከፊ ሁኔታ የተጨፋጨፉበት ይህ ከፍተኛ ብጥብጥ መከሰቱን ተከትሎ፣ ግብጽ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ስታዲየም እንዳይገቡ እገዳ መጣሏንና ጨዋታዎች በዝግ ስቴዲየም ሲከናወኑ መቆየታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ በሂደትም የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ተመልካቾች ብቻ ወደ ስቴዲየም እንዲገቡ መፈቀዱን ገልጧል፡፡
በግብጽ ከዚያ በኋላም የእግር ኳስ ደጋፊዎች ብጥብጥ መከሰቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው የካቲት ወር ላይም የዛማሌክ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች ባስነሱት ብጥብጥ 19 ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን አክሎ ጠቁሟል፡፡

Read 1231 times